ፍርድ ቤቱ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔን ሻረ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2017
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ሻረ ፡፡ ፍርድ ቤቱ የመሻሪያ ውሳኔውን ያሳለፈው ምርጫ ቦርድ በከሳሽ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ከሥልጣን ገደቡ ውጪ የሆነ ፣ ህጉን እና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የሚጻረር ሆኖ በመገኘቱ ነው ብሏል ፡፡
ፍርድ ቤቱ በመዝገብ ቁጥር 315888 ለተከራካሪ ወገኖች በሰጠው የፍርድ ውሳኔ ላይ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በተራ ቁጥር 1 ተከሳሽነት ተጠቅሷል ፡፡ ቦርዱ የኢፌዴሪን ህገ መንግሥት ፣ የአገሪቱን ህጎች እና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ በመጣስ ጣልቃ ገብ ውሳኔዎችን አሳልፏል በሚል አቤቱታ እንደቀረበበት በፍርድ ቤቱ የውሳኔ መዝገብ ላይ ተጠቅሷል ፡፡
እንዲሁም ከቁጥር 2 እስከ 4 ያሉት ተከሳሾች አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ ፣ አቶ ቦርሳሞ ቦሮጄ እና አቶ ማቴዎስ ካነ ከፓርቲው በሥነ ምግባር ጉድለት ተባረው እያለ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን የፓርቲውን ቢሮ እና ንብረት በሐይል ሥለመያዛቸው አቤቱታ መቅረቡ በውሳኔ ሀሳቡ ተመልክቷል ፡፡
የቦርዱ ውሳኔ የተሻረበት ምክንያት
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 21፣ የካቲት 28 እና መጋቢት 17 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከሳሽ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ በሥም በተጠቀሱት አባላቱ ላይ ያሳለፈውን የሥነ ሥረዓት ቅጣት መሻሩ ከሥልጣን ገደቡ ወጭ የተከናወነ ነው ሲል ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አመልክቷል ፡፡ በመሆኑም ቦርዱ የሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ቁጥር11/ አንቀጽ 12 ንዑስ ቁጥር 1 መሠረት ውሳኔው የተሻረ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል ፡፡
የሁለቱ ወገኖች አስተያየት በውሳኔው ላይ
ዶቼ ቬለ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስመልከቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ያም ሆኖ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት በአንደኛው የፓርቲ ወገን ውስጥ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ገነነ ሀሰና ውሳኔውን “ ተገቢ “ ብለውታል ፡፡ “ መጀመሪያም ህጉን ተከትለን ነው የሄድነው ምርጫ ቦርድም ጣልቃ እንዳይገባብን በተደጋጋሚ ሰንጠይቅ ነበር “ ያሉት አቶ ገነነ “ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ክስ ለመሄድ ተገደናል ፡፡ ውሳኔውም ተገቢ እና የጠበቅነው ነው ፡፡ በቀጣይ ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ያደርጋል ብለን እንጠብቃለን “ ብለዋል ፡፡
በውሳኔው በተራ ቁጥር 2 የተጠቀሱትና በሌላኛው ወገን የሚገኙት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጴጥሮስ ዱቢሶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የቀረቡ ማስረጃዎችን ከግምት ያላስገባ ነው ይላሉ ፡፡ ውሳኔ የተባለው ነገር ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ ሳይሆን ፓርቲዎችን ከመቆጣጠር እስከ መሰረዝ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጴጥሮስ “ ፍርድ ቤቱ የህግ ጥሰት ካለ ሊያይ ይችላል ፡፡ ነገር ግን በዚህ ልክ መዝኖ ከውሳኔ ላይ ደርሷል ብለን አናምንም ፡፡ በእኛ በኩል ውሳኔውን በመቃወም ለሚቀጥለው የፍትህ አካል ይግባኝ እንላለን “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ