ርእሠ ብሔር ታዬ መንግሥት ስለሚከተላቸው አቅጣጫዎች የሰጡት ገለፃ
ማክሰኞ፣ መስከረም 26 2019
ትናንት ሥራውን በይፋ የጀመረው ተመራጩ መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያፀና ሥራ እንደሚከውን ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባን ዛሬ ማክሰኞ ያስጀመሩት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር አዳዲስ አሠራሮችን እና አደረጃጀቶችን እንደሚከተል ጠቁመዋል።
መንግሥት ሰላምን፣ ሕብረትን፣ ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ኃላፊነት ይወጣል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነውጥ፣ ዐመፅ እና አንባጎሮ ይታይበታል ያሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሻሻል መዋቅራዊ ሽግግሮች ይደረጋሉ ብለዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የምክር ቤቶቹ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ዘርዝረዋል። የሕዝብን ሰላምና ደኅነትን ማፅናት አንዱ መሆኑንም በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል።
"መልካም አስተዳደርን የሚያዘምን፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ የኑሮ ውድነትን የሚገራ....የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚያፀና ሊሆን ይገባዋል።"
መንግሥት "የኢትዮጵያን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅላቅ ያሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን" የተናገሩት ርእሠ ብሔር ታዬ የሀገራዊ ምክክር ሥራን ለዚሁ ማሳያ አቅርበዋል።
"የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን፣ ለሕዝብ የተገዛ እንዲሁም ስክነትን የጋራ ሃብቱ ያደረገ እንዲሆን ያስቻለ ክዋኔ ነው።"
ፕሬዝዳንቱ የሀገሪቱን የ2019 የትኩረት አቅጣጫ ሲዘረዝሩ "አዳዲስ አሠራሮች እና አደረጃጀቶችን የመከተል" አስፈላጊነትን እና "ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር" ያሉትን ጉዳይ ማምጣት ይገኝበታል ብለዋል።
"ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሕብረትን፣ ትብብርን እና ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ተግባር የሚከናወን ይሆናል።"
ሌላው ፕሬዝዳንቱ የቀጣይ ትኩረት ነው ብለው ያስቀመጡት የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት የተመለከተው ሥራ ነው።
"የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ከተቀባይነት ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያሻግር ወዳጆችን በማበራከት የሚተጋ" እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ መንግሥት እነዚህን ሥራዎች ለመተግበርይከተላቸዋል ካሏቸው መንገዶች አንዱ "የጠብመንጃ ባሕል እና የነፍጥ አዙሪት" መገለጫው ነው ያሉት የኢትዮጵያ የተለምዶ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ውርስን በዘላቂነት ማስቀረት ይገኝበታል።
ርእሠ ብሔር ታዬ ባለፈው ዓመት የሁለቱን ምክር ቤቶች ሲከፍቱ የኢትዮጵያ መንግሥት "የእርቅ እና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገሪቱን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሠራ" መሆኑን፣ "በየቦታው የሚታዩ" ያሏቸው "ግጭቶችን በኃይል ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም" መንግሥት ዘላቂ ሰላም የሚረጋግጠው በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ ያምናል" ብለው ነበር።
ዛሬ የጋራ ምክር ቤቱን በሚከፍቱበት ወቅት ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ጦርነት ውስጥ ትገኛለች። ሀገሪቱ ከገጠማት የውስጥ የፀጥታና ደኅንነት ችግር ባለፈ በተለይ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ መካረር ውስጥ መግባቷ በሀገራት እና ተቋማት ዘንድ ሥጋት አጭሯል።
ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል ተብሎ አቅጣጫ የተያዘበትን የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ለማሳካት ግን ሰላማዊ መንገዶችን እንደምትከተል ተደጋግሞ ተገልጿል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ