1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሃም» ከጎጃምዋ የትመን እስከ ጀርመንዋ ላይፕሲሽ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2016

የዛሬ 34 ዓመት የውጭ ትምሕርት እድል አግኝተው በመጡባት በምሥራቅ ጀርመንዋ ከተማ ላይፕሲሽ በአካዳሚው ዘርፍም ሆነ በከተማ ማዘጋጃ ቤት ለከፍተኛ ሃላፊነት የበቁት ፕሮፌሰር ጌቱ መነሻቸውን የትመንን አልረሱም። ኢትዮጵያ የተማሩበትን የየትመን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚደግፍ ፕሮጀክት በማስጀመር ለትምሕርት ቤቱ ልዩ ልዩ እገዛዎችን አድርገዋል ።

ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀም የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ (SPD)ና የላይፕሲሽ ከተማ ምክር ቤት አባል
ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀም የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ (SPD)ና የላይፕሲሽ ከተማ ምክር ቤት አባል ምስል Prof. Dr. Getu Abraham

ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሃም፤ ከጎጃምዋ የትመን እስከ ጀርመንዋ ላይፕሲሽ

This browser does not support the audio element.

የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ከ30 ዓመት በላይ ጀርመን የኖሩትን የእንሰሳት ሕክምና ተመራማሪ እንዲሁም የምሥራቅ ጀርመንዋ የላይፕሲሽ ከተማ ምክር ቤት አባል ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሃምን ያስተዋውቀናል።የዛሬ 34 ዓመት በእንሰሳት ሕክምና የከፍተኛ ትምሕርት እድል አጝኝተው በመጡበት በጀርመን ላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ በተመራማሪነትና በመምሕርነት የሚያገለግሉት ኢትዮጵያዊ ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀም አሁን በሚሰሩበት በላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ ብቻ አልተወሰኑም። የከተማዋ ምክር ቤት አባልም ናቸው። ከ27 ዓመት የላይፕሲሽ ቆይታ በኋላ ነበር በከተማዋ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ውስጥ ለመሳተፍ ፈቅደው ጉዞውን የጀመሩት። ከዚያ በኋላ ነው በምክር ቤት የህዝብ ድምጽ ለመሆን እድል ያገኙት። ፕሮፌሰር ጌቱ ጊዜ ከሚፈልገው የዩኒቨርስቲው ስራቸው ጎን ለጎን ይህን ሃላፊነት ጨምረው ለመስራት የመረጡበት ምክንያት አላቸው።አንጋፋዋ የፋርማሲ ዶክተር ጠረፈወርቅ አሰግድ ሹቨ

ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀም (SPD) በላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ በስራ ላይ ሳሉ ምስል Prof. Dr. Getu Abraham

 ፕሮፌሰር ጌቱ ለምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር ሲያስቡ በቅርብ ከሚያውቋቸው ጥቂት ሰዎች በስተቀር  ባለቤታቸውን ጨምሮ ብዙዎች አትልፋ የሚል  ዓይነት አስተያየት ነበር የሰጧቸው ። እሳቸውም በጥቂቱም ቢሆን ማሸነፍ መቻል አለመቻላቸውን መጠራጠራቸው አልቀረም። ሆኖም ያ አልፎ አንዴም ብቻ ሳይሆን ሁለቴ ለመመረጥ መብቃታቸው ከምንም በላይ ጀርመናውያን የሚሰጧቸው በጎ አስተያየቶች ያሰቡትን ለማሳካት የበለጠ ጉልበት ሆኗቸዋል። ፕሮፌሰር ጌቱ የተወለዱት በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ የትመን በምትባል  አነስተኛ የገጠር ከተማ ነው። የያኔው ታዳጊ ጌቱ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርቱን በየትመን አጠናቆ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ደግሞ በከፊል እዚያው ጎጃም ብቸና ተማረ። የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰደው ደግሞ ጎጃም ደብረማርቆስ ነበር ።ከዚያም ደብረ ዘይት የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ በተከታተለው የረዳት የእንሰሳት ህክምና ሙያ በዲፕሎም የጨረሰው ወጣቱ ጌቱ ትምሕርቱን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቁ እዚያው ኮሌጅ 2 ዓመት በመምህርነት ሰራ።ወጣቱ ኤርትራዊ የአውቶብስ ሾፌር በቦን

ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀም ለምርጫ ዘመቻ ከተለጠፈው ፖስተራቸው ጋር ምስል Prof. Dr. Getu Abraham

የዛሬ 34 ዓመት ደግሞ የውጭ ትምሕርት እድል አግኝተው በመጡባት በምሥራቅ ጀርመንዋ የላይፕሲሽ ከተማ በአካዳሚው ዘርፍም ሆነ በከተማ ማዘጋጃ ቤት ለከፍተኛ ሃላፊነት የበቁት ፕሮፌሰር ጌቱ መነሻቸውን የትመንን አልረሱም ። ኢትዮጵያ እያሉ የተማሩበትን የየትመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚደግፍ ፕሮጀክት በማስጀመር ለትምሕርት ቤቱን ልዩ ልዩ እገዛዎችን አድርጓል ። 
በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት የተዋወቋቸው ከዚህ ቀደም የዚህ ዝግጅት እንግዳ የነበሩትና ለተማሩበት ትምሕርት ቤት  ተመሳሳይ ድጋፍ ይሰጡ የነበሩት የኮሎኙ ነዋሪ እርዳው ነጋሽ ሚኮ የፕሮፌሰር ጌቱን ስራ ከሚያደንቁት ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው ። ይርዳው እንዳሉት የፕሮፌሰር ጌቱ በላይፕሲሽ ከተማ ምክር ቤት አባል ሆኖም ለውጭ ዜጎች ብዙ የሚያስተምር የውጭ ዜጎችንም የሚያስከብር ተግባር ነው።እርዳው ነጋሽ ሚኮ፤ ከኢትዮጵያዋ «መንጅክሶ ጸዴ» እስከ ጀርመንዋ ኮሎኝ

 

ፕሮፌሰር ጌቱ በፕሮጀክታቸው ከሚረዱ የየትመን አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር ምስል Prof. Dr. Getu Abraham


ፕሮፌሰር ጌቱና ሌሎች በየትመኑ  የትምህርቱ  ፕሮጀክት የሚሳተፉ ሰዎች በሚሰጡት ድጋፍ በርካታ ወላጆቻቸውን ያጡ እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የመጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታታል እንዲሁም ከፍ ያሉ ደረጃዎች ላይ ለመድረስ በቅተዋል። ከመካከላቸው  በቅርቡ በፋርማሲ ትምሕርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘውና ስራም የያዘው ስለሺ ስመኘው አንዱ ነው።  
 

ፕሮፌሰር ዶክተር ጌቱ የማራቶን ውድድር ጨርሰው ያጠለቁት ሜዳልያምስል Prof. Dr. Getu Abraham

የ57 ዓመቱ ጎልማሳ የላይፕሲሽ ከተማ ምክር አባል ፕሮፌሰር  ጌቱ አብርሃም  ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ናቸው።በትርፍ ጊዜያቸውም ማራቶን በመሮጥ ይታወቃሉ። የእንሰሳት ህክምና ምሁርና ተመራማሪ እንዲሁም የላይፕሲሽ ምክር ቤት አባል ፕሮፌሰር ጌቱ አብርሀምን ያስተዋወቃችሁ የዛሬው ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል። ሙሉውን ዝግጅት የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያዳምጡ። አስተያየቶቻችሁንም ላኩልን

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW