ጨረቃ ላይ መንደር የመገንባት ተልዕኮ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2014
ከ 50 ዓመታት በፊት አፖሎ 11 የተባለችውን መንኮራኩር በማምጠቅ የጠፈር ተመራማሪዎች ሰዎችን ጨረቃ ላይ ማሳረፍ ችለዋል። የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ በእንግሊዥኛው ምህፃሩ NASA የሰው ልጆችን ጨረቃ ላይ ማኖር የሚያስችል መንደር ለመገንባት ስድስት የጠፈር ተልዕኮዎችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል።
አርቲሜስ 1 የተባለው የመጀመሪያው እና መንገድ ጠራጊው ጨረቃን የማሰስ ተልዕኮ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም እክል ገጥሞት ለመጭው መስከረም ቀን ተቆርጦለታል። የዛሬውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ጨረቃን የማሰስ ተልዕኮ እና ተግዳሮቶቹን ይቃኛል።
ከ 50 ዓመታት በፊት የጠፈር ተመራማሪዎች ሰዎችን ጨረቃ ላይ ማሳረፍ ችለዋል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ/ ሰኞ ነሀሴ 29 ቀን 2022 ዓ/ም /የአሜሪካዉ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ወደ ጨረቃ የጠፈር ጉዞ አቅዶ ነበር። ተልዕኮው እንደወትሮው ለምርምር ሳይሆን ጨረቃ ላይ ለመኖር የሚያስችል መንደር ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እና ለማሰስ ነበር። «አርቲሜስ 1» እየተባለ በሚጠራው ይህ የመጀመሪያ ተልዕኮ ሰው አልቫ ሲሆን የተልዕኮው አጋሮች የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ እና የአውሮፓ ጠፈር ኤጀንሲ እንደገለፁት፣ ጨረቃን የሰው ልጆች መኖሪያ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የመጀመሪያ ተልዕኮ ነው። ይህ መርሀ ግብር በቀጣይ አምስት ተልዕኮዎችም አሉት።
የዓለም አቀፉ የአስትሮናውቶች ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት እና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ሰሎሞን በላይ እንደሚሉት ይህ ተልዕኮ ጨረቃ እና ማርስ ላይ ለሚደረጉ ምርምሮች ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ይሁን እንጅ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት በሚገኘው ኬኔዲ የጠፈር ማዕከል በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለዚሁ ተልኮ የተዘጋጀችውን ኦሪዮን የተባለች መንኮራኩር የማምጠቁ ስራ እክል ገጥሞታል።በረራው የተስተጓጎለው በአንደኛው የኦሪዮን ሞተር ላይ ችግር ስላጋጠመ መሆኑን ናሳ አስታውቋል። በዚህ የተነሳ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ተልዕኮ ለመጭው መስከረም መጀመሪያ ተላልፏል።ይህ ተልዕኮ ከ2020 ዓ/ም ጀምሮ በተደጋጋሚ በመዘግየቱም በቢሊዮን የሚቆጠር የበጀት ጭማሪ ማስከተሉ እየተገለፀ ነው።
ኔል አርምስትሮንግ በጎርጎሪያኑ ሀምሌ 1969 ዓ/ም አፖሎ 11 የተባለችውን መንኮራኩር ይዞ ጨረቃን ለመጀመሪያ ጊዜ ከረገጠ ወዲህ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች በ1972 ዓ/ም እሰከመጠቀችው አፖሎ 17 ድረስ ስድስት ጊዜ ያህል ወደ ጨረቃ ተጉዘዋል።
ከዚያ ወዲህ ብዙ ነገር ተለውጧል።ሳይንስ እና ቴክኖሎጂም የላቀ መሻሻል አሳይቷል። ያምሆኖ ከአፖሎ 17 ተልዕኮ ወዲህ የሰው ልጆችን ወደ ጨረቃ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት አልሰመረም።ለመሆኑ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ጨረቃን የረገጠው የሰው ልጅ በአሁኑ ወቅት ለምን ወደ ጨረቃ መመለስ አቃተው? ዶክተር ሰለሞን የአየር ንብረት ለውጥ እና ለምርምሩ የሚሰጠውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
ምንም እንኳ በተጠቀሱት ምክንያቶች ወደ ጨረቃ የሚደረገው ጉዞ በአሁኑ ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች ያሉት ቢሆንም፤ እንደ ተመራማሪው ገለፃ ከነ ችግሩም ቢሆን ምርምሩ አስፈላጊ ነው።
በግሪክ አፈ ታሪክ የጨረቃ አምላክ በሆነችው በአፖሎ መንትያ እህት ስም «አርቲሜስ» የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ተልዕኮ በጎርጎሪያኑ 2018 ዓ/ም የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማውም ሰዎችን ወደ ጨረቃ እንደገና መመለስ እና በጎርጎሪያኑ 2017 የተወጠነውን የጠፈር ምርምርን እንደገና የማነቃቃት ዕቅድ ማጠናከር ነው።
መርሀ ግብሩም እስከ 2028 የሚከናወን ስድስት ተልዕኮዎች ያሉት ሲሆን፤ የአሜሪካ እና የአውሮፓ የጠፈር ምርምር ኤጀንሲዎች ከሌሎች በርካታ ሀገራት የጠፈር ምርምር ጣቢያዎች ጋር በትብብር የሚሰራ ነው።
በአውሮፓ የህዋ ሳይንስ ኤጀንሲ የኤሮስፔስ መሀንዲስ የሆኑት ዮርግ ሽሉትስ ለ DW እንደገለፁት የእነዚህ ስድስት የአርቲሜስ ተልኮዎች የመጨረሻ ግብ ሰዎች በ 2025 ዓ/ም ጨረቃ ላይ እንዲደርሱ እና በቀጣዮቹ አመታት በሚደረጉ ጉዞዎች ደግሞ ቋሚ ሰፈራ ለመመስረት ያለመ ነው።
ይሁን እንጅ ከአመታት በኋላ ይተገበራል ተብሎ ለታቀደው /በጎርጎሪያኑ 2030 ለታቀደው/ ጨረቃን የመኖሪያ ቦታ የማድረግ ስራ መንገድ ጠራጊው የመጀመሪያው ተልዕኮ እንኳ የተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ ለሶስት ጊዜ ያህል ተሰርዟል።አሁን እየታዩ ካሉት ችግሮች አንፃር ይህ ዕቅድ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል?
ዶክተር ሰሎሞን በተግባራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ምክያቱም ስራው ብዙ ምርምር እና ትብብር የሚጠይቅ ነው።
ወደ ጨረቃ የሚደረገው ጉዞ ያለምንም እክል መስከረም ላይ በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ ከተከናወነ፤ ኦሪዮን የጠፈር መንኮራኩር በመጀመሪያው ተልኮዋ ጨረቃን በሩቁ በመቃኘት ከ26 እስከ 42 ቀናት ትቆያለች። መንኮራኩሯ ወደ መሬት ከመመለሷ በፊትም ጨረቃን በመዞር ለወደፊት ለሚደረጉ የጠፈር በረራዎች መረጃ ትሰጣለች። እንደ ሽሉትዝ ገለጻ፣ በዚህ ተልዕኮ ወደፊት ለሚጓዘው የጠፈርተኛ ቡድን ሁኔታው ተስማሚ መሆኑን ፍተሻ ይደረጋል። ሌላው በአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ የቁስ ሳይንስ ሊቅ የሆኑት አይደን ኮውሊ እንደሚሉት በቀጣዮቹ የአርቲሚስ ተልዕኮዎች አስቸጋሪውን የጨረቃ ዙሪያ ጨረር ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በሌሎች ፕላኔቶች ላይ ለመኖር የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች በጨረቃ ላይ እንደሚሞከሩ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ሁኔታ የጨረቃ እና የሌሎች ፕላኔቶች የሚደረገው የህዋ ሳይንስ ምርምር ሀገራትን የበለጠ የሀብት ባለቤት እና የሚያደርግ ነው። ይሁን እንጅ የታዳጊ ሀገራት ተሳትፎ በዘርፉ ዝቅተኛ በመሆኑ እንደ ዶክተር ሰሎሞን በወደፊት ዕጣ ፋንታቸው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እና የሚገጥማቸው ችግር ቀላል አይደለም። ስለሆነም የታዳጊ ሀገራት መንግስታት ከአሁኑ ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሀብታም ሀገራትም ፍትሃዊ የህዋ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ታዳጊ ሀገራትን በዘርፉ መደገፍ ይገባቸዋል ብለዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ