ፋጢማ አል-ፊህሪ
ሐሙስ፣ ግንቦት 6 2012
ፋጢማ አል ፊህሪ ማን ነበሩ?
ፋጢማ አል ፊህሪ የተወለዱት እጎአ በ 800 ኛው ዓ ም ነበር። እሳቸውም መሐመድ ብናዎ አብዱላህ አል-ፊህሪ የተባሉ ሀብታም ነጋዴ ሴት ልጅ ናቸው። ቤተሰባቸው በኢድሪስ 2ኛው ዘመን ወደ ፌዝ ከተማ ተሰዶ ይኖሩ ነበር። ለታሪክ ምሁራን እንኳን ሳይቀር የፋጢማ ታሪክ አሁን ድረስ ብዙ እንቆይልሽ የሆኑ ነገሮች አሉት። ከእነዚህ አንዱ ፋጢማ የሞቱበት ዓመት ነው። ይህም 878 አካባቢ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታመናል።
በህይወት ዘመናቸው ፋጢማ «የወንዶች ልጆች እናት» ተብለው ይጠሩ ነበር። እንደ ታሪክ ምሁር መሀመድ ያሲር ሂላሪ ከሆነ ይህ ቅፅል ስም የወጣላቸው ለበጎ አድራጎት ስራቸው እና በርካታ ተማሪዎችን ይረዱ ስለነበር ነው።
ፋጢማ አል-ፊህሪ መስጊድ ለመገንባት ለምን ወሰኑ?
ፋጢማ ጠንካራ አማኝ ነበሩ። አባታቸው እና ባለቤታቸው ሲሞቱ በፌዝ የሚኖረው ሙስሊም ማህበረሰብ እጅግ በአፋጣኝ የሚያስፈልገውን መስጊድ ስለነበር ይህን ለማስገንባት ወስነዋል። ይህም የሰው ቁጥር በፍጥነት በመጨመሩ እና በቂ የአምልኮ ቦታ ባለመኖሩ ነው። ፋጢማም «ከሀዋራ» ጎሳ መሬቱን ከገዙ በኋላ የመስጊዱ ግንባታ በረመዳን ወር በ 254 ሄጊራ ማለትም እጎአ 859 ጀምረዋል።
ከ 10 ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ዝነኛው የአል ቃራዊይን መስጊድ የመጀመሪያው ኃይማኖታዊ ተቋም እንዲሁም በሰሜን አፍሪቃ ትልቁ የአረብ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይጠራል። በርካታ ተማሪዎችን ወደዚህ አካባቢ በመሳብም ታዋቂ የሳይንስ ሊቃውንት አድርጓል።
በዚህም ስፍራ በርካታ ሲምፖዚየሞች እና ውይይቶች ይካሄዱ ነበር። የተገኙ ሰነዶች እንደሚያመላክቱት የማስተማሪያ ወንበሮች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እና በመላው ፌዝ ውስጥ ይገኙ ነበር። እነዚህ ተመሳሳይ መዝገቦችም እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ቤተ-መጻሕፍት በፌዝ እንደነበሩ ይጠቅሳሉ።
የአል ቃራዊያን ዩንቨርስቲ ለምንድን ነው እንዲህ ዝነኛ የሆነው ?
የአል-ቃራዊይን ዩኒቨርስቲ ቀደምት ከሚባሉት የአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ሁሉ የነበረ እና አሁንም በስራ ላይ የሚገኝ ከዓለም እጅግ በጣም ጥንታዊው ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ዩኔስኮ እና ጂኒየስ ወርልድ ሪኮርድ ይጠቁማሉ። ይህንን አመላካች ቀን ሆኖ የተቀመጠውም የአል ቃራዊይን መስጊድ ሆኖ የተመሰረተበት ዓመት ነው። በዚህ ረገድ በቲምቡክቱ ከተመሠረተው የሳንኮራ መስጊድ በአንድ ምዕተ ዓመት (እጎአ 989 ) እና ከቦሎግና ዮንቨርስቲ ደግሞ (እጎአ 1088) ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የተመሰረተ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
ከተመራቂዎቹ ተማሪዎች መካከል በርካታ ባለቅኔዎችን ፣ የሙስሊም የሕግ ባለሙያዎች ፣ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎችን እና የሂሳብ ምሁራን ይገኙበታል። ታዋቂ ከሚባሉት እነዚህ ምሁራን መካከል የታሪክ ምሁር የሆኑት አብዱራህማን ኢብን ካሊዱን ፣ ሐኪሙ እና ፈላስፋው አቡ ዋሊድ ኢብን ሩሺድ፣ የአንዳሉዚያኑ ዶክተር ሙሳ ኢብን ማሞናው እና የሲሊቬስተር 2ኛው ጳጳስ የሆኑት ግሬበርት አውሪላክ ይገኙበታል።
ፋጢማ አል ፊህሪ እንዴት ይታወሳሉ ?
ፋጢማ አል ፊህሪ በተለይ በፌዝ አማኞች ዘንድ እጅግ የተከበሩ እና እንደ ቅዱስ የሚቆሰሩ ሰው ናቸው። እሳቸውንም ለማስታወስ ሲባል እኢአ በ 2017 ቲኒዚያ ውስጥ የክብር ሽልማት በስማቸው ተሰይሟል። ይህም ሽልማት ሴቶችን ለሚያሰለጥኑ እና ለሚያበረታቱ ይበረከታል። ከዚህ በተጨማሪም ለአውሮፓ እና ሰሜን አፍሪቃ ላሉ ተማሪዎች የሚሰጠው ነፃ የትምህርት የስልጠና መርሃግብር ፋጢማ አል-ፊህሪን ያስታውሳል።
ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።