1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጦርነትና ለወራት የተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ የተፈናቃዮች አቤቱታ

ኢሳያስ ገላው
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018

ጦርነት የምግብ እጥረት ለአራት ወራት የተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን ለልመና እና እንግልት እንደዳረጋቸዉ ተገለፀ።

የደሴ ከተማ ገጽታ በከፊል
የደሴ ከተማ ገጽታ በከፊል ፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Isayas Gelaw/DW

ለወራት የተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ

This browser does not support the audio element.

 

ጦርነት በተደጋጋሚ የሚቆራረጥሰብዓዊ ድጋፍ በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ፈተና መሆኑን ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ። በተደጋጋሚ በአካባቢው በሚፈጠር ግጭት ምንም እንኳን እነርሱ ላይ የከፋ ችግር ባይደርስም ኑሯቸው በሰቀቀን የተሞላ እንደሆነ የሚገልፁት በተሁለደሬ ወረዳ ቱርክ ካምፕ ነዋሪው አዛውንት በመንግሥት በኩል ለአራት ወራት የተቋረጠው የምግብ አቅርቦት ድጋፍ ልጆቻቸውን ይዘው ለልመና እንዲወጡ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ።

«016 ቀበሌ ጠቢሳ የሚባለው ልጆቼን ይዤ ለልመና ወጥቻለሁ። ራህመት አድርጉልን እያልን ነው፤ ክርስቲያኖቹም ጨፌ በሚባል አካባቢ ስለማርያም እያሉ ልመና ተሰማርተዋል።»

የምግብ እጥረት ሌላው የተፈናቃዮቹ ፈተና

በአካባቢው በመንግሥትና እና በፋኖ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት በሚያልበት ጊዜ ከካምፕ ወጥቶ ሥራ ለመሥራት ለወጣቶች ፈተና መሆኑን ያነሳው አስተያየት ሰጭም በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የተከሰተው የምግብ እጥረት ሌላ ፈተና መሆኑን ይገልፃል። በግጭት ምክንያት ወጣቶች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት አልቻሉምም ነው የሚሉት። «በተለይ ወጣቱ ከግቢ አይወጣም፤ ወጥተህ እንኳን ሥራ ለመሥራት ራቅ ያለ ቦታ አይሆንምከየት መጣህ ወዴት ነህ የሚባል ነገር አለ አስቸጋሪ ነው። ከዚሁ ችግር አንጻር ያው የዕለት የምትበላው እና የምትጠጣው አስፈላጊ ነው። የምግብ ጉዳይ ነው ቅስማችንን የሰበረው።» በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሳይሆኑ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ የተደረጉት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተለይም በአምባሰል ወረዳ በጦርነት ውስጥ ለከፋ ችግር እየተዳረግን ነው ብለዋል።

«ጦርነት በሚነሳበት አካባቢ እንደፈለክ ወጥተህ  ገብተህ የቀን ሥ መሥራት አይቻልም። ከዚያም ይተኮሳል፤ ከዚያም ይተኮሳል። በቃ ለእኛ ለስደተኞች ምንም ይሄ የምትለው ነገር የለም። ማንም የሚያዝንልህ የለም።»

በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በየመጠለያው ይገኛሉፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Alemenw Mekonnen/DW

በደቡብ ወሎ ዞን 11 የመጠለያ ጣቢያ አለ

በሐይቅ ከተማ የሚገኘው የመካነ ኢየሱስ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎችም ምንም እንኳን አሁን በመጠለያ ጣቢያው ሰላማዊ ኑሮ እየኖሩ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች ለሥጋት ዳርገውናል ይላሉ። በተጨማሪም የምግብ ድጋፍ መቆራረጥ በመጠለያ ውስጥ ያለውን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎብናል፤ ሲሉም ይናገራሉ። «በጣም ችግር ነው ያለው እኛ ድንጋይ ፈለጥንም የቀን ሥራም ሠራን እንሞካክራለን። በጣም ተቸጋግረን ነበር አሁን እየመጣ ነው ብለውናል። ባለፈው ቢሻናቆ ላይ ተኩስ ነበር። እዚያ ላይ አንድ ቀን ሌሊት ሲታኮሱ አደሩ፤ እንጂ እኛ ጋር ሰላም ነው።»

በደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ ለ265,000 ሰዎች በፌዴራል መንግሥት ከወራት የተቆራረጠ ድጋፍ በኋላ ምግብ ተፈቅዷል ሲሉ አቶ አሊ ሰይድ ይናገራሉ። ይህ ድጋፍም በወቅታዊ ችግር ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች እና በመጠለያ ተለይተው ለሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደርስ ነው።

«በ265,120 ሰዎች የምግብ ድጋፍ በፌደራል መንግሥት በኩል ተደርጓል፤ ግማሹ ደርሷል ግማሹ እየተጓጓዘ ነው ጠቅላላ መጠኑ ወደ 47705 ኩንታል ነው። እህሉ ከወቅታዊ ግጭት ጋር ተያይዞ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት ያደረገነው። በዚያውም ተፈናቃዮች ተመድቦላቸዋል። 

የፀጥታ ሥጋት ያለባቸው መጠለያ ጣቢያዎችን ስለመቀየር   

አሁን ላይ የምግብ ድጋፉን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ የሚያውክ የፀጥታ ችግር የለም ያሉት አቶ አሊ ሰይድ ተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ ተፈናቃዮችን ግን ባሉበት ፀጥታውን የማስከበር ሥራ እንጂ የመጠለያ ካምፕ ለውጥ ማድርግ አንችልም ብለዋል።

 ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW