1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥቁር አሜሪካዊቷ የሂሳብ ሊቅ ፤ካትሪን ጆንሰን ሲታወሱ

ረቡዕ፣ የካቲት 18 2012

በጎርጎሪያኑ 1969 ዓ/ም አፖሎ 11  የተባለች መንኮራኩር  ወደ  ህዋ ስትመጥቅና  ኔል አርምስትሮንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ሲያርፍ ከዚህ ስኬት ጀርባ የአንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ሴት ሚና ከፍተኛ ነበር።ይች ሴት ካትሪን ጆንሰን ትባላለች። ካትሪን የሂሳብ ሊቅ ስትሆን በአሜሪካዉ የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ ለበርካታ ዓመታት አገልግላለች።

USA, Florida, Cape Canaveral: SpaceX-Rakete explodiert kurz nach dem Start
ምስል picture-alliance/J. Cantrell

ካትሪን፤ የአፖሎ 11 የጨረቃ ደርሶ መልስ ቀመር ያሰሉ የሂሳብ ሊቅ ናቸዉ

This browser does not support the audio element.

 

በጎርጎሪያኑ 1969 ዓ/ም አፖሎ 11  የተባለች መንኮራኩር  ወደ  ህዋ ስትመጥቅና  ኔል አርምስትሮንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ ሲያርፍ ከዚህ ስኬት ጀርባ የአንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ሴት ሚና ከፍተኛ ነበር።ይች ሴት ካትሪን ጆንሰን ትባላለች። ካትሪን የሂሳብ ሊቅ ስትሆን በአሜሪካዉ የጠፈር ምርምር ማዕከል ናሳ ለበርካታ ዓመታት አገልግላለች።

ያለፈዉ ሰኞ በ101 ዓመቷ ማረፏ የተሰማዉ  የሂሳብ ሊቅ በአሁኑ ወቅት በኮምፒዩተር የሚሰላዉን  ዉስብስብ የሂሳብ  ስሌት በጭንቅላቷ ና የዚያን ዘመኑን የስሌት መርጃ ወይም «ስላይድ ሩል» ተጠቅማ የናሳን የሮኬት የጉዞ አቅጣጫ ያሰላች ሊቅ ነበረች።በእሷ የሂሳብ ስሌት የአሜሪካ የሕዋ ምርምር ኤጀንሲ ናሳ  ጨረቃ ላይ ጠፈረተኞችን አሳርፎ ማምጣት የቻለ ሲሆን በ1961 ዓ/ም አሜሪካ በአለን ሼፓርድ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ላደረገችው ጉዞ የሮኬቱን  የሒሳብ ስሌት ያዘጋጀችው ካትሪን ነበረች።በቀጣዩ ዓመት በ1962 ዓ/ም ጆን ግሌይ ለተባለዉ አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ተመሳሳይ ስራ ሰርታለች።

«ጆን ግሌይ የመጀመሪያዉ መሬትን የዞረ አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ነዉ።እሱ ትክክለኛዉን ስሌት እንዲሰራለት ይፈልግ ስለነበር ያንን አደረኩለት።እናም የበረራዉን አቅጣጫ ስሌት ሰራሁለት።»ነበር ያለችዉ ካትሪን።

ሥራው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ና ትንሽ ስህተት ቢፈጠር  ለናሳ ጠፈርተኛ  ቡድን  ከባድ ኪሳራ ነበር ።ነገር ግን ካትሪን በሚያስደንቅ ብቃት ጠፈርተኞቹ ጨረቃ ላይ ደርሰዉ  በስኬት ወደ መሬት እንዲመለሱ በማድረግ ሙያዊ ሀላፊነቷንና ችሎታዋን አሳይታለች።

ምስል picture-alliance/newscom/UPI Photo/J. M. B. Cantrell

የአሜሪካዉ የህዋ ምርምር ማዕከል ናሳ ለጠፈር ፕሮግራሙ የሮኬቶቹን የጉዞ አቅጣጫና እንቅስቃሴ እንዲያሰሉለት በ1960ዎቹ   በርካት የሂሳብ ሊቃዉንትን አሰማርቶ ነበር።ቡድኑ የፃታና የዘር ስብጥር ያለበት ቢሆንም ፤በወቅቱ በአሜሪካ በነበረው የዘርና የፃታ መድልዎ የተነሳ ወንድ የሂሳብ ሊቆች ቡድን ከሴቶቹ ተለይተዉ የሚሰሩ ሲሆን ካትሪን ጆንሰን የነበረችበት ጥቁር ሴት የሂሳብ  ሊሂቃን ቡድን ደግሞ ከነጭ ሴት የሂሳብ ሊቆች ጋር እንዳይገናኝ በተለያዩ ቦታዎች ተለይተው ነበር የሚሰሩት።እነዚህ ሴት የሂሳብ ሊቃዉንት በእርሳስ፣ በእጅናና በስላይድ ሩል ተጠቅመው ያሰሉ ስለነበር፤ በወቅቱ “ኮምፕዩተር” ተብለዉ የሚጠሩ ሲሆን ካትሪን ጆንሰን አንዷና ዋነኛዋ ነበረች።

ካትሪን በአሜሪካ በዘመናዊ መልኩ  የሴቶች ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የናሳ የሂሳብ ሊቅ ሆነዉ ካገለገሉ በመቶዎች ከሚቆጠሩና ዕዉቅና ካላገኙ ሴቶች መካከል አንዷ ናት። በአሜሪካዉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ናሳ ለ33 ዓመታት በበረራ ምርምር ክፍል የሰራች ቢሆንም  ስራዋም ይሁን ስሟ በወጉ የሚታወቅ አልነበረም።ዉሎ አድሮ ግን፣ የእሷ እና ለናሳ ይሰሩ የነበሩ ሌሎች ጥቁር ሴት የሒሳብ ሊቃውንት አስተዋፅኦ መታወቅ ጀመረ።በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም ካትሪን በናሳ ላበረከተችዉ አስተዋፅኦ በቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፕሬዝዳንታዊ  የነፃነት መዳሊያ ተሸልማለች ። ባራክ ኦባማ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም ካትሪን በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ስራ ለአዲሱ ትዉልድ ተምሳሌት ነች ብለዉ ነበር።

«ካትሪን በ33 ዓመታት የናሳ ቆይታዋ  የዘር፣ የፃታና የቀለም መሰናክል ሁሉ በመስበር  እያንዳንዱ ሰዉ ሂሳብንና ሳይንስን በማጥናት ወደ ክዋክብት መድረስ እንደሚችል በማሳየት ለአዲሱ ለትዉልድ ፈር ቀዳጅ ሆናለች።»

ምስል Reuters/S. Sibeko

ቆይቶም ይህ ያልተነገረ የሴቶች ታሪክ  በጎርጎሪያኑ 2016 «ሂድን ፊገርስ » በሚል ርዕስ ሆሊዉድ ዉስጥ ፊልም የተሰራበት ሲሆን በዚሁ አመት በተመሳሳይ ርዕስ  ሽተርሊ  መፅሀፍ ተፅፎበታል።በዚህ ፊልም ቶራ ጂ ፒ የተባለች ተዋናይት የሂሳብ ሊቋን ካትሪን ጆንሰንን ባህሪ ወክላ  የተጫወተች ሲሆን የፊልሙ  ማዕከላዊ ጭብጥም በዚችዉ የሂሳብ ሊቅ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ ፊልም በ2017 በ ሶስት ዘርፍ ለኦስካር ሽልማት ታጭቶ የነበረ ቢሆንም በተንቀሳቃሽ ምስል ትግበራ የተዋንያን የአፈፃጸም ብቃት ተሸላሚ ሆኗል።በወቅቱም  ካትሪን ጆንሰን በ98 ዓመቷ ብቸኛዋ በህይወት ያለች የታሪኩ አካል በመሆን በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝታ ነበር።

ጥቁር አሜሪካዊቷ ካትሪን ኮልማን ጎብል ጆንሰን ነሀሴ 26 ቀን 1918 ዓ/ም በምዕራብ ቨርጂኒያ ግዛት ዋይት ሰልፈር ስፕሪንግ በተባለቦታ የተወለደች ሲሆን አባቷ በግብርና ስራ እናቷ ደግሞ በመምህርነት ሙያ የተሰማሩ ነበሩ።ለቤተሰቧ 4ኛ ልጅ ስትሆን በልጅነቷ በቁጥር መጫወት ትወድ ነበር። ካትሪን ትምህርት ቤት ገብታ ጆሜትሪና አልጀብራ እስክትማር አልጠበቀችም ።ቤት ዉስጥ መደርደሪያ ላይ ያሉ ሳህኖችን፣ የሰማይ ክዋክብትን ፣የቤት መወጣጫ ደረጃዎችን በመቁጠር ነበር የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችዉ። ያም ሆኖ እሷና ቤተሰቦቿ ይኖሩበት የነበረዉ ከተማ በወቅቱ ለጥቁር ህፃናት የሚፈቀደዉ እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ እንዲማሩ ስለነበር ቤተሰቦቿ ከተማዋን ለቀቀዉ እሷና ሶስት ታላላቆቿ  ሊማሩ ወደ ሚችሉበት  በ 125 ማይል ርቀት ላይ ወደሚገኜዉ ምዕራብ ቨርጅኒያ የትምህርት ማዕከል ወሰዷቸዉ።ከዚህ የትምህርት ማዕከል ጋር ከተቀናጀ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ካትሪንና ታላላቆቿ ትምህርታቸዉን መከታተል ችለዋል።

ምስል Imago Images/Leemage/Novapix/GSFC/NASA

«ወደ ኮሌጅ ሄደና  ቤት ተከራየልን።ሁሌም በመስከረም ወደ ኮሌጁ እንሄዳለን።በሀምሌ ደግሞ ቤታችን እንመለሳለን።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትና የኮሌጅ ትምህርት ለመከታተል በዚህ ሁኔታ ለስምንት አመታት ተመላለስን»ብላ ነበር ካትሪን በአንድ ወቅት።

ካትሪን  በ10 ዓመቷ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀች ሲሆን በ14 ዓመቷ ወደ የአሁኑ በምዕራብ ቨርጂኒያ ዩንቨርሲቲ የቀድሞዉ ምዕራብ ቨርጂኒያ ኮሌጅ ገብታ የሂሳብ ትምህርቷን ተከታትላለች።በወቅቱም የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ እያለች በኮሌጁ ይሰጡ የነበሩ ሁሉንም የሂሳብ ትምህርቶች ተምራ ጨርሳለች። ያ በመሆኑ  አማካሪዋ በነበረዉና በ1940ዎቹ  በሂሳብ የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን ከያዙ ሶስት ጥቁር አሜሪካዉያን መካከል  አንዱ በነበረዉ ዊልያም ዋልድሮን የተዘጋጀ የተለዬ የሂሳብ ትምህርት በተጨማሪ ክፍለ ጊዜ ይሰጣት ነበር።በ1937 ዓ/ም በሂሳብና በፈረንሳይኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በመያዝ መምህር ሆና ተቀጠረች።

በ1940 የበጋ ወቅት ከፍተኛ የሂሳብን ትምህርትን ለማጥናት ምዕራብ ቨርጂኒያ ዩንቨርሲቲ ተመልሳ የገባች ቢሆንም በወቅቱ ለእሷ ችሎታ የሚመጥን  የትምህርት አይነት የማግኜት ፈተና ገጥሟት ነበር።ከበጋዉ የትምህርት ወቅት በኃላም ነብሰጡር በመሆኗ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዳለች። ከዚያም ከአስር አመታት በላይ ከባለቤቷ ከጀምስ ፍራንሲስ ጎብል ጋር ልጅ በማሳደግና በመምህርነት ሙያ የቆየች ሲሆን በ1952 ዓ/ም ናሳ ጥቁር የሂሳብ ባለሙያ ሴቶችን እንደሚቀጥር በመስማቷ ወደዚያዉ አመራች።ከዚያም በናሳ የፅህፈት ስራ ከሚሰሩና «ኮምፒዩተር» በመባል የሚታወቁትን አነስተኛ የጥቁር ሴት አሜሪካዉያን ቡድንን ተቀላቀለች።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጡረታ እስከተገለለችበት እስከ 1986 ዓ/ም ድረስ ጠፈርተኞችን ወደ ህዋ በመላክ ከ33 ዓመታት በላይ ናሳን ያገለገለች ሲሆን በ101 አመቷም ያለፈዉ ሰኞ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።

ምስል Getty Images/E. Miller

በ2010 ዓ/ም ኒወርክ ታይምስ ለተባለዉ የአሜሪካ ጋዜጣ ካትሪን በሰጠችዉ ቃለምልልስ «እንደማንኛዉም የሂሳብ ሊቅ ጥሩ በመሆኔ ናሳ ስራዬን እንጅ ቀለሜን አልተመለከተም ነበር።» በማለት በወቅቱ  የነበረዉን ሁኔታ ገልፃለች።

የናሳ ሀላፊ ጂም ብራደንስታይንም የካትሪን ህልፈት በኃላ በሰጡት መግለጫ « በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ካትሪን በስራችን ቁልፍ መሪ ነበረች» ሲሉ ተደምጠዋል። የካትሪን ቁርጠኝነትና የሂሳብ ችሎታ የሰዉ ልጆች ከጨረቃ አልፎ ማርስ ላይ እያደረገ ላለዉ ምርምር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የአሜሪካዉ የህዋ ምርምር ማዕከል ናሳ የአፍሪካ-አሜሪካዊቷን  የሒሳብ ሊቅ ካትሪን ጆንሰን እረፍት ተከትሎ በትዊተር ገጹ ባሰፈረዉ መልዕክትም «የካትሪን ብቃት የዘርና የማኅበራዊ መሰናክሎችን መሻገር የቻለ ነው» ሲል አወድሷታል።

 

ፀሀይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW