ጾታዊ ጥቃት እና ማህበራዊ ችግር ያብቃ ፤ የትግራይ ሴቶች
እሑድ፣ ሐምሌ 2 2015በትግራይ ባሉ ሴቶች ላይ እየደረሰ ነው የተባለ ፆታዊ ጥቃት እና ማሕበራዊ ችግር እንዲያበቃ የሚጠይቅ የሴቶች የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ በመቐለ ተካሄደ። የተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ ይቀጥል፣ የፆታ ጥቃት ይቁም፣ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የፈፀሙት ለሕግ ይቅረቡ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሴቶች እና አጠቃላይ ማሕበረሰቡ ወደ ቀዬው ይመለስ፣ ትኩረት ለእናቶችና ህፃናት የሚሉ እና ሌሎች በርካታ መፈክሮች በዛሬው የመቐለ የሴቶች ሰልፍ ተስተጋብቷል።
ከሰላም ስምምነቱ በኃላም ቢሆን በተለይም በሴቶች እና ህፃናት አስከፊ ማሕበራዊ ቀውስ፣ የፆታ ጥቃት እና ሌሎች ዘርፈብዙ ችግሮች ተጠናክረው ቀጥለዋል የሚል ቅሬታ የያዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ዛሬ በመቐለ እና ሌሎች የትግራይ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። የተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍ ይቀጥል፣ የፆታ ጥቃት ይቁም፣ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት የፈፀሙት ለሕግ ይቅረቡ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሴቶች እና አጠቃላይ ማሕበረሰቡ ወደ ቀዬው ይመለስ፣ ትኩረት ለእናቶችና ህፃናት የሚሉ እና ሌሎች በርካታ መፈክሮች በዛሬው ጠዋት የመቐለ የሴቶች ሰልፍ ተስተጋብቷል።የሐኪሞች የተቃውሞ ሰልፍ በመቐለ
በዋነኝነት የትግራይ ሴቶች ማሕበር በተባለ እና ከ750 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት በሚገልፀው ተቋም አስተባባሪነት የተካሄደው ይህ ሰልፍ፥ ከመቐለ ውጭም በዓዲጉደም እና ሽረ ዛሬ፣ በአክሱም እና ዓዲግራት ነገ ሴቶች ድምፃቸው ማሰማት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል። የትግራይ ሴቶች ማሕበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ ሃይለስላሴ ከጦርነት ጅማሮ ወዲህ ባለው ግዜ በትግራይ ያሉ ሴቶች አስከፊ ሕይወት ላይ መሆናቸው የገለፁ ሲሆን፥ ከሰላም ስምምነቱ በኃላም ቢሆን ችግሮች መቀጠላቸው ጠቁመዋል። የዛሬው ሰልፍ ዋነኛ ጥያቄም እየቀጠለ ያለው የአጠቃላይ ህዝቡ በተለይም ሴቶች እና ህፃናት ስቃይ እንዲያበቃ መጠየቅ መሆኑ ወይዘሮ አበባ ገልፀዋል።ትግራይ ክልል የጡረተኞች የተቃውሞ ሰልፍ
በተለይም በሌሎች ሀይሎች ቁጥጥር ስር ባሉ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም ፆታዊ ጥቃቶች እየተፈፀሙ መሆናቸው ጨምረው የተናገሩት የትግራይ ሴቶች ማሕበር ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አበባ፣ ፆታዊ ጥቃት እንዲቆም፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የትግራይ ሴቶች ይጠብቃሉ ብለዋል። በዛሬው የመቐለ የሴቶች የተቃውሞ ሰልፍ ቁጥራቸው እስከ ሁለት ሺህ የሚገመቱ ሴቶች ወደ መቐለ ጎዳናዎች በመውጣት ድምፃቸው አሰምተዋል።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ