1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ፑቲን እና ዜሌንስኪ እንዲገናኙ ሩሲያና ዩክሬን ሥምምነት ላይ መድረስ አለባቸው - ክሬምሊን

ቅዳሜ፣ ግንቦት 9 2017

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬን አቻቸው ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ፊት ለፊት ሊገናኙ የሚችሉት ሁለቱ ሀገራት ሥምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ብቻ እንደሆነ ክሬምሊን አስታወቀ። የሁለቱ ሀገራት ተደራዳሪዎች በቱርክ በተገናኙ በማግሥቱ ሩሲያ በሰሜናዊ ዩክሬን በምትገኘው ሱሚ በድሮን በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ሱሚ በድሮን በፈጸመችው ጥቃት የተጎዳ አውቶቡስ
ንግግሩ ከተደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ሩሲያ በሰሜናዊ ዩክሬን በምትገኘው ሱሚ የተባለች ግዛት ሲቪል ሰዎች በጫነ አውቶቡስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ  ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ምስል፦ Ukrainische Militärverwaltung

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩክሬን አቻቸው ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ፊት ለፊት ሊገናኙ የሚችሉት ሁለቱ ሀገራት ሥምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ብቻ እንደሆነ ክሬምሊን አስታወቀ። የፕሬዝደንት ፑቲን ጽህፈት ቤት አቋሙን ያሳወቀው ሞስኮ እና ኪየቭ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቱርክ ያደረጉት ቀጥተኛ ንግግር ያለ ውጤት ከተበተነ በኋላ ነው።

በኢስታንቡል በተደረገው ንግግር የተኩስ አቁም ላይ ከመደረሱ በፊት ዩክሬን ከዶኔትስክ፣ ዛፖሬዥያ፣ ኼርሶን እና ሉኸንስክ ግዛቶች ወታደሮቿን እንድታስወጣ የሩሲያ ተደራዳሪዎች ቅድመ-ሁኔታ ማስቀመጣቸውን አንድ ስማቸው እንዲገልጽ ያልፈለጉ የዩክሬን ባለሥልጣን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

ግዛቶቹ በአብዛኛው ወይም በከፊል በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ቢሆኑም የዩክሬን ወታደሮች መልሰው በእጃቸው ለማስገባት አሁንም ውጊያ እያደረጉ ናቸው። አሜሪካ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም ባዘጋጀችው የሥምምነት ረቂቅ ውስጥ እንዲህ አይነት ቅድመ-ሁኔታ አላካተተም።

የሩሲያ ተደራዳሪዎች አራቱ ግዛቶች እና በጎርጎሮሳዊው 2014 ሩሲያ ከዩክሬን በኃይል የገነጠለቻት ክሬሚያ የሩሲያ ለመሆናቸው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲሰጥ፣ ዩክሬን ገለልተኛ ሀገር እንድትሆን፣ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ እንዳትታጠቅ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ጭምር ማቅረባቸውን ባለሥልጣኑ እንደተናገሩ ሬውተርስ ዘግቧል።

የሩሲያ ተደራዳሪዎች የፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ መንግሥት አጋሮች ወታደሮቻቸውን በዩክሬን እንዳያሰፍሩ እና በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች በጦርነት ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንዳይጠይቁ ጭምር ቅድመ-ሁኔታ አቅርበዋል።

የሩሲያ ተደራዳሪዎች አቀረቡት ስለተባለው ቅድመ-ሁኔታ የተጠየቁት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ንግግሮቹ ከመጋረጃ ጀርባ መካሔድ ስላለባቸው በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

በኢስታንቡል በተደረገው ንግግር የተኩስ አቁም ላይ ከመደረሱ በፊት ዩክሬን ከዶኔትስክ፣ ዛፖሬዥያ፣ ኼርሶን እና ሉኸንስክ ግዛቶች ወታደሮቿን እንድታስወጣ የሩሲያ ተደራዳሪዎች ቅድመ-ሁኔታ ማስቀመጣቸውን አንድ ስማቸው እንዲገልጽ ያልፈለጉ የዩክሬን ባለሥልጣን መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።ምስል፦ Arda Kucukkaya/Turkish Foreign Ministry/REUTERS

ንግግሩ ከተደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ሩሲያ በሰሜናዊ ዩክሬን በምትገኘው ሱሚ የተባለች ግዛት ሲቪል ሰዎች በጫነ አውቶቡስ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ  ሰዎች መገደላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። በጥቃቱ ሌሎች አምስት ሰዎች ተጎድተዋል። ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በሱሚ በሩሲያ የድሮን ጥቃት የተገደሉት በሙሉ ሰላማዊ ሰዎች እንደነበሩ አስታውቀዋል።

“ትላንት እንደ ማንኛውም የዚህ ጦርነት ቀናት ተኩስ የማቆም ዕድል ነበር” ያሉት የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ “ሩሲያ መግደል የመቀጠል ዕድሉን ብቻ ይዛ ቀጥላለች” ሲሉ ተችተዋል።

ዜሌንስኪ “ያለ ጠንካራ ማዕቀብ፤ በሩሲያ ላይ ጠንካራ ጫና ሳይደረግ እውነተኛ ዲፕሎማሲ አይኖርም” በማለት የዩክሬን አጋሮች በሩሲያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጥሪ አድርገዋል።

የዩክሬን ዋና ተደራዳሪ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሩስቴም ኡሜሮቭ ቀጣዩ እርምጃ የዜሌንስኪ እና የፑቲን የፊት ለፊት ስብሰባ እንደሆነ ገልጸዋል። ዩክሬን የጠየቀችው የሁለቱ መሪዎች የፊት ለፊት ግንኙነት “ይቻላል ብለን እናስባለን” ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ይሁንና ፑቲን እና ዜሌንስኪ ሊገናኙ የሚችሉት “በሁለቱ ወገኖች መካከል በሥምምነት መልክ አንዳች ውጤት ሲገኝ ብቻ” እንደሚሆን ዛሬ ቅዳሜ የክሬምሊን ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።

የሩሲያ ዋና ተደራዳሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ ሞስኮ እና ኪየቭ ወደፊት ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል የተኩስ አቁም ዕቅዳቸውን እንደሚያቀርቡ ተናግረው ነበር። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ረዳት የሆኑት የሩሲያ ዋና ተደራዳሪ የሁለቱ ሀገራት የተኩስ አቁም መቼ ሊቀርብ እንደሚችል ግን ያሉት ነገር የለም።

በቱርክ በተካሔደው ንግግር በተደረሰው ሥምምነት መሠረት በቅድሚያ ሩሲያ እና ዩክሬን እያንዳንዳቸው 1,000 የጦር ምርኮኛ ወታደሮች መለዋወጥ እንደሚገባቸው ትላንት አርብ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረው ነበር።

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW