1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ጦርነት ያዳቀቃትና ረሐብ ያጠላባት ሱዳን

ቅዳሜ፣ ግንቦት 5 2015

ለአንድ ወር ግድም በተጠጋው የሱዳን ጦርነት እስከ ትናንት ድረስ ብቻ ከ750 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል ። ጦርነቱ ከመሀል ሰቅዞ ያስቀራቸው በርካታ ነዋሪዎች ደግሞ የዕለት ምግብም ሆነ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በማጣት እጅግ ተቸግረዋል ።

Sudan Khartum Kämpfe Bürgerkrieg
ምስል፦ Mohamed Nureldin/REUTERS

እስከ ዐርብ ድረስ ከ750 በላይ ሰዎች ተገድለዋል

This browser does not support the audio element.

ለአንድ ወር ግድም በተጠጋው የሱዳን ጦርነት እስከ ትናንት ድረስ ብቻ ከ750 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል ። ጦርነቱ ከመሀል ሰቅዞ ያስቀራቸው በርካታ ነዋሪዎች ደግሞ የዕለት ምግብም ሆነ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በማጣት እጅግ ተቸግረዋል ። የርዳታ እህሎች ከመጋዘኖች ይዘረፋሉ ። መሠረታዊ አገልግሎቶች እጅግ ተገድበዋል ። ሕይወት ለሱዳናውያን በእጅጉ ከብዳለች ።  ሱዳናዊው አህመድ ካህሊድ የጦርነቱን አስከፊነት ካንገሸገሻቸው መካከል አንዱ ነው ። 

«አሳዛኝ ነው ። ሱዳን ውስጥ ያለውን ሁኔታ የሚገልጠው አሳዛኝ የሚለው ቃል ነው ። አሳዛኝ ከሚለው በተሻለ የሚገልጥልን ቃል ማግኘት ብችል ያን እጠቀም ነበር ። ምክንያቱም የምሬን ነው ሁሉም ነገር በሙሉ ቀጥ ነው ያለው ። ቀኑ ሲያልፍ እንኳን ዐይታወቀንም ። »
ሱዳናውያን መሽቶ እስኪነጋ በጭንቅ ተውጠው እንደሚያሳልፉ ነው የሚናገሩት ። በተፋላሚዎች በኩል በተደጋጋሚ የሚደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተደጋጋሚ ይጣሳሉ ። በዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ አነሳሽነት የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የሰብአዊ መርኆዎችን ለማክበር ሐሙስ ዕለት መስማማታቸው ተነግሯል ።  በበነጋታው ዐርብ ግን ካርቱም ከተማ በጦር ጄቶች ማጓራት እና በፍንዳታዎች ነውጥ ስትጨነቅ ነው የዋለችው ። ሱዳናዊው ሐሺም የዕለት ጉርስ እንኳን ለማግኘት ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲኖር ይሻል ። 

ከሞት የተረፉ በርካታ ሱዳናውያን ስደት ገብተዋል ምስል፦ JOK SOLOMUN/REUTERS

«የተኩስ አቁም ይረዳል ። ገቢያቸው የተቋረጠባቸው ሰዎች ጭምር፤ በዕለት ገቢ የሚተዳደሩ እና ኩባንያ ያላቸው ሰዎች ገቢ አግኝተው ሕይወታቸውን ለመታደግ፤ ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም ለመመገብ ተኩስ አቁሙ ያስፈልጋል ። ቢያንስ ተንቀሳቅሰው ገቢ ማግኘት ይችላሉ ። »

ተፋላሚዎች የሰብአዊ መርኆዎችን ለማክበር በሚል መፈራረም ብቻ ሳይሆን ያን በዘላቂነት ማክበር አለባቸው ሲሉ የሚያስጠነቅቁ በርካቶች ናቸው ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሱዳን ውስጥ ነዋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት እንቅስቃሴያቸው እጅግ በተገደበበት በአሁኑ ወቅት የርዳታ እህል ተዘርፏል ። ባለፈው ሳምንት ሱዳን ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ መርኃ ግብር (WFP) 4 ሺህ ቶን የሰብአዊ ርዳታ መዘረፉ በርካቶችን አስቆጥቷል ። እንደ ሱዳናዊው አህመድ ካሊድ በአሁኑ ወቅት ሱዳን ውስጥ ስለ ነገ ማሰብ እንኳን ይከብዳል ። 

«ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነው ። በተለይ በመሠረታዊ የዕለት ፍጆታዎች አቅርቦት ረገድ ። የጤና ሁኔታውን አለመግለጽ ይሻላል ። በጣም መጥፎ ነው ። ጤነኛ የሆነ ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይገባዋል ። ምክንያቱም በርካታ ሐኪም ቤቶች፤ መድኃኒት መሸጫዎች ወይንም ቀለል ያሉ የሕክምና አገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎች ዘንድ መድረስ አይቻልም ። »

ሱዳን ዐይታው የማታውቀው የረሐብ አደጋ ከፊቷ መደቀኑን ባለፈው ረቡዕ የዓለም ምግብ መርኃ ግብር ይፋ አድርጓል ። በጦርነቱ ምክንያትም ሱዳን ውስጥ 2,5 ሚሊዮን ሰዎች በሚቀጥሉት ወራት ረሐብ ሊያጠቃቸው ይችላል ሲልም አስጠንቅቋል።   

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW