1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚዳንት ባይደን በአፍሪቃና አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ያደረጉት ንግግር

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 6 2015

አሜሪካ ከአፍሪቃ ጋር አዲስ አጋርነት መመስረቷን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስታወቁ። ፕሬዚዳንት ባይደን ትናንት በአፍሪቃ አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣በዩናይትድስቴትስና መኻከል ያለውን የንግድ ግንኘነት ለማጠናከር ያለመ ሥምምነት ይፋ አድርገዋል።

USA US-Afrika-Gipfel der Staats- und Regierungschefs
ምስል Evelyn Hockstein/Pool via AP/picture alliance

ፕሬዚዳንት ባይደን በአፍሪቃና አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ያደረጉት ንግግር

This browser does not support the audio element.

አሜሪካ ከአፍሪቃ ጋር አዲስ አጋርነት መመስረቷን ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን አስታወቁ። ፕሬዚዳንት ባይደን ትናንት በአፍሪቃ አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣በዩናይትድስቴትስና መኻከል ያለውን የንግድ ግንኘነት ለማጠናከር ያለመ ሥምምነት ይፋ አድርገዋል። 

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን ንግግራቸውን ሲከፍቱ፣የትናንቱ የግማሽ ፍጻሜ የዓለም ዋንጫ ከመካሄዱ በፊት የሞሮኮን ስኬት በማንሳት አፍሪቃውያን መሪዎቹን ዘና አድርገዋቸዋል።
«እዚህ ስለተገኛችሁ ሁላችሁንም ላመሰግን እወዳለሁ።በተለይ ሞሮኮ በዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የመጀመሪያ አፍሪቃዊት ሃገር ሆና ልትጫወት ነው ብያለሁ።»
ባይደን ከጉባዔው ንግግራቸው በኇላ፣አስደናቂዋ ሞሮኮ ከፈረንሳይ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ ተከታትለዋል።

አሜሪካ በአፍሪቃ ያላት ተጽእኖ ከቻይናና ሩሲያ ከፍተኛ ውድድር በተጋረጠበት በአሁኑ ወቅት፣ባይደን በንግግራቸው ለአፍሪቃ አህጉር ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ሞክረዋል።
«ዩናይትድስቴትስ ከአዲሱ የአፍሪቃ አህጉራዊ ነጻ ደንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት ጋር ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርማለች።ይህ የመግባቢያ ሰነድ በሃገሮቻችን መኻከል የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በመክፈት አፍሪቃንና አሜሪካን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ያቀራርባል።»
ፕሬዚዳንቱ ተግባራዊ እየሆነ ነው ያሉት የአፍሪቃ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና፣በዓለምላይ ካሉት ትላልቅ የነጻ ንግድ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ሰዎችን እና አህጉር አቀፍ ገበያን በድምሩ ሦስት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር እንደሚወክል ባይደን ጠቁመዋል።
ዩናይትድስቴትስ በአፍሪቃ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሁሉንም ነች ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን፣የአሁኑ መድረክ ግንኙነትን ስለመገንባትና ስለወደፊቱ የጋራ ሁኔታ ለመምከር እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ምስል Michael Reynolds/Pool via CNP/picture alliance

የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ጉባኤ

«ይህ መድረክ ግንኙነቶችን ስለመገንባት፣ስምምነቶችን ስለመፈጸም ነው።ከሁሉም በላይ ስለወደፊቱ የእኛ የጋራ የወደፊት ሁኔታ ነው።ለአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም የተሻለ ዕድል ለማረጋገጥ የአፍሪቃ ስኬት እና ብልጽግና አስፈላጊ መሆኑን ከረጂም ጊዜ በፊት እናውቃለን።»

በአሜሪካው ሞርጋን ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም ዓቀፍ ትምህርት ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያም አፍሪቃ ለአሜሪካ ኤኮኖሚ የምታበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የባይደን የትናንትናው ንግግር፣ትልቅ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ተስፋዎችን በማካተት፣አሜሪካ ለአፍሪቃ ያላትን ድጋፍ ለማጉላት ረጂም መንገድ ይሄዳል።
ይሁንና፣ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በአፍሪካ ኤች አይ ቪን ለመከላከል ለመከላከል የነደፉት ፔፕፋር፣ወይም ባራክ ኦባማ በፓወር አፍሪቃ ያደረጉትን ዓይነት፣ አበረታች ተነሳሽነት አለማካተቱን የፖለቲካና አለም ዓቀፍ ግንኙነት ተንታኞች ያነሳሉ።

የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና ሽሚያ
ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪቃሃገሮች የምጣኔ ሃብት ዕድገታቸውን ለማሳለጥ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን የንግድ እንቅስቃሴ መሻሻልን በከፍተኛ ሁኔታ ያዩታል።
የሰሞኑ ጉባዔ ያስገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ውጤት መኻከልም፣እንደ ጎርጎሮሳውያን ጊዜ አቆጣጠር በ2025 የሚያበቃውንየአሜሪካን የአፍሪቃ የዕድገትና ዕድል ሕግ(አጎዋ) ዘመን እንዲታደስ ብሎም እንዲስፋፋ ጥያቄ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታ መፍጠሩ ነው።
ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የአሜሪካን ገበያ ከሚያስገኘው የአጎዋ ዕድል መታገዷ ይታወቃል።

በፕሬዚዳንት ባይደን ግብዣ በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በተጓዳኝ በሚያደርጓቸው ውይይቶች፣ይኸው የአሜሪካ ገበያ ተደራሽነት ላይ ውይይት ሊደረግበት እንደሚችል ይጠበቃል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW