1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

«የተጻፈ ይወረሳል፤ የተነገረ ይረሳል እንደሚባለው መጽሐፌ እንዲጽፉ ያበረታታል»

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥቅምት 1 2017

የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን ስለ ግል ታሪካቸው እና ተሞክሮዋቸው መጽሐፍ የጻፉ አንድ ኢትዮጵያዊ መምህር ናቸው። እኝህም ሰው ዋና አላማቸው ወጣቶች ታሪካቸውን እንዲጽፉና መጽሐፍ እንዲያነቡ ማበረታታት እንደሆነ ነግረውናል። በተለያዩ ሃገራት የትምህርት እድል አግኝተው ስለተማሩም ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን ምክሮች ለወጣቶች በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።

አቶ ፍቃዱ ረታ
አቶ ፍቃዱ ረታ ምስል privat

«መፅሀፍ ስንፅፍ የልጅ ልጆቻችንን እያሰብን እንፃፍ»

This browser does not support the audio element.

እንግዳችን አቶ ፍቃዱ ረታ ይባላሉ። ከ 10 ዓመት በላይ በመምህርነት በሐዋሳ ዩንቨርሲቲ ስላገለገሉ፤ «ከመፅሀፍ ፀሀፊ ወይም ደራሲ ይልቅ መምህር እና ተማሪ የሚለው ይበልጥ ይገልፀኛል» ይላሉ። «ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከዩንቨርሲቲ ተመርቀው ስራ የማያገኙ ወጣቶች ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳዬ ነው» ያሉን አቶ ፍቃዱ የቅርብ ጊዜውን « My African Dream» የተሰኘውን መፀሀፋቸውን ጨምሮ እስካሁን አራት መፅሀፎች ፅፈዋል። «ሙያዬ ማስተማር ነው። የፃፍኩትም ፁሁፍ ለተማሪዎቼ ነው። ሌሎች ሰዎች እንደሚፅፉት አይነት ድርሰቶች ወይም ትልልቅ መፅሀፍት፤ ሙያዊ ሂደቱን ተከትሎ የተፃፈ ወይም በጣም ብዙ ጊዜ ወስጄ የፃፍኩት ሳይሆን የምመኘውን እና እንዲያዳምጡኝ የምፈልገውን ነገር ነው የፃፍኩት።»

በአሁኑ ሰዓት በዩናይትድ ስቴትስ University of Nebraska–Lincoln የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት መምህር ፍቃዱ ዴንማርክ እና ቤልጄምም የትምህርት እድል አግኝተው ተምረዋል።  ህይወት ግን ለአቶ ፍቃዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ሁሉ ነገር የጀመረው ከ43 ዓመታት ገደማ በፊት በተወለዱበት የቀድሞ አርሲ ዞን ሴሩ ወረዳ ነው። መፅሀፋቸው ከልጅነት ጊዜያቸው አንስቶ ያሳለፉትን ህይወት ስለሚያወጋ አንባቢያን በራሳቸው ተስፋ እንዳይቆርጡ ያበረታታል የሚል እምነት አላቸው ።«ምክንያቱም ብዙ የሚያሰናክላቸው፤ ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ነገር ይበዛል። የእኔን መፅሀፍ ሲያነቡ ምን ያህል እንደተቸገርኩ የሚያሳዩ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ድህነት። ከባድ ድህነት አሳልፌያለሁ። ከዩንቨርስቲ ስወጣ ብዙ ተቸግሬያለሁ። እንደዚሁም ከኢትዮጵያ ስወጣ ዴንማርክ ሀገር ብዙ ተስፋ አድርጌ ሄጄ ብዙ የተፈተንኩበት እና ያዘንኩበት ተሞክሮ ገጥሞኛል። እና ተጨባጭ የሆነ እቅድ እንዲያቅዱ፣ የነገን ሲያስቡ በደንብ አስተውለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ሀሳብ ተካቶበታል። ከሁሉም ነገር በላይ ደግሞ ታሪካቸውን እንዲፅፉ መፅሀፉ ይጠይቃቸዋል።»   
አሁን ያሉበት «አሜሪካን ጨምሮ የሰዎች መፀሀፍ የማንበብ ልምድ  ቀንሷል» ይላሉ አቶ ፍቃዱ። ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ «የማንበብ ልምዱ እና ከተፃፉ ነገሮች መረጃ መውሰድ ልምዳችን አልነበረም» የሚሉት መምህር ፍቃዱ አጫጭር ቪዲዮዎችን መመልከት ላይ ከማተኮር ይልቅ ወጣቱ የራሱን ታሪክ መፃፍ እንዲጀምር ያበረታታሉ።
«ለምሳሌ የእኔን ቤተሰብ ታሪክ እኔ ካልፃፍኩ ሌላ ሰው ላይፅፍ ይችላል። የእኔን የግል ህይወቴን ፤ ያሳለፍኩትን ውጣ ውረዴን፤ ጥሩ ነገሬን ለትውልድ በሚጠቅም መልኩ  እኔ ካልፃፍኩት ማን ይፅፈዋል። እና ወጣቱ በዛ መልክ ቢያየው፤ በአካባቢያቸው የሚያዩዋቸው ዛሬ ቀላል የሚመስሉ የዛሬ 20 እና 100 ዓመት ግን የሚረሱ ታሪኮች አሉ። የተፃፈ ይወረሳል፤ የተነገረ ይረሳል እንደሚባለው መፅሀፌ በደንብ እንዲያስቡ ይጠይቃቸዋል። ጫማ መጥረግ የጀመርኩት አራተኛ ክፍል ሆኜ ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ሊስትሮ ነበርኩ። ስለገንዘብ፤ ሰርቶ ማግኘት ራስን ማገዝ ፤ ሴቪንግ የሚለውን በኋላ ካምፓስ ገብተን የምንማረውን ህይወት አስተምራኝ አይቼዋለሁ።  »

«መፅሀፍ ስንፅፍ የልጅ ልጆቻችንን እያሰብን እንፃፍ»

 መምህር ፍቃዱ እንዲፅፉ የሚያበረታቷቸውን አንባቢያን ስሜታዊ ሆነው እና ሌላውን ሰው በማያስቀይም ሁኔታ ቢፅፉ ሲሉ ያሳስባሉ።  ወጣቶች ቢያነቡ የሚሏቸው የትምህርት እድል ቁጥር 2 እና « My African Dream»  የሚሉት መፀሀፎቶቻቸውን ናቸው። « የመጀመሪያዎቹ ሶስት መፅሀፍት በነፃ የሚሰጡ ናቸው። አንዳንዴ ግን ሰዎች ነፃ ሲሰጣቸው ክብደት አይሰጡትም። የተከፈለበት ማኪያቶ እና በነፃ የሚሰጥ እኩል አይጠጣም ይላሉ የኢኮኖሚ ሰዎች ። አማርኛውን የትም ቦታ ያገኛሉ። ከእኔ የሊንክድኢን እና ዩቲውብ ገፅ ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ።  ይኼኛው (My African Dream )ደግሞ እንዲታተም እፈልጋለሁ። »
ስሙም እንደሚጠቁመው My African Dream አቶ ፍቃዱ በእንግሊዘኛ የፃፉት መፅሀፍ ነው። አማዞን ላይ ይሸጣል።  መግዛት የማይችሉ ግን ከጠየቋቸው በነፃ ለመስጠት ፍቃደኛ ናቸው። ከአማዞን በሚሰበሰው ገንዘብ ታትሞ ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ እንዲደርስ እና በቀላሉ መፅሀፍ የማያገኙ ሰዎች ጋር ቢደርስ ምኞታቸው ነው።  

የአቶ ፍቃዱ ረታ አራተኛ መፅሀፍ

ሰዎች በእንግሊዘኛ ከተፃፈው መፀሀፍ ምን ሊጠብቁ ይችላሉ? 

«ለየት የሚያደርገው ይኼኛው። በእኔ ደረጃ ያሉትን በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎች ቢያነቡት የሆነ የሚጠይቃቸው ጥያቄ አለ። ይኼ መፀሀፍ ኢትዮጵያን በደንብ ይዳስሳል። ቴክኖሎጂዎችን በደንብ እንድንጠቀም ኢትዮጵያን ምሳሌ አድርጌ ፅፌያለሁ። በቀጥታ ወጣቱ ማሰብ ያለበትን ነገር ፅፌያለሁ። …ሲያነቡት ያገኙታል። በአንድ ቃል አንድን መፅሀፍ መግለፅ በጣም ከባድ ነው። እንደ አዕምሮዋቸው እድገት ምን ለማለት እንደፈለኩ ይገባቸዋል።»
አቶ ፍቃዱ በመፀሀፋቸው ስላዩዋቸው ዘጠኝ ሀገራት ጥሩ እና መጥፎ ተሞክሮዎች፤ስለ የውጭ  የትምህርት እድል እና ሌሎች ወጣቱን ይጠቅማል ስላሉት ነገሮች ፅፈዋል።  የአመራርነት ወይም leadership ጥናት ተማሪ የሆኑት አቶ ፍቃዱ በዚህም በእንግሊዘኛ የፃፉት መፀሀፍ ላይ ወጣቱን ራሱን ከፖለቲካ ውይይቶች እንዲያርቅ እና ይልቁንም የግል ግብ ላይ እንዲያተኩር ይመክራሉ? ፤ለምን? «ፖለቲካ ነክ ነገር ብዙ ሰውን ይከፋፍላል። ማንንም ሲያቀራርብ አላይም። ለማለት የፈለኩት ፖለቲካ ውስብስብ ነው። ኢትዮጵያ ብለን ስለኢትዮጵያ ብቻ የምናስበው አይደለም። ለእኔ ለምሳሌ ፖለቲካ የነፃነት እና የዲሞክራሲ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ለሌላው ወንድሜ ደግሞ ወንድሙን ፣ አካሉን ወይም ዘመዶቹን አጥቶበታል። እና ዝምብለን የምንነካካው ጉዳይ አይደለም። ለዚህ ነው ቶሎ አጀንዳቸው እንዳያደርኩ ወጣቶችን የምመክረው።»

የመፃፍ ጀማሪዎች

ይኼ መፀሀፍ ለንባብ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ 89 ሰዎች በጋራ የሚፅፉበት  የመፃፍ ጀማሪዎች ክበብ ጀምረናል የሚሉት መምህር ፍቃዱ አምስተኛ መፅሀፋቸውን መፃፍ ጀምረዋል። የፀሀፊዎች ክበብ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሰዎች በሳምንት እስከ ሶስት ገፆች እየፃፉ በ10 ወራት ውስጥ ለመጨረስ አብረን እየፃፍን ነው ይላሉ መምህሩ።  ስለ የፀሀፊዎቹ ክበብ ይበልጥ ያብራራሉ። «በ YessEthiopia የበጎ አድራጎ ስራ ስለምንሰራ በጎ አድራጎት ክበብ ውስጥ የመፃፍ ጀማሪዎች ክበብ ጀምረናል። በየሳምንቱ በፈለጉት ጉዳይ ላይ ይፅፋሉ። አንዳንዱ ስለአያቱ፣ ሌላው ስላስተማሩ መምህር ይፅፋል። ሌላው ስለ ራሱ የትምህርት ተሞክሮ፤ ሌላው ስለ ነፃ የትምህርት እድል እና የወጣ የወረደበት ይፅፋል።  መፀሀፍ ስናነብ  ቃላት እንማራለን፣ የታሪክ አገላለፅ እና የተለያዩ ነገሮች እንማራለን።» ይላሉ ስለ ግል ታሪካቸው እና ተሞክሮዋቸው መፅሀፍ የፃፉት እና ወጣቶች ስለ ታሪካቸ እንዲጽፉ እና መፀሀፍ እንዲያነቡ የሚያበረታቱት መምህር ፍቃዱ ረታ።

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW