ፕሬዚዳንቷ እና የሰላም ሚኒስትሩ ያስተላለፉት ጠንካራ መልእክት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2016ፖለቲካ ኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ታየ ደንደአ ታዬ የአማራ ክልል ጦርነት የተቃዉሞ ሰልፍ አዲስ አበባ ጦርነት ይቁም
ከኢትዮጵያዊ ማንነት ይልቅ የብሔር ማንነት በላቀ እየጎላ መሄድ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ርእሠ ብሔር ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ በጅግጅጋ ፣ አዲስ አበባ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ በመንግሥት መከልከሉ ደግሞ አደገኛ እርምጃ መሆኑ የሰላም ሚኒስትር ድኤታ ታዬ ደንደአ በአደባባይ ከሰሞኑ መነገራቸው ትኩረት የሳቡ የፖለቲካ ጉዳዮች ሆነዋል።
ሁለቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በየፊናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ አንድነት በብሔር ማንነት ላይ መሸፈኑ የፈጠረው አደጋ መቀረፍ ያለበት መሆኑንና ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር የከፈሉት መስዋእት እየተጣሱ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ርእሠ ብሔር ሳህለ ወርቅም ይሁን የመንግሥት ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ታዬ አሳሳቢ ያሉትን የሀገሪቱን ሁኔታ በዝርዝር በመግለጽ እርምት መጠየቃቸው "አዲስ የማይታወቅ ችግር የተናገሩበት ባይሆንም"ችግሮች እንዲታረሙ በድፍረት መጠየቃቸው ግን የሚያስመሰግናቸው ብሎም የሕዝቡን ችግር የተጋሩበት መሆኑን ስለማንፀባረቁ ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልፀዋል።
አንደኛው ያነጋገርናቸው ሰው የፕሬዝዳንቷ ንግግር ሰሚ አግኝቶ ተግባራዊ ይሆናል ወይ የሚለው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ሲገልፁ ፣ ሌላኛው ደግሞ የሰላም ሚኒስትር ድኤታ መንግሥትን ወቃሽ ከሆኑ ማን እርምቱን ይውሰድ የሚለውን ግራ አጋቢ ያደርገዋል ብለዋል።
ብሔራዊ ማንነት ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጥያቄ መቅረቡ
ርእሠ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጅግጅጋ ላይ በተከበረው 18 ኛው የብሔር ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን ለተደራራቢ ፈተና መጋለጣቸውን፣ ጦርነትን ጨምሮ በአስከፊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ፣ ከምንም ብቻ ላይ ብሔራዊ ማንነት ወደ ኋላ እየተተወ የብሔር እና የጎሳ ማነነቶች ቅድሚያ ቦታ ያላቸው የመሆኑ አዝማሚያ አሳሳቢ እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
"የእርስ በርስ ጦርነት፣ የከፉ ግጭቶች፣ የፀጥታ መደፍረስን፣ የሚሊዮኖች መፈናቀልን፣ የንፁሃን ደም በከንቱ መፍሰስን፣ የሴቶች መደፈርን፣ የትምህርት መቋረጥን፣ ድርቅን፣ የምግብ እጦትን ወዘተ በአጭሩ የጦርነትን አስከፊ ገፅታ በሕዝቦች፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈራረቅ አይተናል፣ እያየንም ነው" በዘገባው ሀሳባቸው እንጂ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እንድ የአለምአቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የፕሬዝዳንቷ ብርቱ መልእክት ቢሆንም ሰምቶ የሚተገብረው ካለ ጥሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የሰላም ሚኒስትር ባለሥልጣን የመንግሥታቸው ወቃሽነት
"ጦርነትን መቃወም አትችሉም" ለምን? ሲሉ ሕዝብ የሚጠይቀውን ጥያቄ መልሰው የጠየቁትና መንግሥት በአዲስ አበባ ሊደረግ የነበረን ሰላማዊ ሰልፍ ያወገዙት የሰላም ሚኒስትሩ ታዬ ደንደአ ይህንን ማድረግ "ያልሸፈቱት እንዲሸፍቱና የሸፈቱት ወደ ሰላም እንዳይመለሱ ማለትም ሊሆን ይችላል" ሲሉ በሥራ አስፈፃሚነት የሚያገለግሉትን መንግስታቸውን ክፉኛ ነቅፈዋል። ያነጋገርናቸው ተንታኝም መልእክቱ አዲስ ባይሆንም የባለስልጣኑ ግልጽነት ግን የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"ሰላምን የሚጠላዉ ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ መንግስት ነዉ" በሚል ብንከሰስ መልሳችን ምን ይሆናል? ሲሉ የጠየቁት አቶ ታዬ መንግሥታቸው "ትልቅ ታሪካዊ ስህተት" መፈፀሙን ገልፀዋል። "ፀረ-ሰላም እርምጃ የወሰድን ይመስለኛል" ሲሉም አክለዋል። እሳቸው ይህንን ካሉ ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው የሚለው ደግሞ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያ ጥያቄ ነው።
ሁለቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ሰሞነኛ ብርቱ የመንግሥትን የአካሄድ መሻሻል የሚጠይቁ መልእክቶች ጥቅል እንደምታን ያነጋገርናቸው ተንታኝ ገልፀዋል።
የርእሠ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የጅግጅጋው ጠንካራ መልእክታቸው በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት ካቀረቡት ንግግር የበረታና በዝርዝር ችግሮችን ያሳየ ሲሆን አቶ ታየ ደንደአ መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጀምሮት የነበረው ድርድር ያለ ውጤት ሲበተን ተጠያቂ ያደረጉት መንግሥትን ነው። በአማራ ክልል ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ቅድመ ግምገማ ቢኖርም የሚመለከተው ያሉት አካል ፈጥኖ እርንጃ ባለመወሰዱ አውዳሚ ጦርነቱ መከሰቱን የተናገሩት ከሰሞኑ ነው።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ