«ፔሌ» የሚለውን ስም የኳስ ንጉሡ እንዴት አገኘ?
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2015
ሲወለድ በቤተሰቦቹ የተሰጠው ስም ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ (Edson Arantes do Nascimento) ነበር። ብዙዎች ግን የሚያውቁት «ፔሌ» በሚለው አጠር ያለው የቅጽል መጠሪያው ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1958፤ 1962 እና 1970 ዓ.ም የዓለም እግር ኳስ ዋንጫዎችን ለሦስት ጊዜያት በመውሰድ ብቸኛው የኳስ ሰው ነው። ይህን ክብረ ወሰኑን ማንም እስካሁን አልደፈረውም።
ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ «ፔሌ» እንዴት ተባለ?
ይህን መልስ ለማግኘት የፔሌ የህጻንነት ዘመንን መቃኘት ያሻል። አጎቱ ዮርጌ ትንሹ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ እንዴት ፔሌ ሊባል እንደቻለ በአንድ ወቅት ተጠይቀው ስለዚሁ ጉዳይ ቀጣዩን ብለዋል። ፔሌ ህጻን ሳለ በአጥቂነት ልዩ ችሎታው ማንም የሚያቆመው በመታጣቱ ተጋጣሚዎች ዕድል እንዲያገኙ በሚል ግብ ጠባቂ ይደረጋል። ከባላጋራ የተመቱ ኳሶችን በግብ ጠባቂነት ሲያጨናግፍም ትንሹ የኳስ ጥበበኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ «ቢሌ» (Bilé) ይል ነበር። «ቢሌ» ከፔሌ አባት ጋር ግብ ጠባቂ ሆነው የሚጫወቱ ሰው ነበሩ። ከዚያም እንደ ቀልድ በቅጽል ስም «ቢሌ» እያሉ መጥራት ጀመሩ። በሒደት ይሄ ደወ «ፔሌ» መቀየሩም ይነገራል። ፔሌ ራሱ ከ16 ዓመት በፊት «ዘ ጋርድያን» ለተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ይህንኑ አረጋግጧል።
«የሦስት ዓመት ህጻን ሳለሁ አባቴ ዶንዲንሆ ወደ ባስኮ የኳስ ስልጠና ማዕከል ይወስደኛል።»
«የተመቱ ኳሶችን ሳጨናግፍም ‘ጥሩ ነው ቢሌ!’ ወይንም ‘በድንቅ ሁኔታ አጨናግፈሀል ቢሌ’!» እያልሁ እጮህ ነበር»
«ትንሽ ልጅ ስለነበረም ቅላጼው ‘ፒሌ’ የሚል አይነት ይመስል ነበር። ወደ ባውሩ ቀይረን ስንሄድም ይሄ ‘ፒሌ’ የሚለው ‘ፔሌ’ ሆነልህ» ብሏል ስለ ትንሹ ፔሌ አዛውንቱ ፔሌ ሲናገር።
«እኔም ብሆን ስያሜውን አልቀየርሁትም። እንደ አጎቴ ዮርጌ አባባልም የሚናስ ጌራይ ጠንካራ ቅላጼ ስላለኝም ነበር»ም ብሏል «ቢሌ» የሚለውን በቅላጼው የተነሳ «ፔሌ» ስለማለቱ ሲያብራራ።
ምናልባት «ከፈረሱ አፍ» እንደሚባለው የአምፖል ፈልሳፊው ቶማስ ኤዲሰን ስም ጋር በመመሳሰሉ የቀድሞ ስሜን እወድ ነበር ያለው ትንሹ «ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ» ከ«ቢሌ» ወደ «ቤሌ» ከዚያም ወደ «ፔሌ» ስሙ እንደተቀየረ ምላሽ የተገኘ ይመስለናል።
አንድ ለመንገድ፦ ትንሹ «ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ» በልጅነት ዘመኑ «ፔሌ» የሚለውን ስም በጣም ነበር የሚጠላው። ቅጽል ስሙን ከመጥላቱ የተነሳም በዚሁ ስያሜ የተነሳ በአንድ ወቅት ከትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር ተጣልቶ ለሁለት ቀናት ከትምህርት ቤት ታግዶም ነበር። በቋንቋው «ፔሌ» የሚለው ስም ምንም ትርጉም የሌለው በመሆኑም እንደ ስድብ አድርጎም ይወስደው እንደነበር ተናግሯል። ሆኖም ቃሉ በእብራይስጥ «ተዐምር» ማለት እንደሆነ ሲረዳ ግን «ፔሌ» ለሚለው ስያሜ የነበረው ሐሳቡን እስከ ወዲያኛው መቀየሩም ይነገራል።
ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ «ፔሌ» ለአንድ ወር ያህል አልበርት አይንሽታይን ሐኪም ቤት ሲታከም ከቆየ በኋላ በ82 ዓመቱ ሐሙስ፤ ታኅሣሥ 20 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ተለይቷል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ