1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአርባምንጭ የኮንፈረንስ ሪዞርት ምረቃ ላይ ምን አሉ?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2018

በአርባ ምንጭ ሪዞርት የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “አላስፈላጊ ሽኩቻ ከልማት እንዳያስቀረን” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቱሪዝም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ኹነኛ ምሰሶ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የቱሪዝም ባለሙያ ግን የጸጥታ ችግሮችን በማስወገድ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት
የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በዛሬው ዕለት በዛሬው ዕለት ተመርቋልምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአርባምንጭ የኮንፈረንስ ሪዞርት ምረቃ ላይ ምን አሉ?

This browser does not support the audio element.

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርባምንጭ ከተማ በመገኘት በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የተገነባውን የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በዛሬው ዕለት ሥራ አስጀምረዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሪዞርቱ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር “ ኢትዮጵያ ወደ ፊት እንዳትራመድና ወደ ኋላ እንድትጎተት የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የሚፈጥሯቸው ፈተናዎችና ችግሮች ቢኖሩም ሰላምና ብልጽግናን ስለምናስብ እያሸነፍን ጉዟችን እንቀጥላለን “ ብለዋል ፡፡

ኢትዮጵያ  በአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን የብልጽግና ጉዞ መጀመሯን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ  “ ይህ  ምሳሌ የሆነው ዕድገት እንደ አርባምንጭ፣  ዎላይታ ሶዶ፣ ሀዋሳ፣ ነቀምቴ፣ ባሕርዳር፣ ጅማ ፣ ድሬዳዋ እና  ጅግጅጋ ባሉ ከተሞች በተግባር እየታየ ይገኛል ፡፡ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት የ10 ነጥብ 2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዘግባለች“ ብለዋል ፡፡

ዛሬ ለምረቃ የበቃው የአርባምንጭ የኮንፈርንስ ሪዞርት  በግንባታ ጥራቱ ተወዳዳሪ መሆኑን የተናገሩት የማዕድን ሚንስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ “ ይህም ለአርባምንጭ ከተማ መለያ ምልክት ሆኖ የሚያገለግል ነው  “ ብለዋል ፡፡

በ52 ሺህ  ካሬ ሜትር  ላይ የተገነባው  የአርባምንጭ የኮንፈረንስ ሪዞርት የመሰብሰቢያ  አዳራሾች፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች እና ተፈጥሯዊ አቀማመጥን ያካተተ ነው ፡፡  በውስጡ  53 ቅንጡ ቪላዎች እና በሐይቁ ላይ በልዩ ዲዛይን የተገነባ ተንሳፋፊ ሬስቶራንት እንደሚገኝ በምረቃው ሥርዓት ላይ ተገልጿል ፡፡ ሪዞርቱ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል ፡፡

በአርባ ምንጭ ሪዞርት የመረቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “አላስፈላጊ ሽኩቻ ከልማት እንዳያስቀረን” ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

ዶክተር አያሌው ሲሳይ ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ያገለግሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከቱሪዝም ኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ጥናትና ምርምሮቹን በማድረግ ይታወቃሉ ፡፡ በገበታ ለአገር እየተሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ዶክተር አያሌው ይናገራሉ ፡፡

ነገር ግን እስከአሁን የተገነቡት  ምን ያህል ጥቅም እየሠጡ ነው የሚለውን መለስ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዶክተር አያሌው “ በተለይ በቀጣይ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግና የጎብኚዎችን ፍሰት ለመጨመር  መዳረሻዎችን ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራዎች ማከናወን ይገባል ፡፡ በተጨማሪም መንግሥት የፀጥታ ሥጋቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ “ ብለዋል ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል ገበታ ለሸገር ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ገበታ ለትውልድ በተባሉ ፕሮጀክቶች አማካኝነት የዛሬውን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን መገንባታቸው ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW