1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ፍትህ እንዲረጋገጥ እሻለሁ” የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት

ሰኞ፣ ሰኔ 24 2016

የአርቲስቱ አራተኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ እና በአርቲስቱ ስም በተመሰረተው ሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን አዘጋጅነት ለሦስተኛ ጊዜ በተሰናዳው መድረክ የአርቲስቱ ባለቤት ወ/ሮ ፋንቱ ደምሰው የሃጫሉ አገዳደል እውነታ እንዲወጣ ጠየቁ፡፡ ወ/ሮ ፋንቱ “አርቲስቱ የተገደለው ለፖለቲካ እቅድ ማስፈጸሚያ” መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“ፍትህ እንዲረጋገጥ እሻለሁ” የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት
“ፍትህ እንዲረጋገጥ እሻለሁ” የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤትምስል Seyoum Getu/DW

“ፍትህ እንዲረጋገጥ እሻለሁ” የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት

This browser does not support the audio element.

“ፍትህ እንዲረጋገጥ እሻለሁ” የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት

አርስትስ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ድፍን አራት ኣመታትን ያታቆጠረ ቢኆንም የአርቲስቱ ፍትህ እስካሁንም ሰፍኗል ብለው እንደማያምኑ ቤተሰቦቹ አስታወቁ፡፡

የአርቲስቱ አራተኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ እና በአርቲስቱ ስም በተመሰረተው ሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን አዘጋጅነት ለሶስተኛ ጊዜ በተሰናዳው መድረክ የአርቲስቱ ባለቤት ወ/ሮ ፋንቱ ደምሰው የሃጫሉ አገዳደል እውነታ እንዲወጣ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተጋብተዋል፡፡

የአርትስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ፍትህ እስካሁንም ተረጋግጧል ብለው እንደማያምኑ ቅዳሜ ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው አርቲስቱ የተገደለበት 4ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ እና በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው የሃጫሉ ሽልማት መርሃግብር ላይ አጉልተው የተናገሩት የአርቲስቱ ባለቤት ወ/ሮ ፋንቱ ደምሰው፤ አሁንም ድረስ ትልቁ መሻታቸው የግድያው እውነታ ክምንጩ እንዲመረመር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት እና በአርቲስቱ ስም የተመሰረተውን ፋውንዴሽን በበላይ ኃላፊነት ያቋቋሙትና የሚመሩት ወ/ሮ ፋንቱ በቅዳሜው ምሽቱ ንግግራቸው “አርቲስቱ የተገደለው ለፖለቲካ እቅድ ማስፈጸሚያ” መሆኑን የጠቆሙበት ንግግር ነው ያደረጉት፡፡

የአርትስት ሃጫሉ ባለቤት ጥያቄ

“በዚህም ህዝብን ተስፋ እናስቆርጣለን ያሉ በራሳቸው ተስፋ ቆርጠው ሃጫሉን በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ አኖሩት” በማለትም የአርቲስቱን አይሬሰነት በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር  አንስተዋል፡፡ “እውነት ተደብቋል” ያሉት ወ/ሮ ፋንቱ የአርቲስቱ ፍትህ እስኪረጋገጥ መናገርና መጠየቅ እንደማያቆሙም አስረድተዋል፡፡ “የምታውቁት እያላችሁ ምንም እንደማያውቁ አትሁኑ” በማለትም እስካሁን የአርቲስቱ እውነተኛ ፍትህ ተረጋግጧል ብለው የማያምኑ መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የሃጫሉ ሁንዴሳ 4 ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ እና በአርቲስቱ ስም የተመሰረተው ሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን 3 ተኛ መድረክምስል Seyoum Getu/DW

“ለእኔ ማንም ንጹህ አይደለም” ያሉት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለቤት መንግስትም ሆነ ከመንግስት ውጪ ያሉ ያሏቸውየአርቲስቱን እውነተኛ የአገዳደል ምስጢር የሚያውቁ “እውነታው ወጥቶ” ፍትህውም እንዲረጋገጥ ስሞታቸውን አሰምተዋል፡፡ “ገዳይና አስገዳዩን ለህግ አቅርቡልን” በማለትም ማንም በዚህ ንጽህናውን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም የባለቤታቸው አገዳደል እውነታ እንዲወጣና ሀቀኛ ያሉት ፍትህው እንዲረጋገጥ ሁሉም ሰው እንደየሃይማኖቱ እንዲጸልዩ ወ/ሮ ፋንቱ ተማጽነዋል፡፡ ይህንን ንግግራቸውንም ተከትሎ በእለቱ በመርሃግብሩ ላይ የታደሙ አዳራሹ ሙሉ ህዝብ በዝምታ ከተዋጡ በኋላ ትልቅ የሃዘን ድባብና ልቅሶም ተውጠው ታዩ፡፡

ሦስተኛው የሃጫሉ ሽልማት

በቅዳሜውየአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢ እና ሽልማት መርሃ ግብሩ በኦሮሞ አርት ውስጥ በዓመቱ ጉልህ አሻራን ያኖሩ እና በተለያዩ ጊዜያት በአርቱ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች እውቅና አግኝተዋል፡፡የትግል ሙዚቃዎችን ጨምሮ ለዓመታት በአፋን ኦሮሞ በማቀንቀን የምትታወቀው አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የእድሜ ልክ ተሸላሚ ተሰኝተዋል፡፡ በዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ ሱራ ቲ፣ በዓመቱ ምርጥ የባህል ሙዚቃ አርቲስት ታደለ ገመቹ፣ በምርጥ ዘመናዊ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አርቲስት ጉቱ አበራ፣ በዓመቱ “ባለጊዜ” በሚል ነጠላ ዜማው ተወዳጅነትን ያገኘው አርቲስት ዮሳን ጌታሁን የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃ ዘርፍ ኣሸናፊ ሆነዋል፡፡ አርቲስት ገላና ጋሮምሳ የዓመቱ ምርጥ ወንድ አርቲስት ስሰኝ በሴቶች ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አርቲስት የተባለችው ሙዚቀኛ ኤልሳ ንጉሴ ናት፡፡ የቪዲዮና ቅንብር ባለሙያው አመንሲሳ ኢፋ ደግሞ የዓመቱ ምርጥ ዳይሬክተር ተሰኝቷል፡፡ ሽልማቱ ሌሎች ዘርፎችም ጨምሮ ባጠቃላይ በ11 የሙዚቃ ሙያ ዘርፎች ለአሸናፊዎች ተሰጥቷል፡፡

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የሶስት ልጆች አባት ነበር፡፡ ሰኔ 22 ቀን 2012  ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚታወቅ አከባቢ ተገድሎ መገኘቱ ይታወሳል፡፡ በህዝብ ዘንድ እጅግ ጥልቅ ተወዳጅነት የነበረው አርትስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያውን ተከትሎም በማግስቱ በመላው ኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ከፍተኛ አመጽ የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱና እጅግ የበዛ ንብረትም መውደም ይታወሳል፡፡

የሃጫሉ ሁንዴሳ 4 ኛ ዓመት የሙት መታሰቢያ እና በአርቲስቱ ስም የተመሰረተው ሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን 3 ተኛ መድረክምስል Seyoum Getu/DW

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በተለዬ ሁኔታ ለምን ይወደዳል?

በኦሮሞ ጉዳይ ላይ በማተኮር የተለያዩ ጽሁፎችን ያሳተሙ አቶ ማሞ ገዳ ሃጫሉን በተለየ ሁኔታ በህዝብ ዘንድ ያስወደደው ባሉት ጉዳት ላይ ሃሳባቸውን ሲሰጡ፡ “ሃጫሉ ለይቶ የሚወደው ፓርቲ ለውም፡፡ በሃይማኖትም እንዲሁ የሚያስበልጠው የለው፡፡ እሱ የሚወደው ሃቅ ነው፡፡ ሁሉንም ኦሮሞ እኩል መውደዱ ነው፡፡ ከጎጥ ከጎሳ አስበልጦ እውነትና ኦሮሞነትን መውደደው በሁሉም ኦሮሞ ዘንድ የተለየ ቦታ እንዲሰጠው አድርጓል፡፡ ኦሮሞ ስገዳደል ከማየቴ ብሞት ይሻለኛል እንዳለውም አሁን የምንመለከተውን ከማየቱ አስቀድሞ ፈጣሪ ወደራሱ ወስዶታል” ብለዋል፡፡

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ግድያን ተከትሎ በግድያው ተሳተፉ በተባሉት ሶስት ሰዎች ላይም አቃቤህግ ክስ መስርቶ በአንደኛው ተከሳሽ ላይ የእድሜ ልክ እስራት እና በሁለተኛው ላይ ደግሞ የ18 ዓመት ጽኑ እስራት ማስበየኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የአርቲስቱ ቤሰተቦች በዚህ የህግ ሂደቱ ብዙ እምነት እንደሌላቸውና “እውነተኛ ፍትህው” እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉ ደጋግመው ያነሳሉ፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW