1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር ተወያዩ

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2017

"ወሳኝ እና ጠንከር ጠንከር ያሉ" ያሏቸውን ጥያቄዎች እንደነበሯቸው ሆኖም ለማቅረብ ዕድል ማግኘት እንዳልቻሉ የጠቀሱት ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የኢሕአፓ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ይስሓቅ ወልዳይ በመድረኩ በመንግሥት "የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ማወደስ ይበዛ ነበር" ሲሉ ዐቢይ ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት አቋርጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል ።

Äthiopien Addis Abeba 2025 | Premierminister Abiy Ahmed diskutiert mit Oppositionsparteien
ምስል፦ Ethiopian PM Office

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር ተወያዩ

This browser does not support the audio element.

"የፖለቲካ ምኅዳርን መክፈት በ2010 ዓ.ም የወሰንነው ቁልፍ ውሳኔ ነው" ሲሉ የጻፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን "እያከሄድናቸው ካሉ የባለድርሻ አካላት ውይይቶች አካል የሆነ" ያሉትን ውይይት ዛሬ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ጋር ማድረጋቸውንና ዓላማውም "ግብዓት ለመውሰድ የታለመ" ስለመሆኑ ገልፀዋል።

እያንዳንዱ ፓርቲ አራት ተወካዮቹን እንዲያሳትፍ ዕድል በተሰጠበት በዚህ መድረክ ላይ ከተሳተፉ ፓርቲዎች መካከል የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር መብራቱ ዓለሙ የተነሱ ጉዳዮች ምን እንደነበሩ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

"የሰላም፣ የፀጥታ ጉዳይ፣ የዜጎች መታፈን ጉዳይ እና መንግሥት ይህን ነገር ለመፍታት ያለው ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል በብዙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተነስቷል። የኢኮኖሚ፣ የኑሮ ውድነት፣ የሌብነት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት፣ ቀጣዩን ምርጫ የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተው...  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ መብራሪያ ሰጥተዋል"።

"ወሳኝ እና ጠንከር ጠንከር ያሉ" ያሏቸውን ጥያቄዎች ይዘው ቀርበው  እንደነበር፣ ሆኖም ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ዕድል ማግኘት እንዳልቻሉ የጠቀሱት ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የኢሕአፓ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ይስሓቅ ወልዳይ በመድረኩ በመንግሥት "የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ማወደስ ይበዛ ነበር" ሲሉ በዚህ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት አቋርጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል ።

"የሕዝብ ጥያቄ ያልሆነ፣ ሀገራዊ ጥያቄ ያልሆኑ፣ ወደ መፍትሔ የሚሄዱ ሳይሆን መወድስ የበዛባቸውን ጥያቄዎች ለመስማት ፍቃደኛ አይደለንም፣ ይህ ኢሕአፓን አይገልጽም፣ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታም የሚገልጽ አይደለም ብለን ረግጠን ወጥተናል"።

ጥያቄያችሁ ምን ነበር? ብለን ጠይቀናቸዋል።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሲወያዩ ምስል፦ Ethiopian PM Office

"እየተደረጉ ያሉ ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን ለማስቆም መንግሥትዎ ሀሳብ አለው ወይ?" የሚለው ይገኝበታል ብለዋል። የዚህን መድረክ ግብዣ ሳይቀበሉ በውይይቱም ሳይሳተፉ ከቀሩ ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮ አንደኛው ነው። ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ለምን ከዚህ ተሳትፎ እንደታቀቡ ጠይቀናቸው ነበር።

"ከገባንበት አጣብቂኝ ምንም የሚያወጣን ስላልመሰለን ነው"

"በውይይቱ" በመሳተፍ ጥያቄ ማቅረብ ለምን እንዳልፈለጉ የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ ጉዳዩ "ውይይት አይደለም" ሲሉ ወቅሰዋል። ከሰኞ ጀምሮ ሱሉልታ በሚገኘው የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ግቢ ውስጥ ለሁለት ቀናት ያደሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች ትናንት ማግሰኞ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ከዛሬው ውይይት በኋላም ወደዚሁ ማዕከል መመለሳቸውን ለማወቅ ችለናል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 70 ሕጋዊ ፍቃድ የወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ የበላይ ኃላፊ ሜላተወርቅ ኃይሉ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች ነግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ከነጋዴዎች፣ ከመምህራን፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ተከታታይ ውይይቶችን እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW