ጣና ሐይቅ አሁንም ከእምቦጭ ስጋት አልተላቀቀም
ሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2014
የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ልማት አጀንሲ ደግሞ ሥራው የተዳከመው በክልሉ አመራር ትኩረት ማነስና በበጀት እጥረት ነው ብሏል። የእምቦጭ አረምን የማስወገድ ተከታታይ ሥራዎች ካልተሠሩ የሐይቁ ኅልውና አደጋ ላይ እንደኾነ ተናግረዋል።
በአንድ ወር ውስጥ የአረሙን 90 ከመቶ ለማስወገድ በጥቅምት 2013 ዓ.ም ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተጀምሮ መልካም የሚባል ውጤት ተመዝግቦ የነበረ ቢሆንም የታረመውን ማቃጠልና ማስወገድ ባለመቻሉ በጎርፍ ምክንያት አረሙ ወደ ሐይቁ ተመልሶ መግባቱን የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃ አካላት ጥበቃ ልማት አጀንሲ ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ ይናገራሉ። «2013 ዓ ም መቶ በመቶ በዓይን የሚታየውን እናስወግዳለን ብለን እኛ እቅድ ይዘን ነበር፣ የከፍተኛው ተፋሰስ ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ዘጠና ከመቶ እናደርሳለን አለ፣ ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ከተማ አስተዳደር፣ ክልል ቢሮዎች፣ ባለሀብቶች፣ ወደስራ ገባን፣ መሸራረፍ ይኖራል ግን በተባለው ጊዜ ዘጠና ከመቶ ማስወገድ ቻልን፣ ማስወገድ ማለት ማረም ነው፣ ማቃጠል አልቻልንም፣ ቆለልነው፡፡ ስለዚህ ክረምት እንደሚመጣ ታሳቢ አድርገን መስራት ነበረብን…ያ የተከመረው እንደገና ሊያገግም ይችላል ብለን ማሰብ ነበረብን፣ በነበረው ግለት ብንቀጥል ትልቅ ውጤት እናመጣለን።»
አረሙን በማሽን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረትም በችግር የታጠረ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጠዋል። እንደ ዶክተር አያሌው አረሙን በማሽን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት መልካም ቢሆንም የሐይቁ ዙሪያ ጭቃማ በመሆኑ አረሙን ዳር ለማድረግ ፈተና ነው ብለዋል፡፡ አረሙ ከተንሰራፋባቸው 35 ቀበሌዎች መካከል በ30ዎቹ የሰው ኃይል መጠቀም አረሙን ለማስወገድ የሚያስችል ሁኔታ ቢኖርም በ5ቱ የሐየቁ አካባቢዎች ግን አረሙ በማሽን ብቻ ሊወገድ እንደሚችል ጠቁመው፣ አረሙን ሰብስቦና ተቀብሎ ወደ ሌላ ቦታ የሚያጓጉዝ የኤክሰካቫተርና የማጓጓዣ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ስራውን እንደጎዳው አስረድተዋል።
በተሰሩ ስራዎች የአረሙ መጠን ከነበረበት 5000 ሄክታር ወደ ግማሽ ያህሉ ከሐይቁ መወገዱን ያመለከቱት ዶ/ር አያሌው፣ ተከታታይ ስራዎች ካልተከናወኑ የሀይቁ ኅልውና አደጋ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣዩ ዓመትም ስራውን ለማከናወን ቢታሰብም የሚመለከታቸው የክልል አራሮች ቸልተኝነትና የባጀት እጥረት ፈተና እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ ሥጋታቸውን ያስቀመጡት።
አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የጎንደር ዙሪያ ሻሀ ጎመንጌ አርሶ አደሮች ባለፈው ኣመት የተሰራው አረም የማስወገድ ሥራ ውጤታማ የነበረ ቢሆንም አሁን የአረም ማስወገድ ስራው መቋረጡንና አረሙ በሐይቁ ላይ መስፋፋቱን ተናግረዋል። የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ መስፋፋት ጀመረው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ነው። አረሙ የውኃ አካላትን በማጥቃት የሐይቁ መጠን እንዲቀንስና በደለል እንዲሞላ እንደሚያደርግ ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ