1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን በድጋሚ ለምርጫ የመወዳደር አንድምታ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2015

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን በድጋሚ ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን አብዛኛዎቹ አሜሪካኖች እንደማይደግፉት ተገለጸ። እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ2024፣ ለሚካሄደዉ የዩናይትድስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ባይደን ሪፐብሊካን ፓርቲውን እንደሚወክሉ ከሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የመቅረባቸው ዕድል ከፍተኛ ሆኗል።

USA, Accokeek | Präsident Joe Biden
ምስል Patrick Semansky/AP/picture alliance

ከብዙዎች ድጋፍ አላገኙም

This browser does not support the audio element.

ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን በድጋሚ ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸውን አብዛኛዎቹ አሜሪካኖች እንደማይደግፉት ተገለጸ።

እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ2024፣ ለሚካሄደዉ የዩናይትድስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ባይደን ሪፐብሊካን ፓርቲውን እንደሚወክሉ ከሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የመቅረባቸው ዕድል ከፍተኛ ሆኗል።

በሃገሩ ልማድ መሠረት፣ ፕሬዝደንት ባይደን አስቀድሞ በተቀረጸና ትናንት ይፋ ባደረጉት የቪዲዮ መልዕክታቸው፣ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ አስታውቀዋል።

በእስካሁኑ የፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው አሳካሁት ያሏቸውን የሥራ ውጤቶች በአብዛኛው የገለጹበት ይኸው መልዕክታቸው፣ለምርጫ ዘመቻ የሚውል የገንዘብ ማሰባሰብያ መጠየቂያም ጭምር ነው።

ባይደን በመጀመሪያው ዙር የጀመሯቸውን ስራዎች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የሥልጣን ዘመን እንደሚያስፈልጋቸው ይጠይቁ እንጂ፣አብዛኛዎቹ አሜሪካኖች ግን አልተዋጠላቸውም።

ኤን ቢ ሲ ኒውስ የተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየ መሰረት፣ 70 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካዊያን፣ፕሬዚዳንት ባይደን ለሌላ ዙር ምርጫ መቅረባቸውን አይቀበሉትም።

እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ እንደምክንያት የሚያቀርቡትም፣የ80 ዓመቱ አዛውንት ባይደን ለፕሬዚዳንትነት ዕድሜያቸው መግፋቱን ነው።

እሳቸው ግን የአሜሪካንን ስርዓተ መንግስት ጠንቅቄ የማውቅ በመሆኔ፣ለስራው አሁንም ተገቢ ሰው እኔው ነኝ ባይ ናቸው።"አሜሪካንን አውቃታለኹ፣ለዛም ነው በድጋሚ የምወዳደረው።"በርግጥም፣ጆሴፍ ባይደን ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣እንዲሁም በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት(ሴኔት) እንደራሴነት ለአራት አስርት ዓመታት የካበተ ልምድ አላቸው።

የቅርብ ደጋፊዎቻቸውም፣ ከዚህ ረጅም ልምድ ጋር ያላቸው የዕድሜ ፀጋ ሃገሪቱን በጥበብ እንዲመሩ ይረዳቸዋል ሲሉ ይሞግታሉ። "ሁለቱም ዕጩዎች ዕድሜያቸው የገፋ እንደሆኑ አስባለሁ፤ይኹን። ጥበቡ ከዕድሜ ጋር ይመጣል ብዬ አስባለሁ።" ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን፣ዶናልድ ትራምፕ የሃገሪቱ ስጋት እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ። እናም ሌላኛው ለድጋሚ ምርጫ ያነሳሳቸው፣ሪፐብሊካን ፓርቲውን የሚወክሉት ትራምፕን በምርጫው ለመርታት ስለሚችሉ እንደሆነ በዴሞክራቲክ ፓርቲያቸውም ስለታመነበት እንደሆነ ይነገራል። ኒውዮርክ ውስጥ በበርካታ ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያለው ዶናልድ ትራምፕ እንደዚሁ፣ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በድጋሚ መቅረባቸው በብዙ አሜሪካውያን የሚወደድ አይደለም።

ይሁንና፣በሪፐብሊካን ፓርቲው በኩል ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ከፊት ያሉት ትራምፕ በመሆናቸው፣ባይደን ከትራምፕ ጋር ቀርበው የ2020ው ውድድር እንደገና የመካሄድ ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር፣ ማቲው ዊልሰን የሚሉት ይህንኑ ነው።

"የምርጫ አስተያየት መለኪያዎች በግልጽ የሚያሳዩት፣አሜሪካኖች ከትራምፕና ባይደን ሌላ ዕጩ እንደሚመርጡ ነው።አኛ ግን ያንን እንደገና ለማየት በሚያስችል መንገድ ላይ ያለን ይመስለኛል።"

ባይደንና ትራምፕ፣እንደገና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መቅረባቸው፣በርካታ መራጮችን በምርጫው ፍላጎት እንዳይኖራቸው ያደርጋል የሚል ስጋት ከወዲሁ አሳድሯል።

ባይደንና የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው፣ ፕሬዚዳንቱ በግዙፍ የመሰረተ ልማት፣ የአየር ንብረትና ጤና ክብካቤ ያወጧቸው ሕጎች፣በዳግም ምርጫው ወቅት የጀርባ አጥንት ሁኖ እንደሚያገለግል ይተማመናሉ።

ጠንካራ የስራ ገበያ መኖሩ፣ ፕሬዘደንቱ በኮቪድ ወረርሺኝ መከላከልና በዩክሬኑ ጦርነት ያሳዩት ጠንካራ አመራር በድጋሚ ሊያስመርጣቸው እንደሚችልም ያስረዳሉ።

ይሁንና በአሜሪካ ከፍተኛ ዋጋ ግሽበት መኖሩና ምጣኔ ሃብቱም መቀዛቀዙ ባይደን አሁን ካላቸው ዝቅተኛ ይሁንታ ድምጽ ጋር ተዳምሮ በምርጫው ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ስጋት አላቸው።

በመጀመሪያ ደረጃ በሚካኼደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም በዴሞክራቲክ ፓርቲው በኩል፣ባይደንን ለመግጠም ሁለት ዕጩዎች እንዳሉ ታውቋል። በሪፐብሊካን ፓርቲው በኩል፣ለጊዜው የምረጡኝ ዘመቻ የጀመሩት ትራምፕ እየመሩ ይሁን እንጂ የፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎቹ ብዛት እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል። በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር ኒኪ ሔይሊ፣ምርጫውን መቀላቀላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ወግ አጥባቂው የፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ሃገረ ገዢ፣ ሮን ዲሳንቲስም ወደ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሌሎች በርካቶች ደግሞ ገና እያሰቡበት እንደሆነ ተጠቁሟል።

ታሪኩ ኃይሉ 

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW