1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርካታ ሰዎች ለስነ ልቦና ችግር ተዳርገዋል

ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2015

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከቆቦና ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች ብዙዎቹ የስነ ልቦና ችግር እንዳለባቸው ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡“ሰው ከንብረት ዝርፊያ በኋላ የስነ ልቦና ጫና የደረሰበት ነው፣ በተለይ የገጠሩ ማህበረሰብ”ከፍተኛ መሸማቀቅ ታይቷል፣ የተጎዳው ህዝብ የስነልቦና ጉዳቱ እንዲቀረፍ መርዳት ያስፈልጋል፡፡” ብለዋል

Äthiopien | Orthodox Tewahido Church
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

«በጦርነቱ ከ270 ሺህ በላይ ሰዎች ለከፍተኛ ድብርት ተጋልጠዋል»የአማራ ክልል

This browser does not support the audio element.

 በየአካባቢዎቹ በተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስነ ልቦና መጎዳታቸውን አንድ በአማራ ክልል የተደረገ ጥናት አመልክቷል።ከጦርነት ነፃ የወጡ አካባቢ ነዋሪዎችም ላይ የተፈፀሙ አስነዋሪ ተግባራት በአንዳንድ የአካባቢው ሰዎች ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ስብራት መፍጠሩ መስክሯል፡፡ አለምነው መኮንን ከባህርዳር ዝርዝሩን አዘጋጅቷል። 
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በስነ ልቦና የተጎዱ ሰዎችን ማፅናናት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሳስባለች፣ በየአካባቢዎቹ በተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስነ ልቦና መጎዳታቸውን አንድ በአማራ ክልል የተደረገ ጥናት አመልክቷል፣ከጦርነት ነፃ የወጡ አካባቢ ነዋሪዎችም በነዋሪዎች ላይ የተፈፀሙ አስነዋሪ ተግባራት በአንዳንድ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ስብራት መፍጠሩን መስክረዋል፡፡
ባለፉት 2 ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት፣ ባለፉት 4 ዓመታት ደግሞ በተለያዩ ክልሎች የተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች በርካቶችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ሲዳርጉ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለከፍተኛ የስነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና በተባባሪ አካላት ተጠንቶ ባለፈው ግንቦት ይፋ የሆነ ጥናት አንዳመለከተው በሰሜኑ ጦርነት ብቻ በአማራ ክልል 273 ሺህ 239 ሰዎች ለከፍተኛ ድብርት (depression) የተጋለጡ ሲሆን፣ 235ሺህ 802 ሰዎች ደግሞ ለተስፋ ቢስነት (helplessness) የተዳረጉ ናቸው፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦና ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ አንዳንድ ነዋሪዎችም ብዙዎቹ የስነ ልቦና ችግር እንዳለባቸው ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
“ሰው ከንብረት ዝርፊያ በኋላ የስነ ልቦና ጫና የደረሰበት ነው፣ በተለይ የገጠሩ ማህበረሰብ”፣ “በስነልቦና በጣም ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰ፣ ከፍተኛ መሸማቀቅ ታይቷል፣ ብዙ ሰው ስነልቦና ጫና ደርሶበታል፣የሀይማኖት አባቶችም፣ መንግስትም የስነልቦና ባለሙያዎችም በማስተማር የተጎዳው ህዝብ ስነልቦና እንዲመለስ መርዳት ያስፈልጋል፡፡”፣ “የሀይማኖት አባቶች ወደ ተለቀቁ አካባቢዎች ሄደው መጎብኘት ማስተማር አለባቸው”
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ካሊፎርኒያና አላስካ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ በተለይ ለዶቼ ቬሌ እንዳሉት የሀይማኖት አባቶች የማፅናናት ተልዕኳቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
“ዋናው ትልቁ ነገር የእኛ ሥራ ህዝቤን አፅናኑ ነው፣ በተለይ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ጉዳት የደረሰበትን ህዝብ ማፅናናት የእኛ ኃላፊነት ነው፣ ገበሬው፣ ነጋዴው ሰርቶ መኖር የሚፈልግ ህዝብ፣ በትንሹ እግዚአብሔርን አመስግኖ የሚኖር ህዝብ፣ ተፋቅሮ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ያመጣብን የፖለቲካው ችግር ነው፣ እኛ ከፖለቲካው በላይ ሆነን ነው መገኘት ያለብን ”
በሚያልፍ ጦርነትና በሚያልፍ ፖለቲካ በህዝቦች መካከልም ቁርሾ  እንዳይኖርም በትኩረት ማስተማርና መስበክ እንደሚያስፈልግም ብፁዕነታቸው አሳስበዋል፡፡
ብፁዕነታቸው፣“ ፖለቲካ እንደሚያልፍ ህዝባችን ማስረዳት አለብን፣ ለምሳሌ የንጉሱ ፖለቲካ ሲያልፍ አይተናል፣ የደርግ ፖለቲካ ሲያልፍ አይተናል፣ የኢህአዴግም ምንም እንኳ መንፈሱ እንዳለም ቢሆን ሲያልፍ አይተናል፣ የነገውም ያልፋል፣ በሚያልፍ ወጀብ በቀላሉ በቋንቋ በብሔር በጎሳ የተነሳ ህዝቦቻችን እርስ በእርቸው እንዳይጨካከኑ ነው ጠንክረን መስራት ያለብን፡፡” ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ከተጠመደለት ወጥመድ መውጣት መንቃት አለበት ያሉት ብፁዕ አቡነ በርናባስ፣ ብሔራዊ እርቅና ውይይት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
“የአማራና የትግራይ ህዝብ እንዳይገናኝ፣ ኦሮሞውና አማራው እንዳይገናኝ ተቆራርጠው እንዲቀሩ የሚሰሩ አሉ፣ ያ እንዳይሆን ነው መንቃት ያለብን፣ ፖለቲካው ሲያልፍ የህዝቡ አእምሮ ያኔ ብርሀን ያያል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የእርቅ ችግር የለበትም ውስጡ አንድ ነው፣ አሁንም እኮ ህዝቡ አልተለያየም ተጭነውት ያሉት ፖለቲከኞች ናቸው፣ ይህ ሲያልፍ ያልፋል፣ ብሔራዊ እርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጀምሮ የሀይማኖት አባቶችም አንድ ሆነውበት፣ ምሁራንም አንድ ሆነውበት፣ ፖለቲከኞችም ባለስልጣኖችም አምነውበት ለብሔራዊ እርቅ ከተዘጋጀን እግዚአብሔር ራሱ ነው የሚሰራው፣ 24 ሰዓትም አይስድበትም፡፡”
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ካሊፎርኒያና አላስካ ሀገረስብከት ሥራ አስኪያጅና የሲያንቲያጎ ቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስን አስተደዳሪ አባ ሀብተማሪያም በበኩላቸው በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ ማድረጉ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ጠቁመው በስነልቦና የተጎዱ ወገኖችን ማፅናናትና መንፈሳዊ ህይወት መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
“የሀይማኖት አባቶች እንደቀደመው ሳይሆን አሁን የተለየ ትኩረት መስጠት ያለብን የወደቀን መንፈስ ማንሳት ነው የሞተ መንፈስ የወደቀ ስጋን አይሸከምም ነገር ግን ጠንካራ መንፈስ ሁሉንም ነገር መሸከም ይችላል፣ መንፈሳዊ ኃይል መስጠት፣ ማበረታታት፣ ማቀራረብ፣ በተለይ ህዝቡ አንድ አይነት ስነልቦና ያለው ህዝብ ነው ከዚያም ከዚህም ያለው፣ ያን መፍትሄ የሚሰጠን በሰላም፣ በፍቅር በይቅርታ ችግሮቻችን ፈትተን በዘለቄታው ያ ህዝብ አብሮ የሚኖርበትን መንገድ የማመቻቸት ድርሻ የቤተክርስቲያን ድርሻ የሀይማኖት ሰዎች ድርሻ፣ የሁላችን ድርሻ ነው ብየ ነው የማምነው፡፡”
በሰሜኑ ጦርነት ከሰብአዊ ጉዳቱ በተጨማሪ በአማራ ክልል ብቻ በ8 ዞኖች፣ በ87 ወረዳዎችና በ945 ቀበሌዎች ከታህሳስ 7 እስከ ሚያዝያ 30/2014 ዓ ም በተደረገው ጥናት  290 ቢሊዮን ብር  የንብረት ውድመት መመዝገቡ  መረጋገጡን ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ካሊፎርኒያና አላስካ ሀገረስብከት ሥራ አስኪያጅና የሲያንቲያጎ ቅዱስ ገብረኤል ቤተክርስን አስተደዳሪ አባ ሀብተማሪያምምስል Alemenew Mekonnen/DW
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ካሊፎርኒያና አላስካ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስምስል Alemenew Mekonnen/DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW