1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፓስፖርት የማውጣት እንግልት በአማራ ክልል

ዓርብ፣ ኅዳር 13 2017

ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፓስፖርት መታወቂያ ለማውጣት ወደ ባሕርዳር ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚመጡ ተገልጋዮች በተራዘመ ቀጠሮና በከፍተኛ ወጪ በእጅጉ መማረራቸውን ገልጠዋል፡፡ “ፓሰፖርት ለማውታት ለትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች ብቻ እስከ 12 ሺህ ብር ወጪ እናወጣለን”ብለዋል ተገልጋዮች።

Äthiopien Antragsteller Pass in Bahirdar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ፓስፖርት የማውጣት እንግልት በአማራ ክልል

This browser does not support the audio element.

 

ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፓስፖርት መታወቂያ ለማውጣት ወደ ባሕርዳር ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሚመጡ ተገልጋዮች በተገልጋዩ ቁጥር መበራከት፣ በተራዘመ ቀጠሮና በከፍተኛ ወጪ በእጅጉ መማረራቸውን ገልጠዋል፡፡ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ተራ ለማስያዝ ለሚደረግ ምዝገባ፣ አሻራ ለመስጠትና ፓስፖርት ለመውሰድ እስክ 6 ወራትና ከዚያ በላይ ይወስድባቸዋል፡፡
“ፓሰፖርት ለማውታት ለትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች ብቻ እስከ 12 ሺህ ብር ወጪ እናወጣለን” ብለዋል ተገልጋዮች።

ፓስፖርት ለማውጣት 12 ሺህ ብር

ከሰሜን ወሎ ዞን ሀራ ከተባለ አካባቢ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ባህርዳር በተለያዩ ጊዜዎች እስክ 3 ጊዜ መመላልሷንና ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ መዳረጓን አንድ ተገልጋይ ተናገራለች፡፡ በነዚህ ጊዜዎች ለትራንስፖርት፣ ለአልጋና ምግብ ወጪዎች እስከ 12 ሺህ ብር ወጪ ማድረጓን ገልጣለች።
ለደርሶ መለስ ለትራንስፖርት ብቻ 2 ሺህ ብር እንደምታወጣ የምትናገረው ይቺ ወጣት፣ ምዝገባም ሆን አሻራ ለመስጠት አንድ ቀን ስለማይበቃ እስከ 4 ቀናት አልጋ ይዞ መጠበቅ እንዳለ ነው ያስረዳችው፣ ጥንቃቄ ካልተደረግ ደግሞ መዘረፍም እንዳለ ነው ያስረዳችው፡፡ ከምዝገባ ፓስፖርቱን እስከመውሰድ ባለው ጊዜ ከ12 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጓንም ተናግራለች፡፡ በሚያጋጥም የፀጥታ ችግር ምክንያት ከመንገድ የተመለሰችበት ጊዜ እንደነበረም አስታውሳለች።
በባሕርዳር ኢሚግሬሸንና ዜግነት አገልግሎት  ቀልጣፋ አሰራር ስላለመኖሩ

ሌላ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪና ፓስፖርት በቅርቡ እንዳወጡ የነገሩን ተገልጋይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና የተቋሙ ሠራተኞች ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም ይላሉ፣ ከሠራተኞች ማነስ ይሁን አሊያም ከሠራተኞቹ የሥራ መሰላቸት፣ ቀልጣፋ አሰራር በተቋሙ አይታይም ነው ያሉት። በተለይ ከሌሎቸ አካባቢዎች መጥተው አገልግሎቱን ለማግኘት  የሚሞክሩ ሠዎች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ እንደሆኑ ገልጠዋል።

በባህርዳር ፓሰፖርት ለመውሰድ እስከ 6 ወራት ቀጠሮ  ይሰጣል።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ፓሰፖርት ለመውሰድ እስከ 6 ወራት ቀጠሮ 

የተገልጋዩ ቁጥር እጅግ በርካታ እንደሆነ አመልክተው፣ ፓስፖርቱን ለማግኘት ወራትን እንደሚወስድ ተናግረዋል፣ በተለይ ከባህርዳር ወጪ አገልግሎቱን ለማግኘት ከሶስትና አራት ጊዜ በላይ ስለሚመላለሱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ለከፍተኛ እንግልትና ወጪ እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡“እንግልት፣ የሥራ ፍስሰትና መጉላላት ይፈጥራል” ያሉትን ሂደት እኚሁ አስተያየት ሰጪ አብራርተዋል።“ተራ ለመያዝ ረጅም ኪሎሜትር አቋርጠው የሚመጡ አሉ፣ የደቂቃዎች ሥራ የሆነውን የአሻራ መስጠት ሂደት ረጅም ጉዞ ተጉዘው በሕር ዳር 3 እና 4 ቀን አልጋ የሚይዙ አሉ፣ እንደገና ፓስፖርት ለመውሰድ ደግሞ ሌላ ወጪና እንግልት ያጋጥማቸዋል” ብለዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እንግልትና ወጪ እንዲቀንስ ጠይቀዋል፡

ባህርዳር የሚገኘው ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቢሮምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከወልዲያ ከተማፓስፖርት እንዳወጣች የነገረችን ሌላዋ ተጠቃሚም አንዳንዴ በተቋሙ ሠራተኞች መደብደብና መባረር እንዳለ ለዶይቼ ቬሌ በሰጠችው አስተያየት አመልክታለች፡፡
የቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ አስተያየት እንዲሰጡን ለባሕርዳር ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ አስማረ ብንደውልም፣ ጉዳዩ የፌደራሉን ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደሚመለከት ምላሽ ሰጥተዋል።

ለፌደራሉን ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማስተዋል ገዳ ደውለን መታውቂያ ከላክሁላቸው በኋላ ምላሽ እንደሚሰጡ ወይም የባሕር ዳር ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምላሽ እንደሚሰጥ እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም፣ የመታወቂያ ኮፒ ከላክሁላቸው ብኋላ ከትናነት ጀምሮ ለህዝብ ግንኙንት ዳይሬክተሯም ሆነ ለባሕርዳር ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ኃላፊ በተድጋጋሚ ብንደውልም ሆነ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ጭምር ብንጠይቅም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።


ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW