1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በ75 ዓመታቸው አረፉ

ማክሰኞ፣ መስከረም 7 2017

ይህንን ጉዳይ ቀድመው ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ" በማለት ሐዘናቸውን ገልፀዋል።

ዕዉቁ የባዮሎጂ ሊቅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተለዩ ስሞች የሚጠሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሕብረቶችን ለረጅም ጊዜ መርተዋል
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ (ከግራ ወደቀኝ የመጀመሪያዉ) ሥለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ባንድ ወቅት መግሎ,ጫ ሲሰጡምስል DW/G. Tedla

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በ75 ዓመታቸው አረፉ

This browser does not support the audio element.

 

አንጋፋው መምህር እና ፖለቲካኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዛሬ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ. ም በሕመም ምክንያት አረፉ።

ይህንን ጉዳይ ቀድመው ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ" በማለት ሐዘናቸውን ገልፀዋል። 

ፕሮፌሰር በየነ ሲመሩት የቆዩት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌ፤ የትግል አጋራቸው "ጽኑ እና ተዓማኒ" ያሉትን ትግል ስለማድረጋቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። "ለአጭር ጊዜ" ታመው ለተሻለ ሕክምና ወደ ኬንያ ተወስደው የነበረ ቢሆንም በዚያው በናይሮቢ ሕይወታቸው ማለፉንም ዶክተር ራሔል ገልፀዋል።

ፕሮፌሰር በየነን ለ35 ዓመታት እንደሚያውቋቸው የነገሩን ሌላኛው አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ፕሮፌሰር በየነን ኢትዮጵያን ያገለገሉ "የሰላማዊ ትግል አርበኛ" ነበሩ ሲሉ ገልፀዋቸዋል።//

ስለ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በጥቂቱ 

"ስለ ኢትዮጵያ መቼም በእኛ በኩል የምንሰስተው፣ የማንሆነው፣ የማናደርገው አይኖርም"። 

ይህን ያሉት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ።

በ 1942 ዓ. ም በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ሃድያ፤ ሾኔ ከተማ አቅራቢያ የተወለዱት መምህርና ፖለቲከኛው ሰው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አካባቢ ያጠናቀቁ ሲሆን የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ መካነ አዕምሮ በሥነ ሕይወት አጠናቀው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካን ሀገር ተምረው ተመርቀዋል።

ከ 1978 እስከ 1982 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ፕሮፌሰር በየነ በ1983 ወደ "ተግባራዊ ፖለቲካ" መግባታቸውን እና የሽግግር መንግሥቱ አባል እንደነበሩ፣ አልፎም በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር ድኤታ ሆነው ለጥቂት ጊዜ ማገልገላቸው ይነገራል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ (ከግራ ወደ ቀኝ የመጀመሪያዉ) መድረክ የተባለዉን የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ሕብረት በሚመሩበት ወቅትምስል DW/G. Tedla

ኢሕአዴግ በ1983 ባዘጋጀው የሰላምና ዴሞክራሲ ጉባኤ (የቻርተር ጉባኤ) ላይ መሳተፋቸውን እና ኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለማንበር ቃል መገባቱ ትኩረታቸውን ስቦ እንደነበር ባንድ ወቅት ለሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የገለፁት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ "ኢትዮጵያዊነት በዋዛ የሚታይ አይደለም" በሚለው እምነታቸውም ይታወቃሉ። ለዚህም ሲባል የረጅም ጊዜ ትግል እና የፖለቲካ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንም ይገልፁ ነበር። ፕሮፌሰር በየነ ሲመሩት የቆዩት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌ የትግል አጋራቸው "ጽኑ እና ተዓማኒ" ያሉትን ትግል አድርገዋል ሲሉ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

"ፕሮፌሰር በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ፖለቲካ ውስጥ ሰላማዊ ትግሉን በተግባር መሬት ላይ ለማውረድ የቻሉ መሪ ናቸው። ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሚነሳበት ሁሉ የመጀመርያው ምልክት ነቸው፤ ለሀገሪቱ"። 

የሕዝብ ውክልና እና አገልግሎት

በ 1992ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሾኔን ሕዝብ በመወከል የፓርላማ አባል ሆነው ያገለገሉት እኒሁ መምህር እና አንጋፋ ፖለቲከኛ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤቶች መካከል "የፕራይቬታይዜዥን" አማካሪ ምክር ቤት አባል ሆነው ሰርተዋል፣ ከጳግሜን 4 ቀን 2012 ዓ. ም ጀምሮ ደግሞ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተሹመው በኋላም የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲሠሩ ቆይተዋል።

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለረጅም ጊዜ በመምሕርና ተመራማሪነት ያገለገሉት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነዉምስል Addis Ababa University/Ethiopia

ፕሮፌሰር በየነን ለ35 ዓመታት እንደሚያውቋቸው የነገሩን ሌላኛው አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ፕሮፌሰር በየነን ኢትዮጵያን ያገለገሉ "የሰላማዊ ትግል አርበኛ" ነበሩ ሲሉ ገልፀዋቸዋል

ፕሮፌሰር በየነ በኢትዮጵያ ለሚታዩ የወቅቱ የሰላም መደፍረሶች ምክንያቱ በተለያየ ወቅት በመንግሥት ለሥራ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የተዘዋወሩ ዜጎች በመንግሥት በቂ ጥበቃ አለመደረጉ፣ የሀብት ሽሚያ እና መሬትን የእኔ ብቻ የሚል አመለካከት መሆኑንም በቅርቡ ገልጸው ነበር። ዴሞክራሲያዊ የውሳኔ አሰጣጥ በሀገሪቱ ከተቃኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ "የሚጋጭበት፣ ችግር ውስጥ የሚወድቅበት ምክንያት አይኖርም" ሲሉም ይከራከሩ ነበር።

"ይህችን ሀገር የሚያድናት ዴሞክራሲ ነው። ከዴሞክራሲም መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ነው"።

ፕሮፌሰር በየነ ሲመሩት የነበረው የፒሊሲ ጥናት ተቋም በግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ሀገራዊ ይዘት ያለው ጥናቶችን ለማካሄድ መቸገሩን፣ በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ ዙሪያ በተደረገ ጥናት ማሻሻያ እንዲደረግ ፍላጎት መኖሩን አመልክቶ ነበር።

ለሦስት እና አራት ቀናት "ለአጭር ጊዜ" ታመው እንደነበር እና ለተሻለ ሕክምና ወደ ኬንያ በተወሰዱበት እዚያው ናይሮቢ ማረፋቸውንም ለማወቅ ችለናል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW