ጦርነት የጎዳቸው የአፋር ክልል ወረዳዎች ለማገገም እየታገሉ ነው
ሰኞ፣ ኅዳር 5 2015
መምህር መሃመድኑር ዑስማን ከሚኖሩበት ሰሜናዊ የአፋር ክልል ዞን ኢረብት ወረዳ በጦርነት ሳቢያ መረጋጋት በተሳነው አከባቢ ከቀዬያቸውና ከመመህርነት የስራ ገበታቸው ከተፈናቀሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ አሁን ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል፡፡ መምህሩ አሁን ተገኝቷል ባሉት የሰላም ተስፋ በብዛት በጦርነት ከወደሙት የመማሪያ ክፍሎች መካከል በተረፉቱ በውስኖቹ ውስጥ በዚህ ሳምንት የማስተማር ስራቸውን አንድ ብለው መጀመራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ በርግጥ እንደ መምህር መሃመድኑር አስተያየት በጦርነቱ ምክኒያት የተፈናቀለው ማህበረሰብ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀዬው አለመመለሱና ከመሰረታዊ ፍላጎቶች መጓደል ጋር ተያይዘው ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ተማሪዎችም ቁጥር አሽቆልቁሎ መታየቱን አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም መሰረታዊ የአገልግሎት አውታሮችን በነዚህ በጦርነት በተጎዱ አከባቢዎች የመመለሱ ስራ ጊዜ የማይሰጠው ነው ይላሉ፡፡
"የባንክ አገልግሎት በነዚህ አከባቢዎች ከተቋረጠ 2 ዓመት ደፍኗል" ያሉት እኚው ነዋሪ፤ በኬላዎች ላይ በሚወሰዱ ጥብቅ ቁጥጥሮች መሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች አንኳ ወደ እነዚህ አከባቢዎች እንደልብ አለመግባታቸው ኑሮን ፈታኝ አድርጎታል፡፡
በነዚህ በጦርነት ላይ በከረሙ የአፋር ክልል ወረዳዎች አሁን የጦርነት ድምጽ አይሰማም፡፡ በቅርቡ በትግራይ ክልል እና ፌዴራል መንግስት መካከል ተጀመረው የሰላም ሂደትም ተስፋን በማጫሩ ተፈናቃይ ማህበረሰብ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተሻለ ሁኔታ ወደ ቀዬያቸው መመለስ ጀምረዋል፡፡
በሰላሙ ድርድር የአፋር ህዝብ እንደ ሌላው ሁሉ የደስታው ተካፋይ ነው ያሉን ደግሞ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ገዓዝ አህመድ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ገዓዝ ማብራሪያ የአፋር ክልል ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ዞኖች የመሰረታዊ ልማት ዝርጋታዎች ከትግራይ ክልል ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው እኩል የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆንም አስገድዷል፡፡
የሰብዐዊ መብት ተሟጋቹ ጦርነቱ በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከቁሳዊ ውድመትም በላይ ነው ይላሉ፡፡ “ብዙ ሰዎች በዚህ ጦርነት ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከ600 ሺህ የላቁ በስድስቱ ወረዳዎች ብቻ ተፈናቅለው ሰብዓዊ መብታቸውም ክፉኛ ተመሰቃቅሏልም” ነው ያሉት፡፡
በጦርነቱ እጅግ የተጎዳው ህዝብ ሰፊ የስነልቦናም ግንባታ የሚያስፈልገውና የአፋር የጦርነቱ ተጎጂ አከባቢዎች ከትግራይና ሌሎችም በጦርነት ከተጎዱ አከባቢዎች እና ማህበረሰብ ጋር ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑንም ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አብራርተዋል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ሰዎች አፈናቅሏል፤ በቢሊየን የሚተመኑ ሃብት ንብረቶችን ደግሞ አውድሞ የሺዎችን ህይወትም ቀጥፏል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ታምራት ዲንሳ