ጥር 9 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 9 2014የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የአፍሪቃ ዋንጫ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ግጥሚያውን ዛሬ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በማከናወን ላይ ይገኛል። በምድቡ የመጀመሪያ ግጥሚያው አብዛኛውን ሰአት በ10 ተጨዋች ብቻ ተወስኖ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ በኬፕ ቬርዴ 1 ለ0 እንዲሁም በሁለተኛ ግጥሚያው በአዘጋጇ ካሜሩን የ4 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ዋሊያዎቹ በ33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ስላገኙት ልምድ እና ስለዛሬው ግጥሚያ ቀደም ሲል መግለጫ ሰጥተዋል። ዘገባ ይኖረናል። በርካታ ወሳኝ ተጨዋቾች ለአፍሪቃ ዋንጫ ካሜሩን ባቀኑበት በአሁኑ ወቅት በተከናወነው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ድል ቀንቷቸዋል። በቡንደስሊጋው መሪው ባየርን ሙይንሽን እና ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጋጣሚዎቻችን በድምር 9 ግቦች አንኮታኩተዋል። ኖቫክ ጄኮቪች በውድድሩ ሳይሳተፍ ከአውስትራሊያ ተባሯል።
እግር ኳስ
ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የካሜሩን ቆይታ እና ወቅታዊ ኹኔታ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለኢትዮጵያውያን የስፖርት ጋዜጠኞች በተዘጋጀው የዙም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርተዋል። አሰልጣኙ መግለጫውን የሰጡት የምድቡን የመጨረሻ ግጥሚያ ለማከናወን ሰሞኑን ከካሜሩን መዲና ያውንዴ ወደምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ባፎሳም ከተማ ያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ቡርኪና ፋሶን ከመግጠሙ ቀደም ብሎ ነው። መግለጫውን የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ተከታትላ ቀጣዩን አጠር ያለ ዘገባ ልካልናለች።
ከኢትዮጵያ እና ቡርኪና ፋሶ የዛሬ ግጥሚያ ባሻገር የምድቡ ሌላኛው ጨዋታ ካሜሩን እና ኬፕ ቬርዴም የሚያከናውኑት በተመሳሳይ ሰአት ነው። በ33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር በርካታ በአውሮጳ ሃገራት ሊጎች የሚሰለፉ ተጨዋቾች ተሳታፊ ኾነዋል። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፦ አርሰናል 5 ተጨዋቾቹ ለአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ወደ ካሜሩን አቅንተውበታል። እነሱም፦ ጋቦናዊው ፒዬር-ኤመሪክ አውባሜያንግ፣ ግብጻዊው ሞሀመድ ኤልኔይ፣ ጋናዊው ቶማስ ፓርቴይ፣ አይቮሪኮስታዊው ኒኮላስ ፔፔ እና ቱኒዚያዊው ዖማር ሬኪክ ናቸው።
የጋቦን ብሔራዊ ቡድን የአርሰናሉ አጥቂ ፒዬር -ኤመሪክ አውባሜያንግ እና የፈረንሳይ ኒስ አማካይ ማሪዮ ሌሚና ወደ እየ ቡድናቸው እንዲመለሱ ፈቅዷል። ሁለቱ ተጨዋቾች በኮሮና የተነሳ ልባቸው ላይ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ መኾኑ ተዘግቧል።
ሊቨርፑል በበኩሉ ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላኅ፣ ሴኔጋላዊው ሳዲዮ ማኔ እና ጊኒያዊው ናቢ ኬታን የመሳሰሉ ወሳን ተጨዋቾቹ ለአፍሪቃ ዋንጫ ፉክክር ወደ ካሜሩን አቅንተውበታል። እንዲያም ኾኖ ግን ትናንት ሊቨርፑል አስተማማን ድል አስመዝግቧል።
አልጄሪያዊው አጥቂው ሪያድ ማኅሬዝን ብቻ ወደ ካሜሩን የላከው ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ሦስት ተጨዋቾቹ ወደ ካሜሩን ያቀኑበት ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ ጥሏል። የአቮሪኮስቶቹ ኤሪክ ባይሊ እና አማድ ዲያሎ እንዲሁም የቱኒዝያው ሐኒባል መጅሪብ በአፍሪቃ ዋንጫ የተነሳ ለማንቸስተር ዩናይትድ አይሰለፉም።
ዋነኞቹ አጥቂዎች ሞ ሳላህ እና ሳዲዮ ማኔን ለአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ወደ ካሜሩን የላከው ሊቨርፑል ትናንት ከተስተካካይ ሁለት ጨዋታዎቹ አንዱን አከናውኖ ድል ቀንቶታል። ሊቨርፑል በትናንቱ ጨዋታ ብሬንትፎርድን 3 ለ0 አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሊቨርፑል ወደ ግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ቢችልም የተጋጣሚውን የግብ ክልል ጥሶ ግን ግብ ለማስቆጠር ተስኖት ቆይቶ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ቀንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን አማካዮ ፋቢንሆ የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላት ገጭቶ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ከእረፍት መልስ ኦክላዴ ቻምበርላይን በ69ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ አግብቷል። 74ኛው ደቂቃ ላይ በቻምበርላይን ተቀይሮ የገባው ታኩሚ ሚናሚኖ ሜዳ ውስጥ በገባ በ3 ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋን የማሳረጊያ ግብ ከመረብ አሳርፏል።
14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብሬንትፎርድን ድል ያደረገው ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ በ11 ነጥብ ይበለጣል። በደረጃ ሰንጠረዡ መሪነቱን ያስጠበቀው ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ቅዳሜ ዕለት ቸልሲን ገጥሞ አንድ ለዜሮ አሸንፏል። በዚህም ነጥቡን ወደ 56 ከፍ አድርጓል። ቸልሲ በ43 ነጥቡ ከሊቨርፑል ስር ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ነገ ከብራይተን ጋር ይጋጠማል።
ትናንት በሊድስ ዩናይትድ 3 ለ2 የተሸነፈው ዌስትሀም ዩናይትድ በ37 ነጥብ የ4ኛ ደረጃን ይዟል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት አርሰናል በ35 ነጥቡ የአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 4 ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቶትንሀም በበኩሉ 33 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ቀጣይ ጨዋታዎቹን በአጠቃላይ ማሸነፍ ከቻለ ነጥቡን ከሊቨርፑል እኩል 45 በማድረስ የሦስተኛ ደረጃን የመያዝ ዕድል አለው።
ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት አስቶን ቪላን ገጥሞ ሁለት እኩል በመለያያት ነጥብ ተጋርቷል። በዚህም መሠረት በደረጃ ሠንጠረዡ 32 ነጥብ ሰብስቦ የ7ኛ ላይ ሰፍሯል። የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ የሚገኘው በርንሌ ብዙም ሳይርቅ 17ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጠና ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ዋትፎርድ ጋር ዛሬ ማታ ጋጠማል።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ ግጥሚያ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዐርብ ዕለት ፍራይቡርግን 5 ለ1 ያደባየበት ግጥሚያ በርካታ ግቦች የተመዘገበበት ነው። ቅዳሜ ዕለት መሪው ባየርን ሙይንሽንም ኮሎኝን 4 ለ0 በማሸነፍ የግብ ጎተራ አድርጎታል። ላይፕትሲሽ ሽቱትጋርትን 2 ለ0 እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ቤርሊን ሆፈንሃይምን 2 ለ1፤ ማይንትስ ቦሁምን 1 ለ0 አሸንፈዋል። ቮልፍስቡርግ ከኼርታ ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ሲለያዩ፤ አውግስቡርግ እና አይንትራኅት ፍራንክፉርት አንድ እኩል ወጥተው ነጥብ ተጋርተዋል። በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ ወራጅ ቀጣና ግርጌ 16ኛ ላይ የሚገኘው አርሜኒያ ቢሌፌልድ በደረጃው የመጨረሻ ዘርዝ ከሰፈረው ግሮይተር ፊዩርትስ ጋር ትናንት ተጋጥሞ ሁለት እኩል ተለያይቷል።
የሜዳ ቴኒስ
ሠርቢያዊው የዓለማችን ዕውቅ የሚዴዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች በሀገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በተባረረባት የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ አሸነፈ። ኖቫክ ጄኮቪች የኮሮና ክትባት ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለውድድሩ አውትራሊያ እንዲገባ የተጠው ቪዛ ተሰርዞ ትናንት የተባረረ ሲሆን፤ ዛሬ ሀገሩ ሠርቢያ ገብቷል። ኖቫክ ጄኮቪች አውስትራሊያ የገባው ራስን ለይቶ ከማቆየት ነጻ በሆነ «ልዩ የቪዛ ፈቃድ» መኾኑን ከሁለት ሳምንት በፊት በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ገጹ መግለጡ በበርካታ አውስትራሊያውያን ዘንድ ቁጣ አጭሮ ነበር። የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚንሥትር ስኮት ሞሪሰን ኖቫክ ጄኮቪች ከሀገር ስለተባረረበት ጉዳይ ሲናገሩ፦ «ድንበሮቻችንን በጥብቅ ለማስጠበቅ የተወሰነ» ብለዋል። ብዙ ስደተኞች በዚህ ደንብ እና በሌሎች ሕግጋት በሚጉላሉባት አውስትራሊያ ኖቫክ ጄኮቪዝ ልዩ ፈቃድ አገኘ መባሉ በሀገሪቱ ፖለቲካም በርካታ ምስቅልቅል ፈጥሯል።
ኖቫክ ጄኮቪች በሌለበት የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ውድድር የኦሎምፒክ ባለድሉ ጀርመናዊው በዓለም የሜዳ ቴኒስ ውድድር አጠቃላይ ከፍተኛ ነጥብ በመሰብሰብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሌክሳንደር ዜቬሬቭ የሀገሩ ልጅ ዳንኤል አልትማይርን አሸንፏል። አሌክሳንደር ቀጣይ ተጋጣሚው አውስትራሊያዊው ጆን ሚልማን ነው። በዓለም የሜዳ ቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር (ATP)ፉክክር አጠቃላይ 11015 ነጥብ በመሰብሰብ ኖቫክ ጄኮቪች አሁንም የመሪነቱን ቦታ እንዳስጠበቀ ነው። ሩስያዊው ዳኒል ሜድቬዴቭ በ8935 ነጥብ ይከተላል። አሌክሳንደር ዜቬሬቭ 7970 ነጥብ ይዞ የሦተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ