1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 300 ገደማ ከሚሆኑ ዑለማዎች ጋር ሊወያዩ ነው

ሐሙስ፣ የካቲት 7 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 300 ገደማ ከሚሆኑ ዑለማዎች (የሙስሊም ምሁራን) ጋር ሊወያዩ ነው። በዉይይቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ምርጫ እና አወቃቀርን በተመለከተ እስካሁን የነበረዉን ዉዝግብ ይፈታል የተባለ ሰነድ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

Äthiopien  Institutioneller Reformausschuss der Muslime
ምስል DW/Y. Gebrezihaber

የደራሲ አህመዲን ጀበል ማብራሪያ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ከሁለት እስከ ሶስት ቀን ይወስዳል ያለዉ ዉይይት የሚደረግበትን ጊዜ  በቅርብ ቀናት ከማለት ሌላ ትክክለኛዉን ቀን አልጠቀሰም። በስብሰባው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለመገኘት መስማማታቸውን ኮሜቴው ገልጿል። ባለፈው ሰኔ የተቋቋመው ይህ ኮሚቴ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ካጠናቸው ሶስት  ጉዳዮች አንዱ የመጅሊስ መዋቅር እና ምርጫ ጉዳይ መሆኑን በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። 
የኮሚቴው ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ እንደተናገሩት የመጅሊስ አባላት ምርጫ “በምን አይነት ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት” በስብሰባ ይወሰናል።  የኮሚቴው ምክትል ጸሐፊ ደራሲ አህመዲን ጀበል ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ ግን በዉይይቱ ላይ እንደሚወሰን ገልጸዋል።“የወደፊቱ የምርጫ ሁኔታ እንዴት ይሁን የሚለው የሚጠናቀቅበት እንጂ በዚያን ቀን ሊመረጥ ከቻለም አስመራጭ ግብረ ኃይሉ ሊመረጥ ይችላል። ከዚያ ውጭ የመጅሊስም፣ የዑለማም ወደፊት ነው። ከዚያ ስብሰባ በኋላ ነው የጊዜ ሰሌዳ ተደርጎለት እና ይፋ ተደርጎ ነው እንጂ በዚያው ፕሮግራም የሚያልቅ አይደለም” ብለዋል።    
አዲስ የመጅሊስ መዋቅር ያዘጋጀዉን የኮሚቴዉና የሙሕራንን ኮሚቴ የመሩት  ደራሲ አህመዲን የተቋሙ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ስለ ምርጫ ሂደቱ የተቀመጠ ክፍል እንዳለ አስረድተዋል። የስብሰባው ተሳታፊዎች ሰነዱን አሻሽለው ወይም እንዳለ ተቀብለው ሊያጸድቁት እንደሚችሉ የሚናገሩት  አህመዲን የወደፊቱ የምርጫ ሁኔታ ከዚያ በኋላ  እንደሚታወቅ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ለዓመታት በዘለቀው የህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ እና ተቃውሞ ከሚነሱ አጀንዳዎች መካከል “የመጅሊስ አባላት ምርጫን ያለ መንግስት ጣልቃ ገብነት በነጻነት ማከናወን” የሚለው ከዋናዎቹ አንዱ ነበር።  
ዘጠኝ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ የሸሪዐ ፍርድ ቤት እና መጅሊስ “ህጋዊነት እንዲታወጅ” መንግሥትን መጠየቁንም በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ “ጥያቄያችን እንደ እስተዛሬው ጥያቄ ነው። ሁልጊዜ ሲጠየቅ ኖሯል። የአሁኑ ጥያቄ ተግባር ላይ ይውላል ብለን ነው የምንጠብቀው” ብለዋል። 
የኮሚቴው አባላት እስካሁን ሲያከናውኑ በቆዩዋቸው ተግባራት ላይ ለመነጋገር ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ነበር። በውይይቱ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተገኝተዋል።

ተስፋለም ወልደየስ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW