1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በሴኔጋል

ቅዳሜ፣ የካቲት 17 2004

ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸው የሴኔጋል ዜጋ በነገው ዕለት አዲስ ፕሬዚደንት ለመምረጥ ወደምርጫ ጣቢያዎች ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሥራ አራት ዕጩዎች በተወዳዳሪነት

የሴኔጋሉ ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድምስል REUTERS

ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸው የሴኔጋል ዜጋ በነገው ዕለት አዲስ ፕሬዚደንት ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሥራ አራት ዕጩዎች በተወዳዳሪነት ቀርበዋል።

ነገር ግን፡ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን በዕጩነት መቅረባቸውን ያልተቀበሉ ቡድኖች እና ሲቭል ማህበረሰቦች እያካሄዱት ባለው ኃይል የታከለበት ተቃውሞ ለወትሮው መረጋጋት በሰፈነባት ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር ውስጥ አሳሳቢ ውዝግብ አስከትሎዋል። ከብዙ አሠርተ ዓመት በተቃዋሚው ጎራ መቆየት በኋላ አብዱላይ ዋድ እአአ በ 2000 ዓም ሥልጣን በያዙበት ጊዜ ትልቅ የሕዝብ ድጋፍ ነበራቸው። ይሁንና፡ ዛሬ ከአሥራሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዚደንቱ ያኔ አግኝተውት የነበረውን ሰፊ ድጋፍ አጥተዋል። እና አሁን በሀገሪቱ የቀጠለው ኃይል የታከለበት ተቃውሞ በሳህል አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው እና አክሚ በመባል ለሚታወቀው አሸባሪ ድርጅት ሴኔጋል ውስጥ የሚያንሰራራበትን አጋጣሚ ይፈጥር ይሆን በሚል ብዙዎች መሥጋታቸው አልቀረም።

------

ሴኔጋል በሀገሯ የነበሩና በማግሬብ አካባቢ ሀገሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው በምሕፃሩ አክሚ የተባለው የአሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው ብላ የጠረጠረቻቸውን የሞሪታንያ ዜጎችን ገና በ2010ዓም ነበር ያባረረችው። የቀድሞው የተመድ የምዕራብ አፍሪቃ ልዑክ የሞሪታንያው ተወላጅ መሀመድ ኡልድ አብደላም አክሚ በሴኔጋል የሚንቀሳቀሱ ክፍሎች እንዳሉት በ2011ዓም ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። አንዳንድ በዚሁ አካባቢ በአክሚ ታግተው የነበሩ ግለሰቦች ጠባቂዎቻቸው ሴኔጋላውያን እንደነበሩ የተመድ በሊቢያ የቀድሞው መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ ከተገደሉ በኋላ ያካባቢውን ፀጥታ የሚቃኝ ባለፈው ወር ወደዚያው ለላከው አንድ ቡድን ገልጸውለታል። ያካባቢውን ፖለቲካዊና ሀይማኖታዊ ሁኔታዎችን በቅርብ የሚከታተለው ሴኔጋላዊው ጋዜጠኛ ማም ሌስ ካማራ እንደሚለው፡ አክሚ በሴኔጋል ሊስፋፋ የሚችልባቸው የተለያኡ ሁኔታዎች አሉ።
«« ሴኔጋል ውስጥ ሀይማኖት ከፖለቲካ ይበልጥ ጠንካራ ነው። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት አብዱላይ ዋድ ኻሊፉ ጉልበት ላይ ሲወድቁ የሚያሳዩ ሥዕሎች ይህንን ያረጋግጣሉ። እርግጥ፡ ሴኔጋል ውስጥ ሀይማኖትን መሠረት ያደረገ መንግሥት የለም። ግን፡ በሀገሪቱ የሚወሰድ ርምጃ ሁሉ በሀይማኖት መቻቻል ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። »
»
ሴኔጋልም የአሸባሪው ድርጅት አል ቓይዳ መሪ የነበሩት የኦሳማ ቢን ላደን ትውልድ ሀገር ከሆነችው እና የተለያዩ አክራሪ ሀይማኖታዊ ቡድኖች ከሚገኙባት ሳውዲ ዐረቢያ ጋ የኤኮኖሚ ትሥሥርዋን አጠናክራለች። የሴኔጋል ሙሥሊም ኢማሞችም አክራሪ የእሥልምና መሥመር የሚከተሉ ቡድኖች ወዳሉባቸው ግብፅ፡ የባህረ ሠላጤ ሀገሮችና ሊቢያን ወደመሳሰሉ በመሄድ ሥልጠና ማድረግ ከጀመሩ ቆየት ብለዋል። በናይጀሪያም ከሚንቀሳቀሰው ቦኮ ሀራምም ጋ ግንኙነት እንዳላቸው ተረጋግጦዋል። በሴኔጋል ካሉት የሙሥሊም ወንድማማችነት ቡድኖች መካከል አንዱ ብዙዎቹን ተከታዮቹን ለሥልጠና የሚልከው ወደ ናይጀሪያ መሆኑ ይታወቃል። ጋዜጠኛው ማም ሌስ ካማራም ይህን ሂደት ሲመለከት፡ በተለይ የወደፊቱ ዕጣ ፈንታቸው ያልታወቁት አዘውትረው ሥራ አጥ የሆኑት የሀገሩ ወጣቶች ሁኔታ እጅግ ያሳስበዋል።


« በእሥልምና ደንቦች ላይ የተመሰረተ ኑሮ መኖርን ለሚያስተጋቡበት የአክራሪ ሰባኪዎች ንግግር በወቅቱ ትልቅ ትኩረት የሚሰጡ ብዙ ወጣቶች በሀገሪቱ አሉ። »
ይህን ዓይነቱ አክራሪነትና አል ቓይዳም ሥር እየሰደደ የሚሄድበት ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚጠናከረው ደካማ መንግሥታት ባሉባቸው ሀገሮጭ ነው። ለምሳሌ፡ ማሊና ሞሪታንያን በመሳሰሉ ሀገሮች ውስጥ አክሚ ሥር ከሰደደ ሰንበት ብሎዋል።
ፕሬዚደንት ዋድ ለሦስተኛ ጊዜ ለመወዳደር መወሰናቸው አክሚ በዚችው ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ውስጥ ተፅዕኖውን እንዳያስፋፋ ብዙዎች ሠግተዋል፤ ይሁንና፡ ፈረንሣዊው የሽብርተኝነት ጉዳይ ተመራማሪ ዦን ሻርል ብሪዛር ሴኔጋል በአክሚ እጅ ከምትወድቅበት ደረጃ በወቅቱ እጅግ ርቃ እንደምትገኝ ነው የገለፁት።
«

« አክሚ የተባለው ቡድን እስካሁን ተጽዕኖ ካሳረፈባቸው አካባቢዎችም ውጭ በሌሎች አካባቢዎች ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህ ግን እስካሁን ስር በሰደዱባቸው አካባቢዎች፡ በተለይም፡ በሳህል አካባቢ ህልውናቸውን ማጠናከር የሚሰኘውን ስልታቸውን ይጻረራል። »
በመዲናይቱ ዳካር በሼኽ አንት ዲዩፕ ዩኒቨርሲት የእሥልምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ አብዱል አዚዝ ኬቤም ሴኔጋል የአሸባሪዎች ሰለባ የምትሆንበት ሥጋት አልተደቀነባትም ባይ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፡ የሴኔጋል ወንድማማችነት ቡድኖች ሀገሪቱን ከፅንፈኝነት ተፅዕኖ ይከላከላሉ።
«
« የወንድማማችነት ቡድኖች የፀጥታ ሁኔታዎች መስተካከልን ያመቻቻሉ። እና የተከሉዋቸው መስረቶች ሲናጉ ያኔ አክራሪ መስመር የሚከተሉ ሌሎች ቡድኖች የሚስፋፉበትን ዕድል በመፍጠር ስጋት ሊያስከትል ይችላል። ይህ እውን ከሆነ ሊከተል የሚችለውን ሁኔታ ማንም አያውቅም። »

ፖለቲካው እነዚህን ቡድኖች ለራሱ እንደመሣሪያ ለመጠቀም እስካልሞከረ ድረስ ቡድኖቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችል ኬቤ አስታውቀዋል።

ምስል DW
ምስል Reuters


ዲርከ ከፕ
አርያም ተክሌ
መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW