ፈንድቃ የኪነ-ጥበብ ማዕከል እንዳይፈርስ ጥሪ ቀረበ
ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2015« ፈንድቃን ማፍረስ የማህበረሰቡን ብዙ ነገር ማፍረስ ነዉ። ፈንድቃ ዘር የለዉም፤ ፈንድቃ ኢትዮጵያን የያዘና ሁሉን ያቀፈ ነዉ።»
አዲስ አበባ እምብርት ካዛንችስ ላይ የሚገኘዉ የፈንዲቃ የባህል ማዕከል ባለቤት ሎሬት መላኩ በላይ ከተናገረዉ የተወሰደ ነዉ። አርቲስ መላኩ በላይ ፤ ከጎዳና ሕይወት በመነሳት ከታዳሚዎች በሚያገኛት የሽልማት ገንዘብ ትምህርቱን የተማረ፤ ሕይወቱን የቀየረ መሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲነገር ሲዘገብ ቆይቷል። ታዋቂዉ የባህል ተወዛዋዥ መላኩ በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ የጀመረባትን የፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት፤ ከስምንት ዓመታት በፊት ገዝቶ ወደ ባህል ማዕከልነት ማሻገር የቻለ ወጣት ነው፡፡ ይሁንና ሰሞኑን የኪነ-ጥበብ ባለሞያዉ መላኩ በላይ ያቋቋመዉ ይህ የባህል ማዕከል፤ ለልማት በሚል ከመንግሥት የመፍረስ ትዕዛዝ እንደወጣበት ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ብሎም የኢትዮጵያ አንዱ ድምቀት የሆነዉ ፈንዲቃ የባህል ማዕከል የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሁሉ የጋራ ባህል፤ እውቀት፣ ታሪክና የአብሮነት መገለጫዎች በሙዚቃ፣ በባህላዊ ውዝዋዜ፣ በሥነ-ሥዕል፣ በሥነ-ጽሑፍ እና በተያዩ ኪነ-ጥባባዊ ክንዋኔዎች የሚያስተዋውቅ፤ የበርካታ አገራት ቱሪስቶች መዳራሻ እና የአገር በጎ ገጽ ግንባታ ማዕከል፣ እንዲሁም የወጣቶች የዕውቀት ማበልፀጊያና የልምድ መለዋወጫ ማዕከል፤ በመሆኑ በሃገር ዉስጥብ ብሎም በተቀረዉ ዓለም ይታወቃል። ፈንድቃ ይፍረስ መባሉን ሰምተን ለፈንድቃ ባለቤት ሎሬት መላኩ ስልክ ደዉለን በጠየቅነዉ ጊዜ፤ ፈንድቃ ባህል ማዕከል የህዝብ ነዉ ሲል ነዉ የተናገረዉ።
« አሁን ያለዉ ነገር ገሃድ የወጣ እና፤ እኔን የሚያሸማቅቅ ምንም ነገር የለም። ፈንድቃ ከእኔ አልፎ የህዝብ እንደሆነ፤በተፈጠረዉ ሁኔታ መስክሯል። ሁሉም ኢትዮጵያዉያን፤ ሁሉም አለም አቀፍ ዲፕሎማቶች፤ ናቸዉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ስለፈንድቃ እየመሰከሩ ያሉት።»
ሎሬት መላኩ እስቲ የተፈጠረዉን ነገር አጫዉተን ?
«ፈንድቃ የተፈጠረዉ ነገር፤ ስገዛዉ በሊዝ ነዉ። ሊዝ ማለት፤ 90 ዓመት ኮንትራት ከመንግስት ጋር መያዝ ነዉ። የ 30 ዓመት ክፍያ ነበረዉ ፤ አስቀድሜ ከፍዬ የሰርተፍኬት ሽልማት ተከፍያለሁ።»
አንድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ በጻፉት አስተያየት፤
«ዋናው ቁም ነገር፤ ፈንድቃ የሚለው ሃሳብ በዓለም የትም ቦታ መልሶ መቁዋቁዋም በሚያስችለው ደረጃ የታማኝነት እዉቅና አግኝቷል ፤ ፈጥሩዋል። ይህ በታላቅ ጥረት የሆነ ነገር ነው። የሚያሳዝነው: ካዛንቺስ "አዝማሪ ቤቶች" የኢትዬጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሲሆኑ፤ ፈንዲቃ ብቸኛው የዛ ታሪክ አስተዋሽ ባለታሪክ በመሆኑ በማትረፍ ፈንታ ለማፍረስ መቸኮሉ ነው። ይህ የማገናዘብ ጉድለት መኖሩን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምልክት ነው፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። በኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች የባህል ድልድይ የሆነዉ ፈንድቃ መነሳት ክስረት ፤ ሃገርን የሚጎዳ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። አርቲስት መላኩ በላይ ወደሚያስተዳድረዉ የባህል ማዕከል በየዓመቱ ወደ 200,000 ጎብኚዎች ይመጣሉ። አርቲስ መላኩ በጣሊያን ስታር 2022፣ በቲኤዲ ህብረት 2022፣ በፕሪንስ ክላውስ ሎሬት 2020፣ ለሙዚቃ ቪዛ 2019 እና በፈረንሣይ ሜዳሊያ 2015 ተሸልሟል። አዲስ አበባ ልማት እንደሚያስፈልጋት በመረዳት በፈንድቃ ደመቅ ያለ ኢትዮጵያዊ ባህል እየተጋራን አካባቢውን ለማልማት የቢዝነስና የሕንፃ ፕላን አዘጋጅተናል። ዕቅዱ አሁን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፀድቋል ሲል አርቲስት መላኩ ተናግሯል።
የጃዛምባ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መስራች፣ እና እዉቁ የጃዝ ጊታር ተጫዋች ሄኖክ ተመስገን፤ ፈንድቃ ይፈርሳል የሚለዉን ጉዳይ ሰምቶ በጥልቅ ማዘኑን ተናግሯል። “ፌንዲካ ለእኔ ትልቅ ትርጉም ያለዉ ማዕከል ነዉ፤ የመፍረሱ ዜና በእውነት አሳዛን ነው“
ሄኖክ የዓለም አቀፍ የሙዚቃ ባንዶች በፈንዲቃ ትዕይንት ለማየትም ሆነ ለመሳተፍ ቅድሚያ እንደሚሰጡ እና ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን እውቅና እና ዝና አጉልቶ አሳይቷል። ፈንድቃ ለባህል እና ኪነ-ጥበብ አድናቂዎች እና ብሎም ለጎብኝዎች ዋነኛ ማዕከል መሆኑን፤ ለከተማዋ ብሎም ለሃገሪቱ የጥበብ ገጽታ አስተዋፅዖ ማድረጉንም አክሏል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ