1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፔሌ፦ ብራዚሊያዊው የኳስ ንጉሥ ስንብት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2015

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለሦስት ጊዜያት በመውሰድ ብቸኛው የኳስ ሰው፤ ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ፤ በይበልጥ በሚታወቅበት ስሙ ፔሌ ከካንሰር ኅመም ለመዳን ሲታገል ቆይቶ በ82 ዓመቱ አርፏል። ሐሙስ፤ ታኅሣሥ 20 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ብራዚሊያዊው የኳስ ንጉሥ ከዚህ ዓለም ተለይቷል።

Fussballspieler Pele
ምስል John Pratt/Keystone/Getty Images

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ለሦስት ጊዜያት በመውሰድ ብቸኛው የኳስ ሰው፤ ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ፤ በይበልጥ በሚታወቅበት ስሙ ፔሌ ከካንሰር ኅመም ለመዳን ሲታገል ቆይቶ በ82 ዓመቱ አርፏል። ሐሙስ፤ ታኅሣሥ 20 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ብራዚሊያዊው የኳስ ንጉሥ ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ፔሌ ለኳስ ከተሰጠው እጅግ ልዩ ተሰጥዖው የተነሳም ብዙዎች «ሲወለድ በእግሩ ኳስ ይዞ ነው» ሲሉ ያደንቁታል።ገና ሲወለድ አንስቶ ችሎታውን የተረዱለት አባቱ፦ከፈጣሪ ልዩ ስጦታ ተሰጥቶሀል ተጠቀምበት እያሉ ያበረታቱት ነበር። ተጠቀመበት፤ ገና በጮርቃነቱም ዓለምን አስደምሟል። 

ሰኔ 22 ቀን፣ 1958 ዓ.ም፤ ፔሌ ገና በ17 ዓመቱ በእርግጥም ኮከብ መሆኑን አስመስክሯል። ከዚያ በኋላ ሁሌም የሚታወቅበትን 10 ቁጥር መለያውን ያደረገው ፔሌ በወቅቱ ከብራዚል ቡድኑ ጋር ሆኖ ስዊድንን በፍጻሜው 5 ለ2 በመርታት የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ድሉን አጣጥሟል። በ55ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠሩት ሁለት ግቦች የዚህ ታዳጊ ኮከብ ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ ነበሩ። የፔሌ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ፣ እያንዳንዱ ያቀብላቸው የነበሩ ኳሶች፤ እያንዳንዱም ግቦች ልዩ ነበሩ። 

ፔሌ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ብራዚል ጣሊያንን 4 ለ1 ካሸነፈች በኋላ ዋንጫውን ከፍ አድርጎ እየሳቀምስል STF/AFP/Getty Images

ፔሌ በእድሜ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ፣ ለጋው የፍጻሜ ግጥሚያ ተሳታፊ፤ በእድሜ ትንሹ በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦች በማስቆጠር ሔትሪክ ሠሪው፤ እንዲሁም ወጣቱ በፍጻሜ ፍልሚያ ግብ አስቆጣሪ በመሆን በፊፋ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ከብዙዎች ይለያል። ፔሌ የዛሬ 52 ዓመት በተደረገው የሜክሲኮው የዓለም ዋንጫ ስድስት ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸትም ማግባት ብቻ ሳይሆን በቡድን በመሥራትም ድንቅ ችሎታውን አስመስክሯል። ይህንንም ፊፋ በድረ-ገጹ ማንም ያልደረሰበት ክብረ-ወሰኑን እንደያዘ የቆየ ሲል አወድሶ ስለ ፔሌ ዝክር ጽፏል። አምስት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን በማመቻቸት አራት ተጨዋቾች ፔሌን ይከተሉታል። እነሱም፦ ሮቤርት ጋዶቻ፤ ፒዬር ሊትባርስኪ፤ ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና እና ቶማስ ሔይስለር ናቸው።

በ1958 ብራዚል ፈረንሳይን 5 ለ2 ባሸነፈችበት ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ፔሌ 10 ቁጥር መለያ ለብሶ ኳሷን በጭንቅላት ሊያገባ ሲጥርምስል Keystone/Hulton Archive/Getty Images

ፔሌ በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ሦስት ግብ ሊሆኑ የቻሉ ኳሶችን በማመቻቸትም ክብረ-ወሰን ይዟል። አንደኛው ስዊድንን ባሸነፉበት የፍጻሜ ግጥሚያ ነው። ሌላኛው ደግሞ የዛሬ 52 ዓመት ብራዚል በሜክሲኮ ሲቲ ኤስታዶ አዜትካ ስታዲየም ውስጥ ጣሊያንን 4 ለ1 በረታችበት የፍጻሜ ግጥሚያ ነው። በወቅቱ የመጀመሪያውን ግብ 18ኛው ደቂቃ ላይ በከፍታ በመዝለል በጭንቅላት ገጭቶ ያስቆጠረው ፔሌ ነበር።
በኳስ አጨዋወት ልዩ ችሎታው፤ ቴክኒኩ እና ለጨዋታው በነበረው ፍቅር ዓለምን አስደምሟል፤ የኳስ ንጉሡ ፔሌ።  የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፊፋ (FIFA) «እግር ኳስ እና ዓለም ስለ ፔሌ አዝኗል» ሲልም ጽፏል። በእርግጥም በመላው ዓለም የሚገኝ የእግር ኳስ አፍቃሪ እና አድናቂዎቹ ከልብ አዝነዋል። 

ኤድሰን አራንቴስ ናሲሜንቶ፤ 
የካስ ንጉሡ ፔሌ፤ 
በሰላም እረፍ!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW