ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በቀጣዩ የጅቡቲ ምርጫ ይወዳደራሉ? “ይህን አልመልስም”
ቅዳሜ፣ ግንቦት 16 2017
ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ በሚያዝያ 2018 በሚካሔደው የጅቡቲ ምርጫ ሊወዳደሩ እንደሚችሉ በገደምዳሜ ፍንጭ ሰጡ። የ77 ዓመቱ ጉሌሕ መቀመጫውን በፈረንሳይ ፓሪስ ካደረገው አፍሪካ ሪፖርት የተባለ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ጉሌሕ በምርጫው በዕጩነት እንደሚቀርቡ በይፋ አላረጋገጡም።
ይሁንና በሚያዝያ 2018 በሚካሔደው የጅቡቲ ምርጫ በዕጩነት ይቀርቡ እንደሁ በአፍሪካ ሪፖርት ተጠይቀው “ይህን አልመልስም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሀገራቸውን “በግዴለሽነት ወደ አደገኛ ምዕራፍ” መምራትም ይሁን “ክፍፍል መዝራት” እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ ለስድስተኛ የሥልጣን ዘመን በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ዕድሜው ከ75 ዓመት በላይ የሆነ ዕጩ የሚያግደውን የጅቡቲ ሕገ-መንግሥት ማሻሻል ወይም መቀየር ያስፈልጋቸዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት በተካሔደው የጅቡቲ ምርጫ ከተሰጡ ድምጾች ጉሌሕ 97 በመቶውን ያገኙ ሲሆን ፓርቲያቸውም በሀገሪቱ ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ይዟል።
ጉሌሕ በጎርጎሮሳዊው 1999 ሥልጣን የያዙት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን በመተካት ነበር። ኦፕቲዶን በ1977 ጅቡቲ ከፈረንሳይ ቅኝ ገዢነት እንድትወጣ የመሩ ናቸው። ሐሰን ጉሌድ ኦፕቲዶን ለ22 ዓመታት ጅቡቲን ሲመሩ ኢስማኤል ዑመር ጉሌሕ የጽህፈት ቤታቸው ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ጅቡቲ መረጋጋት በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የተሻለ ሰላም ያላት ትንሽ ሀገር ብትሆንም በጂዖግራፊያዊ አቀማመጧ ስልታዊነት የልዕለ ኃያላን የጦር ሠፈሮች የሚገኙባት ናት። ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና በጅቡቲ የጦር ሠፈር ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ከኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የምትዋሰነው ጅቡቲ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ሲኖሯት በአፍሪካ አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ሀገራት መካከል ነች።