1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በባሕር ዳር “በማይገባ ነገር መገዳደል ይብቃን” የሚል ጥሪ አቀረቡ

እሑድ፣ ግንቦት 4 2016

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ጫካ” ለሚገኙ ኃይሎች “በማይገባ ነገር መገዳደል ይብቃን” የሚል ጥሪ አቀረቡ። ጥሪውን ያቀረቡት ለዓመት ገደማ በመንግሥት እና በፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ቀውስ ውስጥ በገባው አማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር የተገነባ ድልድይ ሲመረቅ ነው። ዐቢይ የፋኖ ታጣቂዎችን በሥም ባይጠሩም “ይብቃን ጥፋት” ሲሉ ተደምጠዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአንድ ዓመት ገደማ መረጋጋት በራቀው የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባ ድልድይ ሲመረቅ “ይብቃን መገዳደል፣ ይብቃን ጥፋት ይብቃን” ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

በባሕር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ ዛሬ ተመርቋል

This browser does not support the audio element.

ከአምስት ዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የአባይ ወንዝ ድልድይ ዛሬ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የክልል እና የፌደራል የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተመርቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት “የአማራ ክልል ህዝብ ጥቅም ተነክቷል ያሉና ወደ ጫካ ገብተው የሚታገሉ አካላት አሁን ባለው የአማራ ክልል አስተዳደር ስር ሆነው  ለልክልላቸው ልማት እንዲሰሩ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአማራ ክልል የቀጠለው የመከላከያ ሰራዊትና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት

“...ዛሬ አማራ መሪ አግኝቷል፣ ታማኝና ትጉህ መሪ አግኝታል፣ ‘ለአማራ እቆረቆራለሁ’ የሚል፣ ‘የአማራ ጥቅም ሊነካ አይገባውም’ የሚል፣ ‘አማራ በልኩ መጠቀም አለበት’ የሚል፣ ስለ አማራ መብት፣ ስለአማራ ዴሞክራሲ የሚታገል ማንኛውም ግለሰብና ቡድን፣ ከአረጋ አመራር ስር ሆኖ ክልሉን መጥቀም ስለሚችል፣ ይብቃን መገዳደል፣ ይብቃን ጥፋት ይብቃን፣ ኑ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ፣ ከፕረዚደንታችሁ ጋር ሆናችሁ ክልላችሁን አልሙ፣ ሰላማችሁን ጠብቁ፣ እኛም በሙሉ ልብ ከጎናችሁ ሆነን ለክልላችሁ ሰላም እና ልማት አብረናችሁ እንሰራለን፣ በማይገባን ነገር መገዳደል ይብቃን ልላቸው እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

ዉይይት፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ግጭቶች ለምን አይቆሙም?

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አዲሱ ድልድይ ባህር ዳር ለተጎናፀፈችው ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ተጨማሪ ውበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

“ለክልላችን ርዕሰ መዲና ለሆነችው ባሕር ዳር ቀደምት ምልክቷ ከሆኑት ከጣና ሐይቅና ከዘንባባ ተክሎቿ በተጨማሪ ከዚሁ ስጦታዎቿ ጋር ተሰላስሎ (ይህ ድልድይ) ዳግም ውብና ልዩ መለያ ምልክት ሆኖ ለማገልገል ይኸው በግርማ ሞገስ ከፊታችን ቆሟል” ብለዋል። 

አዲሱ የዓባይ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት፣ 43 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሁለቱም አቅጣጫ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን ያካተተ ነው፡፡

ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን የተባሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት አስተያየት የድልድ ግንባታ በአገራችን ከ17ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ይታወቅ እንደሆነ አስታውሰዋል፣ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ለከተማዋ ልዩ ውበትና የቀድሞውን ድልድይ ጫና የሚቀንስ ነው ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 2.5 ሚሊዮን ማሻቀቡ

“ትልቁ የዓባይ ድልድይ መሰራት ለአማራ ክልል ህዝብና ለባሕር ዳር ከተማ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፣ ትልቅ የምስራች ነው፣ ምክንቱም ከምስራቅ እስከምዕራቡ፣ ከሰሜን እስከ ደቡቡ የሚያገናኘን ድልድይ ነው፤ ይህ ድልድይ መሰራቱ ትልቅ ዋጋ አለው፣ እንደ ድልድይ ማገልገሉ ብቻ ሳይሆን በትልቅ ዲዛይን፣ በትልቅ የስነህንፃ ጥበብ የተገነባ ስለሆ ለቱሪስት መስህብነትም እንደሚያገለግል ተደጋግሞ ተነግሯል፣ እናም ይህ ድልድይ በጣም ትልቅ በረከት ለእኛ ለኢትዮጵያውን በተለይ ደግሞ ለከተማችን ለውቢቷ ባህር ዳር ታላቅ ስጦታና በረከት ነው ብየ አስባለሁ” ነው ያሉት፡፡

ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት የጀመረው አዲሱ የዓባይ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት፣ 43 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሁለቱም አቅጣጫ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን ያካተተ ነው፡፡ የድልድዩ ግንባታ 1 ቢሊዮን 437 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ድልድ በ1950 መጀመሪያዎች ተገንብቶ አንድ ክፍለ ዘመን ያክል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW