1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጠልሰም፤የበይነ-መረብ የጥበብ ገበያ

ረቡዕ፣ መስከረም 11 2015

ጠልሰም የበይነ-መረብ የጥበብ ዕልፍኝ/online Art Gallery/ የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች ዲጅታል ቴክኖሎጅን ተጠቅመው የጥበብ ስራዎቻቸውን በመላው ዓለም ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ነው። በዚህ የተነሳ መድረኩ በአጭር ጊዜ ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ ነው ተብሏል።

Telsem Galerie von Abrham Yilma
ምስል፦ Abrham Yilma/Anthony Boyd Graphics

ዲጂታል መድረኩ የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ስራዎችን በመላው ዓለም ተደራሽ ያደርጋል

This browser does not support the audio element.


በዓለማችን የሚታየው የሳይንስ እና የቴክኖሎጅ እድገት የግብይት ስርዓትን እየለወጠ መጥቷል።በኢትዮጵያም በቴክኖሎጅ አማካኝነት ወደ ዓለም አቀፉ ገበያ ዘልቆ ለመግባት የሚያስችሉ ዲጅታል መድረኮች ብቅብቅ ማለት ጀምረዋል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ትኩረቱ የኢትዮጵያ ስዓሊያንን ስራ ለሽያጭ በሚያቀርብ «ጠልሰም» በተሰኘ የበይነመረብ መገበያያ ላይ ነው። 
ሕይወትንና ተፈጥሮን ይበልጥ እንድንወድና እንድናደንቅ ከሚያደርጉ ድንቅ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች መካከል ስዕል አንዱ ነው። ስዕል በሀገራችን በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ጥንታዊ ጥበብ ቢሆንም ለጥበቡም ሆነ ለጥበበኞቹ የተሰጠው ትኩረት ግን አነስተኛ መሆኑ ይነገራል። ይህንን ችግር ተሻግረው በግል ጥረቶቻቸው በጥበቡ የሚገፉም  የስዕል እና የቅርፃቅርፅ ስራ ከውሱን የጥበብ ጋለሪዎች እና አልፎ አልፎ ከሚዘጋጁ  አውደርዕዮች በስተቀር ሰፊ ገበያ  አልተፈጠረለትም።በሌላ በኩል በነዚሁ ውስን ጋለሪዎች  ስዕሎቻቸውም ቢሸጡ እንኳ ለኮሚሽን የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ  በመሆኑ ጥበበኞቹ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ ነው።የኮምፒዩተር ሳይንስ ባለሙያው አብርሃም ይልማ ከሁለት ዓመት በፊት ትምህርቱን አጠናቆ  ወደ ስራ ሲገባ  የተመለከተው ይህንኑ ችግር ነው። 
ከዚህ በተጨማሪ ስዕል መግዛት የሚፈልጉ ሰዎችም በቀላሉ ማግኘት እንደማይችሉ ተገነዘበ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም አብርሃም የኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያውን ተጠቅሞ ከዓመት በፊት በጎርጎሪያኑ 2021 መጨረሻ ጠልሰም የተባለ የበይነመረብ  መገበያያ መድረክን  መሰረተ።ለመሆኑ ጠልሰም የሚለው ስም ለዲጅታል መድረኩ መጠሪያነት ለምን ተመረጠ? «ጠልሰም ማለት በመጀመሪያ ትርጉሙ አምሳያ፣ ተምሳሌት፣ ቅርጽ፣ ሀረግ የክታብ ጽሁፍ ማለት ሊሆን ይችላል። የጥንታዊ የስዕል ጥበብ አካል ነው። በሽታ ለመከላከል ከመናፍስት ለመጠበቅ ይጠቀሙበት የነበረ የጥንት ጥበብ ነው። በተለያዩ የጥንታዊ መጽሐፍቶች ላይ ይገኛል ።ይህንን መጠቀማችን በኢትዮጵያ ስእል አዲስ ነገር አለመሆኑን እና ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ አገልግሎት ይውል እንደነበረ ለማሳየት ነው።» በማለት ገልጿል። 
ጠልሰም የበይነመረብ የጥበብ ዕልፍኝ/online  Art Gallery/  የኢትዮጵያ ሰዓሊዎች ዲጅታል ቴክኖሎጅን ተጠቅመው የጥበብ ስራዎቻቸውን በመላው ዓለም ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ነው። በዚህ የተነሳ አብርሃም እንደሚለው መድረኩ በአጭር ጊዜ ጥሩ ተቀባይነት እያገኘ ነው። 
በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሳይንስ እና የቴክኖሎጅ እድገት የዓለማችንን የግብይት ስርዓትን ለውጧል።ይህ የቴክኖሎጂ እድገት የመረጃ ልውውጥን እና  ተደራሽነትም እያሰፋ ነው። ከዚህ አንፃር ጠልሰምን የመሳሰሉ የዲጅታል የጥበብ ገበያዎች ገዥዎች እና ሻጮች በዲጂታል መንገድ መስተጋብር እንዲፈጥሩ በማድረግ የጥበብ ስራዎችን  የሽያጭ መጠን  እንዲሁም ግብይቶች የሚከናወኑበትን ፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል።ይህም የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ስዕሎቻቸውን በመሸጥ ሂደት ላይ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመፍታት  ጠቢባኑ ለማሰላሰል እና የፈጠራ ችሎታቸውን ለማስፋት ብዙ ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርጋል።ለጥበቡ እድገት አስተዋፅኦ አለው።

ምስል፦ Abrham Yilma/Anthony Boyd Graphics
ምስል፦ Abrham Yilma/Anthony Boyd Graphics
ምስል፦ Privat

አብርሃም እንደሚለው የስዕል ስራ የሚያስገኘው ገቢ ብዙም ባለመሆኑ ፊታቸውን ወደ ሌላ ስራ ያዞሩ ስዓሊያንንም ያነቃቃል።
በሌላ በኩል አሁን አሁን በመጠኑ መሻሻል ቢታይበትም በኢትዮጵያ ስዕል እና ቅርፃቅርፅን የመግዛት ባህል እምብዛም ኢይደለም።በዚህ የተነሳ የጥበቡ ገበያ በአብዛኛው በውጭ ሀገር ጎብኝዎች እና ተጓዦች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ይነገራል። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የእንቅስቃሴ ገደብ፤ ቆይቶም በሀገሪቱ የሚታየው አለመረጋጋት እና ግጭት የጎብኝዎች ቁጥር እንዲቀንስ በማድረጉ የስዕል ገበያውም ልክ እንደሌሎቹ ዘርፎች መቀዛቀዝ እንደታየበት የጥበቡ ቤተሰቦች ይገልፃሉ።ከዚህ አኳያ ጠልሰም የዲጅታል መገበያያ መድረክ ገዥዎች  ባሉበት እንዲደርስ በማድረግ ጥሩ ገበያ እየፈጠረ ነው።
በዚህ ሁኔታ ጠልሰም ከተመሰረተ ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ወደ ሃያ የጥበብ ባለሙያዎችን በማሳተፍ በርካታ ስዕሎቻቸውን መሸጥ ችለዋል። የሙሉ ጊዜ ስዓሊ ቴወድሮስ በቀለ ከነዚህ መካከል አንዱ ነው።ስዓሊው በዚህ መድረክ እስካሁን 18 ስዕሎችን የሸጠ ሲሆን፤  መድረኩ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተደራሽነትን ችግር ማስቀረቱን ይገልፃል።
በመድረኩ ለሽያጭ የሚቀርቡት ስዕሎች የተለያዩ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ዋናውን ስዕል እንዲመስሉ ተደርገው የሚጫኑ በመሆናቸው ገዥዎች ጋ ሲደርሱም በድረ-ገፁ ከተመለከቱት ስዕል ጋር አብርሃም እንደሚለው ልዩነት አያሳይም።ያ በመሆኑ እስከ አሁን ድረስ  ምንም አይነት ቅሬታም ሆነ ጥያቄ እንዳልደረሰው ተናግሯል። ነገር ግን ደንበኞች በሥዕሉ ካልተደሰቱ እና መድረኩ ላይ ከተመለከቱት  ስዕል  የተለየ ሆኖ ካገኙት  የ7 ቀናት የመመለሻ  ቀነ ገደብ አለው። ስዕሎቹን ከስዓሊያን ለመቀበልም ራሱን የቻለ ሂደት እና አሰራር  አለው።
በጠልሰም የጥበብ እልፍን ደንበኞች የፈለጉትን የጥበብ ስራ ከመረጡ በኋላ የተለያዩ  የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም መግዛት ይችላሉ። በአሁኑ ጊዜ ጠልሰም  የኔፔይ / yenepay/ እና  «ቻፓ» የተባሉትን የክፍያ ዘዴዎች ለሀገር ውስጥ ገዥዎች ፤ለዓለም አቀፍ ደንበኞች ደግሞ ማስተር ካርድ፣ ቪዛ እና ፔይፓል የመሳሰሉ  የክፍያ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ። 
አብርሃም እንደገለፀው መድረኩ ላይ የሚጫኑ ስዕሎች ጥራታቸውን የጠበቁ ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ «ቪዥዋል አርቲስቶች» ማህበር ጋር በመተባበር የሚሰራ ሲሆን፤  የጥበቡን ኢንደስትሪ ለማሳደግም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር  ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግሯል። 
ወጣቱ ፤ለወደፊቱም ትራንሰንድ ዲጅታል ክራፍትስ /Transcend Digital Crafts / በተባለው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያው አማካኝነት  የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንደ ጠልሰም ያሉ በርካታ ዲጅታል አማራጮችን የማቅረብ ዕቅዶች እንዳሉት ገልጿል።

ምስል፦ Abrham Yilma/Anthony Boyd Graphics

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW