1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍትኅ ለተጠማች ኢትዮጵያ መዓዛ አሸናፊ ምን ይዘው ይሆን?

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24 2011

በኢትዮጵያ "የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን" የተሰጠውን የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲመሩ የተመረጡት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የዳኞችን ነፃነት ማረጋገጥን ጨምሮ በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል። ወይዘሮ እሌኒ ገብረ መድኅን ገለልተኛ፣ ግልፅና ፍትኃዊ የሚሏቸው ወይዘሮ መዓዛ ፍርድ ቤቱ ያለበት ኹኔታ ማጥናት ቀዳሚ ሥራቸው እንደሆነ ገልጸዋል

Meaza Ashenafi
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress/C. Niehaus

ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የመጀመሪያዋ ሴት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነዋል

This browser does not support the audio element.

ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የተሾሙበት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ጉዳዮች "የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን" አለው። በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ይኸው ፍርድ ቤት "መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን" ተሰጥቶታል። የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ላይ ይግባኝ የሚያዳምጠውም አሁን ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው። የጥብቅና ባለሙያው አቶ ሰዒድ አብደላ "ፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌድራል ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶችን የሚያስተዳድር ነው። በዚያው ስር የሰበር ችሎት አለ። ይኸ ሰበር በአጠቃላይ በአገሪቱ ሙሉ መሠረታዊ የሕግ ሥሕተት አለባቸው የሚባሉ ጉዳዮችን አይቶ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው" ሲሉ ያስረዳሉ። ወይዘሮ መዓዛ ፕሬዝዳንትነት አቶ ሰለሞን አረዳ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ተቋም የዳኞችን፤ ሥነ-ምግባር የመከታተል፤ መልምሎ ለምክር ቤቱ በማቅረብ የማሾም ሥልጣን ጭምር አለው።  የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት  በአገሪቱ ትልቅ ሥልጣን ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ሰዒድ "የፍትኅ ሥርዓቱን ለማስተካከል ብዙ ኃላፊነት የሚወስድ ተቋም ነው" ሲሉ ይገልጹታል።

የጀርመን ጉብኝታቸውን የመጨረሻ ምዕራፍ አቋርጠው ትናንት ምሽቱን ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ሁለቱን ዕጩዎች ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትኅ እንዲያረጋግጥ የተገነባው ተቋም ፍትኅን በገንዘብ የሚሸጥ፤ ለደሐ እና ለእውነት መቆም ሲገባው ፍትኅ በማጓደል ደሐ የሚያስለቅስ" ሆኗል ሲሉ ወርፈዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ የአገሪቱን ሕግ የመተርጎም ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠውን የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲመሩ የተሾሙት ወይዘሮ መዓዛ እና አቶ ሰለሞን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሕዝብ የሚሰጧቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ቀን ከሌት ተግተው እንደሚሰሩ ተስፋ አድርገዋል።  

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተወልደው ያደጉት የ54 አመቷ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ኃላፊነታቸውን በቅንነት፣ በታታሪነት እና ሕግና ሥርዓትን መሰረት በማድረግ ለመወጣት ቃለ-መሐላ ፈፅመው ከዛሬ ጀምሮ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ "የመጀመሪያ የቢሮ ሥራዬ የፍርድ ቤቱ ኹኔታ ያለበትን ማጥናት ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ወይዘሮዋ በኢትዮጵያ የፍትኅ ሥርዓት ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን ሲቆናጠጡ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው። 

የወይዘሮ መዓዛ ሹመት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ዘንድ አዎንታዊ አቀባበል ገጥሞታል። አይዘሮ መዓዛ ያላቸውን የሥራ ልምድ እና ስኬቶቻቸውን እየጠቀሱ ትክክለኛ ውሳኔ ሲሉ አድናቆታቸውን የገለጹ በርካቶች ናቸው። የአዲስ ስታንዳርድ የድረ-ገፅ መፅሔት አርታዒዋ ጸዳለ ለማ በትዊተር አዲሷ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ የፍትኅ ሥርዓት ዕምነትን ለመገንባት የሚፈልገውን ሁሉ የሚያሟሉ መሆናቸውን ገልጻለች። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራቿ ወይዘሮ እሌኒ ገብረ መድኅን በበኩላቸው ፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት አጭር መልዕክት ገለልተኛ፣ ጠንካራ ተደራዳሪ፣ ግልፅ እና ፍትኃዊ መሆናቸውን ገልጸው ሹመታቸውን አድንቀዋል። የጥብቅና ባለሙያው አቶ ሰዒድ "ወይዘሮ መዓዛ ከነበራቸው እንቅስቃሴ አንፃር በአገሪቱ ውስጥ ለፍትኅ መከበር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ናቸው። የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች እና የሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩ፤ በተለያዩ ቦታዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው። ከዚህ አንፃር ያላቸው ልምድ በአስተዳደሩ በኩል ጥሩ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብዬ አስባለሁ" ሲሉ ይናገራሉ። የጥብቅና ባለሙያው "ወይዘሮ መዓዛ በዳኝነቱ በኩል ፍርድ ቤቶችን በማወቅ በኩል በዛ ቦታ ላይ ብዙ ስላልሰሩ ክፍተት ሊፈጠር ይችላል" ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

 ወይዘሮ መዓዛ ማን ናቸው?

ምስል Federal Government Communication Affairs Office of Ethiopia

ወይዘሮ መዓዛ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች እና የመጀመሪያዋ ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ማኅበሩ የኢትዮጵያ ሕግጋት ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በመወትወት፣ አነስተኛ ገቢ ላላቸው እንስቶች ሕጋዊ ድጋፍ በማቅረብ እና ሴቶችን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ብሔራዊ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆኑ ባደረጋቸው ጥረቶች ተለይቶ ይታወቃል።

የቀድሞዋ ጠበቃ በምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ-ሐብታዊ እና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚሰራውን ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በኃላፊነት መርተዋል። የአፍሪቃ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ከፍተኛ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል። በሙያቸው በኢትዮጵያ የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪቃ የጾታ እና ማኅበራዊ ልማት ማዕከል ውስጥ ተሳትፎ አድርገዋል።

ከሕግ ሙያቸው ባሻገር ሴት ሥራ ፈጣሪዎች እና ባለሙያዎችን አሰባስበው የመጀመሪያውን የሴቶች ባንክ እንዲቋቋም አድርገዋል። እናት የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይኸው ባንክ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚያገኙትን የፋይናንስ አገልግሎት የማሳደግ ሕልም አለው። ወይዘሮ መዓዛ የእናት ባንክ የቦርድ ሊቀ-መንበር ሆነው አገልግለዋል።

ጠበቃ ሰዒድ አብደላ እንደሚሉት የዳኞችን ነፃነት ማስጠበቅ፣ የዜጎችን የፍትኅ ፍላጎት ማሟላትን የመሳሰሉ በርካታ የቤት ሥራዎች ይጠብቋቸዋል። "በዚህ ስልጣናቸው ዳኛ ነፃ ሆኖ እንዲሰራ መሥራት አለባቸው። አስፈፃሚው አካል በጣም ጣልቃ የሚገባበት ኹኔታ ነበረ" የሚሉት ጠበቃ ሰዒድ ወይዘሮ መዓዛ በዜጎች ዘንድ አለ የሚሉትን "የፍትኅ ጥማት" ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል። "በአሁን ሰዓት መዝገቦች እጅግ በጣም ይዘገያሉ። አንድ ጉዳይ ፍርድ ቤት ሔዶ ለመወሰን በጣም ረዥም ጊዜ ይወስዳል። ዳኞች ቁጥራቸው እንዲጨምር እንዲሁም ደግሞ መዝገቦችን በፍጥነት እየሰሩ ውሳኔ እንዲያገኙ" ማድረግ አለባቸው ሲሉ ጠበቃ ሰዒድ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ ወይዘሮ መዓዛ ያሉባቸውን በርከት ያሉ የቤት ሥራዎች ያስረዳሉ።

በዛሬው ዕለት በወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የተተኩት አቶ ዳኜ መላኩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር። ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ሰለሞን አረዳ እንደ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ሁሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ የሕግ ትምህርት ቤት ምሩቅ ናቸው። በፌድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ፣በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዳኝነት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሰርተዋል። በዓለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት በገላጋይ ዳኝነት በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ሰለሞን በሙያቸው የማማከር አገልግሎትም ይሰጣሉ።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW