1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ በጀርመን ፍራንክፈር ከኢትዮጵያውያን ጋር ሊወያዩ ነው  

እሑድ፣ መስከረም 20 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱ ተገለጸ። በፍራንክፈርት ከተማ የፊታችን ጥቅምት 21 (ኦክቶበር 31) ስለሚካሄደው ውይይት እና የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት በተመለከተ ዛሬ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፍራንክፈርት ቆንስላ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ተሰጥቷል።

Deutschland Diskussion im äthiopischen Konsulat in Frankfurt mit Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጀርመን ከኢትዮጵያን ጋር ሊወያዩ ነው

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሐምሌ ወር ማገባደጃ ላይ በአሜሪካ ሦስት ግዛቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተው ጥልቅ ውይይት ያካሄዱት ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ  አህመድ በቀጣዩ ወር መጨረሻ ላይ በፈረንሳይ ፓሪስ እና በጀርመን ፍራንክፈርት ከተሞች ተመሳሳይ ውይይት ከኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚያደርጉ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በአውሮፓ የተለያዩ አገራት የሚያደርጉት ጉብኝትም " በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር "፣ " ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ " በሚል በአሜሪካ ያደረጉት ጉዞ ቀጣይ አካል እንደሆነ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ጄኔራል አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝት ጉዞ መርኃ ግብር ለመረዳት እንደቻልነው ጥቅምት 20 ወደ ጀርመን ርዕሰ መዲና በርሊን በማቅናት ከአገሪቱ ከመራሔተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እና ከተለያዩ የአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ያደርጋሉ። ሜርክል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የሚያካሂደውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በስልክ ጥሪ እንደጋበዟቸው ይታወሳል።  በጥቅምት 20 " ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ " የተባለ ወደ 11 የሚጠጉ የአፍሪቃ አገራት መሪዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ በርሊን ላይ ይካሄዳል። የአፍሪቃ መሪዎች ከጀርመን ጋር ባላቸው የልማት ትብብር ላይ በሚመክረው በዚህ ልዩ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም እንደሚታደሙ ታውቋል። 

በመጨረሻም በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት እና የአውሮፓ ዋና ማዕከል ተብላ በምትጠራው የፍራንክፈርት ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከመላው አውሮፓ የሚሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሚገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ በጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ. ም. ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ይህን ዝግጅት ለማስተባበር ዛሬ ከፍራንክፈርት እና የተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተውጣጡ ከ 80 በላይ የማህበራት እና የተቋማት አደረጃጀት ተወካዮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ተዘጋጅቶ ነበር። ከውይይቱ በኋላ የተዋቀረው የጠቅላይ ሚኒስትሩን አቀባበል የሚያስተባብረው ንዑስ ኮሚቴ የማህበራዊ ጉዳዮች የስፖንሰር አፈላላጊ የሚዲያ እና ቅስቀሳ የመስተንግዶ እና ሎጂስቲክ እንዲሁም ልዩ ልዩ ተግባራትን የሚያከናውኑ አባላትን በፈቃደኝነት ሰይሟል።

በፍራንክፈርቱ ትልቁ የኮሜርስ ባንክ አሬና ስታዲየም በሚከናወነው በዚህ ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ ከ 15 ሺህ እስከ 25 ሺህ የሚገመቱ የለውጡ ደጋፊ ኢትዮጵያውያን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቆንስላ ጄኔራል አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ ገልጸዋል። አቶ ምህረተአብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ መላው ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ላይ በመታደም በአገራችን ለተጀመረው ለውጥ ያላቸውን ድጋፍ እና አጋርነት እንዲገልጹ ጠይቀዋል። የፊታችን ጥቅምት 21 በፍራንክፈርት ከተማ በሚከናወነው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአቀባበል ሥነ-ሥርአት ከመላው አውሮፓ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴም ተጀምሯል። 

ዛሬ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ያነጋገርናቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከር እና ለማገዝ በልዩ ልዩ የልማት እና የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው አገራቸውን ለመርዳት እና በውጭ ያካበቱትንም ዕውቀት እና ልምድ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በማካፈል ከፍተኛ የዕውቀት ሽግግር በማካሄድ የዜግነት ድርሻቸው የመወጣት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል ። 

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW