ፕላስቲክን ወደ ነዳጅ የቀየሩት ወጣቶች
እሑድ፣ ሐምሌ 17 2014
በዓለማችን የአካባቢ ብክለትን ከሚያስከትሉ እና የአፈር ለምነትን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጎዱ ነገሮች መካከል የፕላስቲክ ቆሻሻ አንዱ ነው። ይህንን ችግር ለመከላከል ሀገራት የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ለመጠቀም ከፍተኛ ወጭ ያወጣሉ።ያም ሆኖ መልሶ መጠቀም የተቻለው ከ10 በመቶ በታች ነው። ከወደ ጅማ ስድስት ወጣቶች የፕላስቲክ ቆሻሻን ወደ ነዳጅ መቀየር የሚያስችል ማሽን ሰርተዋል።የዛሬውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በወጣቶቹ ስራ ላይ ያተኩራል።
በአሁኑ ወቅት የፕላስቲክ ቆሻሻ በዓለማችን ትልቅ ችግር ነው።.ፕላስቲክ በባህሪው ቶሎ የማይበሰብስ በመሆኑ በቆሻሻ መጣያዎች እና በውቅያኖሶች ሳይቀር ለዘመናት ተከማችቶ ይቆያል።ይህም የአፈር ለምነትን እና በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ህይወት ያላቸው ነገሮችን እየጎዳ ነው።በዚህ የተነሳ የፕላስቲክ ቆሻሻ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀውስ አስከትሏል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ በ አመት ወደ 300 ሚሊዮን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ይከማቻል። ይሁን እንጅ ከዚህ ውስጥ 9% ብቻ እንደገና ጥቅም ላይ ይውላል።ምክንያቱም የፕላስቲክ ቆሻሻንን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ውጤታማ ባለመሆኑና የሚያስፈልገው ወጭም ከፍተኛ በመሆኑ ነው።በዚህ የተነሳ ችግሩ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሀገራት የከፋ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያሰቡ ስድስት ወጣቶች የፕላስቲክ ቆሻሻን ወደ ነዳጅ መቀየር የሚያስችል ማሽን ሰርተዋል።
ወጣቶቹ የጅማ ዩንቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና የዚህ ዓመት ተመራቂዎች ሲሆኑ ማሽኑን የሰሩት ለመመረቂያቸው መሆኑን ከወጣቶቹ መካከል አንዷ የሆነችው ስምረት ጴጥሮስ ገልፃለች።
«የመመረቂያ ጽሁፋችንን ነው የሰራ ነው። ፓይሮላይሲስ በሚባል ቴክኖሎጅ።«ዌስትፕላስቲክን» እንዴት ወደ ነዳጅ መቀየር እንደሚቻል እሱን መስራት የሚችል ማሽን ነው።«ዲቨሎጵ» ያደረግነው። ለስድስት ነው ይህንን ፕሮጀክት የሰራነው። የሀሳብ በፍርዱ፣ አቤል ደጀኔ፣አማኑኤል ግርማ፣ምትኩ ሰቦቃ፣ ፂዮን በቀለ እና እኔ/ስምረት ጴጥሮስ/ ሆነን ማለት ነው ። ከ አድቫይዘራችን ጋር እሱ እየረዳን እያገዘን ለመስራት ችለናል ማለት ነው።»በማለት ስምረት ገልፃለች።
እንደ ስምረት ገለፃ ማሽኑ ፕላስቲክን ወደ ነዳጅ እንዲቀይር ለማድረግ ፓይሮላይሲስ የተባለውን ቴክኖሎጅ ተጠቅመዋል።መነሻቸውም በአካባቢው የተመለከቱት ተጨባጭ ችግር ነው።
ችግሩ በኢትዮጵያም ከፍተኛ መሆኑን ነባራዊ ሁኔታውን ቀድመው መመልከታቸውን የምትገልፀው ስምረት፤ በተለይ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና እጥረት እያስከተለ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር ማሽኑን ለመስራት የገፋፋቸው ሌላው ምክንያት ነው።
ነዳጁን ለማምረት በግብዓትነት የተጠቀሙት በተለምዶ ጀሪካን እያልን የምንጠራውን የዘይትና ሌሎች ፈሳሽ ነገሮችን ለመያዝ የሚያገለግለውን «HDPV» የተባለውን የፕላስቲክ አይነት ሲሆን ለወደፊቱ ግን ሁሉንም አይነት ፕላስቲኮች ለመጠቀም በተለይ የውሃ መያዣ የፕላስቲክ ጠርሙሶች/PET/ በአካባቢ ብክለት በብዛት የሚታወቁ በመሆናቸው እነሱን በስፋት ለመጠቀም ዕቅድ እንዳላቸው ገልፃለች።
በተደረገው ሙከራ በአንድ ሰዓት ውስጥ ሦስት ኪሎ ግራም ፕላስቲክ በመጠቀም ሁለት ሊትር ነዳጅ ማምረት መቻሉን ተናግራለች። እንደ ስምረት ገለፃ በስፋት ከተሰራበት ከዚህ በላይ ማምረት ይቻላል።
ወጣቶቹ የተጠቀሙት ቆሻሻ ፕላስቲክን ወደ ነዳጅ የመቀየር ሀሳብ አዲስ አይደለም።ብዙ ተመራማሪዎች ይህንን ሂደት ተጠቅመው ውጤት ያገኙት ሲሆን፤አሰራሩም ከኦክሲጅን ነፃ በሆነ አካባቢ ፕላስቲክን ከ300º ሴ እስከ 900º ሴ ድረስ በማሞቅ ንጥረ ነገሩን ወደ ነዳጅ የሚቀይር ነው ። በአጠቃላይ የፓይሮላይሲስ ቴክኖሎጂ ቆሻሻን ወደ አዲስ ኃይል የመቀየር ሂደት ሲሆን፤ አዋጭ እና ውጤታማ ነው ። ነገር ግን ሂደቱን ለማከናወን ጥራት ያለውን ማሽን መጠቀም አስፈላጊ ነው።ከዚህ አንፃር ወጣቶቹ ማሽኑን የተሻለ ለማድረግ የማሻሻል ስራ እንደሚሰሩ ሌላው የቡድኑ አባል ወጣት የሀሳብ በፍርዱ ገልጿል። ከማሻሻያው በኋላም ወደ ገበያ የማቅረብ ሀሳብ እንዳላቸው አስረድቷል።
በአሁኑ ወቅት በሶስት አይነት መንገድ የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። በሜካኒካዊ ፣ በማቃጠል እና በኬሚካላዊ መንገድ ። ሜካኒካዊ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ዘዴ የወዳደቁ ፕላስቲኮች መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ አማራጭ ሲሆን፤ የፕላስቲክ ቆሻሻን በመፍጨት ወይም በማዋሃድ ለተመሳሳይ ምርቶች እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግን ያካትታል። ይሁን እንጂ በዚህ ሂደት የሚመረተው የፕላስቲክ ምርት ጥራት የሌለው በመሆኑ የተቀባይነት ችግር ስላለበት.ብዙም ውጤታማ አይደለም። ሁለተኛው ኬሚካላዊ መልሶ የመጠቀም ዘዴ ሲሆን የሩቲኒየም ብረታ ብረት እና ካርቦንን የመሳሰሉ ውህዶችን እንደ ማነቃቂያ በመጠቀም የፕላስቲክ ቆሻሻን ወደ ነዳጅ መቀየር ነው። ይህ ዘዴ ከሌሎቹ በተሻለ መልኩ ፈጣን እና ውጤታማ ቢሆንም፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና ቤተሙከራ የሚፈልግ ፤ በዋጋ ደረጃም ውድ ነው።
ሶስተኛው በማቃጠል መልሶ የመጠቀም ቴክኖሎጅ ሲሆን በሙቀት ሀይል ፕላስቲኮችን በማቅለጥ ወደ ነዳጅ መቀየር ነው። ይህ ዘዴ በአብዛኛው እየተሰራበት ቢሆንም ፤ከፍተኛ የሙቀት ሀይልን የሚፈልግ በመሆኑ በዛ ያለ ማገዶ መጠቀምን ይጠይቃል። ይህንን ለማሻሻልም ወጣቶቹ የማገዶ እንጨትን ሳይሆን የወዳደቁ የቡና ተረፈ ምርቶችን እና ሌሎች ቆሻሻዎችን በማቃጠል ፕላስቲኮቹን ለማቅለጥ ተጠቅመዋል።በዚህም እንደ ወጣት የሀሳብ ቆሻሻን በቆሻሻ በማቃጠል ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ ጥረዋል።
በሌላ በኩል በሂደቱ እንደ አሲድ ጋዞች እና ከባድ ብረቶች ያሉ መርዛማ ነገሮች ስለሚፈጠሩ ብክለትን ለመከላከል ጥንቃቄ ይፈልጋል።በዚህ ረገድ ወጣቶቹ በሰሩት የፕላስቲክ ማቃጠያ ማሽን ላይ ለችግሩ አፅንኦት መስጠታቸውን በጅማ ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ተቋም የሜካኒካል ምህንድስና መምህር እና የፕሮጀክቱ አማካሪ የሆኑት አቶ አብርሃ ካህሳይ ገልፀዋል።
ወጣቶቹ የሰሩት ማሽን ወይም ቴክኖሎጅ በአሁኑ ወቅት በሌሎች ሀገራት በስፋት እየተሰራበት ቢሆንም ፤ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት ግን ዋጋው ውድ በመሆኑ የተነሳ ብዙ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም።በመሆኑም በአካባቢ የሚገኑ ነገሮችን በመጠቀም ማሽኑ በሀገር ውስጥ መሰራቱ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አብርሃ አስረድተዋል።
በማሽኑ ለሙከራ የተመረተው ነዳጅ ውጤታማነቱ የተሞክረ ቢሆንም በቀጣይ ተጨማሪ ጥናት እና ማሻሻያ የሚያስፈልገው መሆኑንም ገልፀዋል።ለዚህም የዩንቨርስቲው ድጋፍ እንደሚቀጥል አቶ አብርሃ ተናግረዋል።ከዚህ አኳያ ለሁለት ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው የሁለተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር እንዲከታተሉ መፈቀዱን ጨምረው ገልፀዋል።ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶች እና ሌሎች የጥናት ተቋማት እገዛ ቢያደርጉ የበለጠ የተሳካ ስራ መስራት ይቻል ነበር ብለዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ