ፈርሶ በቆየው የሸገር ከተማ መንገድ ዳር ቤቶች የነዋሪዎች ቅሬታ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 9 2017
በጡረታ እድሜ ላይ እንደሚገኙ አስረድተው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ትንሽ መጠለያ ሆኖ ከቀራቸው ሌላ መተዳደሪያቸው አድርገው ሲጠቀሙባቸው የነበሩ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ ሱቆች ሙሉ በሙሉ ወድመውባቸዋል። ለደኅንነታው በመስጋት ስማቸውን ሳይገልፁ አስተያየታቸውን ብቻ ያጋሩን አዛውንቱ የሸገር ነዋሪ፤ ለኮሪደር ልማት በሚል በመንግሥት ያለምንም ካሣ የገቢያቸው ብቸኛ ምንጭ የነበሩ ሱቆች በመፍረሳቸው አሁን ያለምንም ገቢ ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል።
«እንደ አጋጣሚ እኔ የምኖረው መንገድ ዳር ነው። ቤታችን ከፈረሰ አሁን ሰባት ወር ደፍኗል። ሥራም አልጀመሩም። በዚያ ላይ ጡረተኛ ነኝ። ቤቴ በመንገድ ዳር መሆኑ ከዚህ በፊት በእጅጉ ሲጠቅመኝ ነበር። ወደ ሰባት ሱቆች ሠርቼ እነሱን በማከራየት እኔን እና አቅመ ደካማ ባለቤቴ በሱ ነበር ኑሮን ስንገገፋ የነበርነው። አሁን ከእነዚያ ሰባት ክፍል ሱቆች አንድም አልቀረኝ ሁሉም ፈርሷል።» ሲሉ እንደ ግል የደረሰባቸውን አስረድተዋል።
«የቤቶች መፍረስ» መተዳደሪያ ማጣት
አቅመ ደካማ እና በሽተኛ መሆናቸውን የገለጹልን ነዋሪው ቤቶቻቸውከፈረሱ በኋላ ከሣ እንኳ እንዳልተሰጣቸው አመልክተው፤ የፈረሱ ቦታዎች ላይም የተሠራ ልማትም አለመኖሩን ተናግረዋል። አያይዘውም ሌላው ቢቀር እስካሁን እንኳ ብንጠቀምበት ለኛም ገቢ ለሚከራዩም ሥራቸውን የሚሠሩበት ይሆን ነበር በማለት ቤቶቹ በፈረሱባቸው ቦታዎች ላይ እስካሁን የተከወነ አንዳችም ልማት አለመኖሩንም አመለክተዋል።
በዚሁ በከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞቹ ለልማት በሚል የሚፈርሱ ቤቶች ምትክ የሌላቸው ናቸው በሚል ከነዋሪዎቹ ቅሬታም አስነስቷል። በዚሁ ከየመንገድ ዳሩ በሚፈርሱ ቤቶች ኑሯቸው መመሳቀሉን ያነሱልን ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ የሰበታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። እንደሳቸው አስተያየት ለድፍን 40 ዓመታት የኖሩበት መኖሪያ ቤታቸው ሊፈርስ ቀን እስኪቆረጥለትም ቀጣይ መዳረሻቸውን አያውቁም።
«አሁን መጥተው ለክተው ዝም ብለው ነው የሄዱ። ከፊት ለፊታችን ያሉ ቤቶች ስለፈረሱ የእኛም ሌላ እጣ ፈንታ የለውም። ስለቀጣይ እጣ ፈንታችን ምንም ሳይሉን ነው መኖሪያችንም መጦሪያችንም የሆነውን ቤታችንን ለዚህ የዳረጉት» ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ለከተማ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት የቀረበ ጥሪ
ነዋሪዎቹ የከተማ አስተዳደሩን ባለሥልጣናት በማነጋገር «የመፍትሄ ያለህ!» ብሉም የተሰጣቸው መፍትሄ አለመኖሩንም ይናገራሉ። «የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሸመ አዱኛን ለማነጋገር ሁለት ጊዜ ተሰብስበን ሄድን ምክትላቸውን አግኝተን አነጋግረናቸው ነበር። ግን ከዚያም በኋላ አባከና ብሎ እልባት የሰጠን የለም። ሌላው ቀርቶ እስካሁን ምንም ባልለማበት ፈርሶ ቁጭ ባለው ቦታ ያከራየውም አከራይቶ የተከራየውም ሠርቶበት ቢሆን መንግሥትም ገቢ የሚያገኝበት እንጂ የሚከስርበት አልነበረም። ካሣ ግምት አሊያም ምትክ ቦታ አልተሰጠን መሄጃ የለንም። እናም ሕዝቡ የሚለው ይህን ነው ብላችሁ ምሬታችንን ከሚመለከተው አካል ጆሮ ብታደርሱልን ብለን ነው» ብለዋል።
ዶይቼ ቬለ የነዋሪዎቹ ቅሬታ ላይ የከተማ አስተዳደሩን ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ጥሯል። የሸገር ከተማ ከንቲባን ዶ/ር ተሾመ አዱኛን ጨምሮ ለከተማ አስተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣናት የእጅ ስልክ ላይ ደውለን ምላሻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ለዛሬ አልሰመረም።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ