«ፈጣሪ አንተን በአካል ሳያሳየኝ እንዳይቀር እጸልያለሁ አልኩት»
ዓርብ፣ መጋቢት 2 2014ኢብራሂም ሙሐመድ፤ ዛሬ የ 23 ዓመት ወጣት ነው። ተወልዶ ያደገው ምስራቅ ወለጋ ውስጥ ሲሆን፤ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው ወሎ ዩንቨርስቲ ነው። ወጣቱ የ5ኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሳለ ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል። ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የገባበት ነው። የትምህርት ተቋሙ እሱን እና ሌሎች ተማሪዎችን እስከ አዲስ አበባ ድረስ ይሸኛል። ኢብራሂም ግን ወደ ወለጋ ቀጥሎ መጓዝ ባለመቻሉ እና አዲስ አበባ ውስጥ መቆያ ስላልነበረው የዛኑ ዕለት ወደ ኮምቦልቻ ይመለሳል። « ግቢ ገባሁ እና የዩንቨርስቲውን ዲን አገኘኃቸው እና ይሔንን ጉዳይ ሳወያያቸው ምንም ልንረዳህ አንችልም አሉኝ።» እሱም ይህንን ብሶቱን ዘርዝሮ ለዶይቸ ቬለ ይጽፋል። መልዕክቱም አየር ላይ ይውላል። « ስፅፍ የሚረዳኝ ሰው አገኛለሁ ብዬ አልነበረም ። ምናልባት የመንግሥት አካል ሰምቶ ዩንቨርስቲው በራሱ ወጭ ወደ ቤተሰቦቼ የምሄድበትን መንገድ ያመቻችልኛል በሚል ነበር። » ኢብራሂም መልሶ ለዶይቸ ቬለ እስኪጽፍ ሁለት ዓመታት ገደማ ተቆጥረዋል። እሱም፤ ያለፈውን እያስታወሰ የሆነውን ገለፀልን። «ነገሮች ተገጣጠሙና እኔ የጻፍኳት ጽሑፍ በእናንተ ዝግጅት አማካኝነት አሜሪካን የሚኖር አንድ ሰው ጆሮ ገባች» እሱም «አይዞህ ባለህበት ተረጋጋ ታሪክህን ሰምቻለው አካወንትህን ላክልኝ» አለኝ። እየቀለደብኝ ቢመስለኝም «እስኪ ጉዱን ልየው ብዬ ላኩለት» ሲል ኢብራሂም ይቀጥላል። « ጭንቀቴን እስኪያስረሳኝ ድረስ ነበር የተደሰትኩት»።
ኢብራሂም ያገኘውን ገንዘብ ተጠቅሞ ወደ ቤተሰቦቹ መሄድ የሚችልበት የትራንስፖርት መንገድ ሲመቻች ከቤተሰቦቹ ጋር ይገናኛል። «ለቅፅበት እንኳ ዐይቸውም ዐይቶኝም የማያውቅ ሰው ውለታ በዚህ አላበቃም» የሚለው ኢብራሂም ይልቁንስ ይህ ሰው እስክመረቅ ድረስ እንደሚረዳኝ እና ከተመረቅሁ በኋላም ሥራ እንደሚያስጀምረኝ ቃል ገባልኝ» ይላል። « ይሔ ሁሉ ሲሆን በአካል አንተዋወቅም ነበር። እና ፈጣሪ አንተን በአካል ሳያሳየኝ እንዳይቀር እጸልያለሁ አልኩት» የኢብራሂምም ምኞት ይሳካል። ትምህርቱንም ይቀጥላል። ኮሮና ባይገባ ኖሮ ኢብራሂም ሊመረቅ ሶስት ወር ገደማ ነበር የቀረው።
የኢብራሂም የክፉ ቀን ደራሽ ጆኒ አባተ ይባላል። ኢብራሂምን ለመርዳት የወሰነበትን ምክንያት እና አጋጣሚ ሲያስታውስ ደስ እያለው ነው። « በኮቪድ ምክንያት ከቤት መውጣት አልቻልንም እና ዶይቸ ቬለን እያዳመጥን ነበር። እና ታሪኩን ስሰማ በጣም ተሰማኝ።» እና ራሴን በእሱ ቦታ አድርጌ አሰብኩ ያኔም ቢያንስ ትንሽ ነገር ላድርግ ብዬ ወሰንኩ። ይላል ጆኒ። እሱም ድጋፉን ሳያቋርጥ የእህቱ ድርጅት ውስጥ ኢብራሂምን ተመርቆ ሲጨርስ አስቀጠረው። «ጥሩ ነገር በማድረግ ጥሩ ነገር ይገኛል የሚለው» ጆኒ ኢብራሂም በጣም ታማኝ ሰራተኛ ሆኖ እንዳገኘው ይናገራል።
አሁን በመካኒክነት ተቀጥሮ እየሠራ የሚገኘው ኢብራሂም ውለታ ዋሉልኝ ያላቸውን የዶይቸ ቬለ ጣቢያን እና ድጋፍ አድራጊው ጆኒን ለማመስገን ወደ ዶይቸ ቬለ ሲጽፍም ሌሎች ወጣቶች «ከእኔ ታሪክ ሊማሩ የሚችሉት ነገር አለ» ይላል። ይህም ትዕግስት እና ተስፋ አለመቁረጥን ነው። ኢብራሂም ሌሎችን ተስፋ እንዳይቆርጡ ሲመክር እሱም በትግስት ወለጋ የሚገኙ ወላጆቹን ለማግኘት እየጠበቀ ነው። በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከዩንቨርስቲ ተመርቆ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ወደ ትውልድ ቦታው አልተመለሰም።
ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ