በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ
ሐሙስ፣ መጋቢት 4 2017
በትግራይ ክልል ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ ዳግም ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል። ዛሬ በመቐለ በርካታ ነዋሪዎች ከባንክ ገንዘብ ያወጣሉ፣ ሸቀጦች ይገዛሉ። አንዳንድ ባንኮች አንድ ደንበኛ በቀን ሊያወጣው የሚችል የጥሬ ብር መጠን ወደ 5 ሺህ ብር እንዲቀንስ ያደረጉ ሲሆን፥ ለምግብነት በሚያገለግሉ ሸቀጣች ላይም የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ በመቐለ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በነበረ ሁኔታ ከሦስት ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተዘግቶ የቆየው የመቐለ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተከፍቶ በዶክተር ደብረፅዮን ቡድን ለከተማዋ በከንቲባነት የተሾሙት ዶክተር ረዳኢ በርሀ ሥራ ጀምረዋል። የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ፥ የዶክተር ደብረፅዮን የህወሓት ቡድን እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በየፊናቸው ከንቲባ መመደባቸው ተከትሎ በሁለት ከንቲቦች ውዝግብ አንድ መቶ ቀናት ያክል ተዘግቶ እንደነበረ ይታወሳል። ዛሬ በመቐለ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በይፋ ሥራ መጀመራቸውን ያወጁት የህወሓቱ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ረዳኢ በርሀ፥ ሕግና ስርዓት ተከትለን፣ በመቐለ ምክርቤት ውሳኔ መሰረት የአስተዳደር ሥራውን ተረክበናል ብለዋል።
ዶክተር ረዳኢ "በፀጥታ ኃይሎች ታጅበን የሌሎች ጥቅምና ሐሳብ ጨፍልቀን ሳይሆን ሕግና ስርዓት አክብረን፣ ከመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ንግግር ሲደረግ ቆይቶ አሁን በሰላማዊ መንገድ የመቐለ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የሓድነት ክፍለከተማ ጨምሮ ዛሬ ጉዳዩ ተጠናቋል። ይህ ነው ሂደቱ" ብለዋል።
በሌላ በኩል ዶቼቨሌ ያነጋገራቸው በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ በበኩላቸው ይህንኑ አይቀበሉም። አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ እንደሚሉት የአንድየህወሓት ቡድንአጀንዳ ለማስፈፀም እየተንቀሳቀሱ ያሉ የታጣቂዎች የመቐለ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ያሉ የመንግስት መዋቅሮች በማፍረስ፣ በሕገወጥ መንገድ ስልጣን ለሚፈልጉት አካል አሳልፈው እየሰጡ መሆኑ ይገልፃሉ። «ይህ ረዥም ርቀት እንደማያስኬድም» ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ የቆየው ፖለቲካዊ ችግር ወደ የፀጥታ አደጋ እንዳይሸጋገር ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ያነሳው ዛሬ በትግራይ ሰላምና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ስም የተሰራጨ መግለጫ፥ ይሁንና «ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቷል» ብሏል። በትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በኩል የተሰራጨው የጽሑፍ መግለጫ እንደሚለው የፌደራል መንግስቱ ወደ ትግራይ እንዲገባ "መጋበዝን" ተቃውሟል። የፌደራል መንግስቱ ወደ ትግራይ እንዲገባ መጥራት «የተለየ የኃይል ተሳትፎ መጋበዝ ነው» ሲልም መግለጫው ጨምሮ ያነሳ ሲሆን፥ «ከፌደራል መንግስት ጋር ያለውን መተማመን ከመጉዳት በዘለለ የማይጠቅም ውሳኔ ነው» በማለትም ትላንት በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የቀረበውን ሐሳብ ተችቷል።
የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግስቱ “አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ አለበት” ማለቱን ተከትሎ መግለጫ ያወጣውበዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በበኩሉ፥ «ሦስተኛ» ሲል የገለጠው « ወገን ወደ ትግራይ እንዲገባ ጥሪ መደረግ የለበትም» ብሏል። የህወሓት ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስትና የዓለም ማህበረሰብ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ድርሻቸውን ይወጡም ብሏል።
መግለጫው አያይዞም «ሶስተኛ ወገን ወደ ትግራይ እንዲገባ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ጥሪ መደረግ የለበትም» በማለት አቋሙ አስታውቋል። የህወሓቱ መግለጫ እንደሚለው "የክህደት ቡድን" እያለ የጠራው የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት የአቶ ጌታቸው ረዳ አመራር፥ «በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሶስተኛ ወገን ትግራይ ውስጥ እጁን እንዲያስገባ የሚያደርገው ጥሪ ግልፅ ብሄራዊ ክህደት እና የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ በፍፁም ተቀባይነት የለዉም» ሲል አክሏል።
ሚልዮን ኃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ