1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትአውሮጳ

ፖላንድ ድንበር ላይ የተረሱ ፣ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች

ኂሩት መለሰ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2017

ፖላንድ ድንበሯ ላይ ለአምስት ሜትር የሽቦ አጥር ከገነባች ወዲህ ስደተኞች የአጥንት መሰበር ወይም በሽቦ አጥሩ ጉዳት የሚፈጠር ከባድ ቁስል በተደጋጋሚ ይደርስባቸዋል። በዚህ ዓመት የፖላንድ ድንበር ጠባቂ ባወጣው ዘገባ ቁጥራቸው 30 ሺህ የሚጠጋ ሰስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ለመግባት ሙከራ አድርገዋል።

Polen | Flüchtlingskrise die polnische Grenzregion zu Belarus
ምስል፦ Karol Grygoruk

ፖላንድ ድንበር ላይ የተረሱ ፣ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች

This browser does not support the audio element.

ሰሜን ምሥራቅ ፖላንድ የሚገኘው የብያዋቬዮዣ ብሔራዊ ፓርክ ከአውሮጳ የመጨረሻው ጥናታዊ ደን የሚገኝበት ስፍራ ነው። አሌክሳንድራ ችርሳንቭስካ  መቀመጫውን ዋርሶ ፖላንድ ያደረገው ስደተኞችን ለመርዳት «ሕጋዊ ጣልቃ ገብነት የሚያደርገው የሰብዓዊ መብቶች ማኅበር »ሠራተኛ ናት። ከጎርጎሮሳዊው 2021 ዓም አንስቶ በፖላንድና በቤላሩስ ድንበር ላይ በሚገኘው በዚህ ጥንታዊ ደን ውስጥ በየቀኑ ትመላለሳለች። ያኔ ቤላሩስ በአውሮጳ ኅብረት ላይ ጫና ለማድረግ ከሦስተኛ ሀገር የሚመጡ ስደተኞች ፖላንድ በቀላሉ እንዲገቡ ታደርግ ነበር። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ፖላንድ ስደተኞቹን ለመግታት ድንበርዋን ማጠርና እነርሱንም  መመለስ ጀመረች። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በድንበሩ አካባቢ ሰብዓዊ ቀውሱ እየተባባሰ ሄደ። ከአችርሳንቭስካ ጋር ስደተኞች አስከፊ ሁኔታ ላይ ወደሚገኙበት የቤላሩስና የፖላንድ ድንበር የሄደችው የዶቼቬለዋ ጋዜጠኛ ናዲን ቮይቺክ እደዘገበችው ችርሳንቭስካ በሚገርም ሁኔታ በጭቃማው ደን መሀል በስልክዋ አቅጣጫ መሪነት እየተዘዋወረች ስደተኞችን ትረዳለች።   
ችርሳንቭስካ በደማቅ ቀለም ስልኳ ላይ ምልክት የተደረገበትን ካርታ ትመለከታለች ። እያንዳንዳቸው ምልክት የተደረገባቸው ስፍራዎች ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ ናቸው። ይህም ግሩፓ ግራኒሳ በተባለው የግንኙነት መረብ ፣ አክቲቪስቶች ቤላሩስን በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሚገኘው ጫካ  ሰብዓዊ ተልዕኮዎችን የሚያከናውኑበት ጣልቃ ገብነት ነው። በዋነኛነት በዚያ ለሚገኙ ስደተኞች ትኩስ ሾርባ፣ ውሐ ልብስ ጫማ እና የስልክ ቻርጀሮች ያቀርባሉ። ብዙውን ጊዜ የህክምና እርዳታም ይሰጣሉ።ጠንከር ያለ ከሆነ ደግሞ ሐኪም ያግዛቸዋል።  

ባለአምስት ሜትር የብረት አጥር ፍልሰትን አያስቆምም 

ፖላንድ ድንበሯ ላይ ለአምስት ሜትር የሽቦ አጥር ከገነባች ወዲህ ስደተኞች የአጥንት መሰበር ወይም በሽቦ አጥሩ ጉዳት የሚፈጠር ከባድ ቁስል በተደጋጋሚ ይደርስባቸዋል። ችርሳንቭስካ እንደምትለው አጥሩ ሰዎችን ከመሰደድ አያስቆምም፤ ሕይወታቸው በሀገራቸው አደጋ ላይ ስለሆነ እነርሱም ከመሰደድ ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም። በጎርጎሮሳዊው 2024 ግሩፓ ግራኒሳ ወደ 5600 የአስቸኳይ ጊዜ ጥሪዎችን ተቀብሏል። ከመካከላቸው ወደ1400 ለሚሆኑት ደርሰዋል። በዚህም 3400 ሰዎችን ረድተዋል።  ድንበር ላይ በሚገኘው በዚህ ጫካ ውስጥ የሶሪያ ፣የኤርትራ የሱዳን የሶማሊያ እና የአፍጋኒስታን ስደተኞች አሉ። በዚሁ ዓመት የፖላንድ ድንበር ጠባቂ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ቁጥራቸው 30 ሺህ የሚጠጋ ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው ለመግባት ሙከራ አድርገዋል። የአውሮፓ ኅብረት የድንበር ተቆጣጣሪ ፍሮንቴክስ እንደዘገበው በ2024 ዓመት ምኅረት በምሥራቅ አቅጣጫ በቤላሩስ በኩል የሚካሄድ ፍልሰት በሚባለው መስመር የሚሰደዱት ቁጥር በ200 ፐርሰንት አድጓል።  

ስደተኞች መፈናፈን ያልቻሉበት የፖላንድ ጫካ ምስል፦ Karol Grygoruk

ስደተኞች ለአስቸኳይ ሁኔታዎች በተዘጋጁ ስልኮች እርዳታ ይጠይቃሉ

ጋዜጠኛ ናዲን ስደተኞችን ከምትረዳው ከችርሳንቭስካ ጋር ወደ ጫካው በተጓዘችበት  ቀን አሌክሳንድራ ስደተኞችንለመርዳት ስትንቀሳቀስ  እግረ መንገድዋን ከዚህ ቀደም ቡድኑ ባካሄዳቸው ጣልቃ ገብነቶች የተጣሉ እቃዎችን ትሰበስባለች። ከመካከላቸው ለሌላ እርዳታ የሚጠቅሙም ይገኙበታል።  የጫካውን ጽዳት ለመጠበቅም ስፍራውን ከቆሻሻ ነፃ ታደርጋለች። የእጅ ጓንት ቴርሙስ የተቀደደ ጃኬት የህጻናት ጫማ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ላስቲክ እና የመሳሰሉትን ትሰበስባለች። ይህን እያደረገች ስልክዋ በድንገት ጠራ ። የሚደወለው ከዋናው ካምፕ ነው። መስመሩ ጥሩ አይደለም። ከወዲያኛው ወገን በደንብ አይሰማም፤ተበሳጨች ፤ግን በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዳለ ተረድታለች። እርዳታ የሚፈልጉ ሁለት አፋጋናውያን በዓለም አቀፉ የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ ደውለዋል። ወዲያው ተለውጣ «መፍጠን አለብን» አለች። መንገድ ላይ ያገኘቻቸውን ቆሻሻዎች እንደያዘች የተተዉላትን የስልክ መልዕክቶች እያዳመጠች ወደ ዋናው ካምፕ በማምራት ላይ ሳለች ማኅበራቸው ምን እንደሚያደርግ ማስረዳት ጀመረች። 
« ሰዎች እርዳታ ከፈለጉ በአስቸኳዩ ስልክ ያገኙናል። የሚያነጋግሯቸው ሰዎችም የት እንደሚገኙ ያጣራሉ።ብዙውን ጊዜ ለነርሱ ቅርብ የሆነ ስፍራ ያለ ሰው በተቻለ ፍጥነት ሊረዳቸው ይሄዳል።  ፈጥኖ መድረስ ያለበትም በብርዱ ምክንያትና እነርሱም ደክመው ስለሚመጡ ነው። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ ስልክ የሚፈልጉትንም የምናውቅበት ነው። ብዙውን ጊዜ ምግብ ፣ትኩስ ሻይ ፣ወሐ ፣በክረምት ደግሞ ማሞቂያ ይዘንላቸው እንሄዳለን። የሚያስፈልጋቸውን ልብስ ልክና፣ የጫማ ቁጥር እንጠይቃለን። አንዳንዴም ለመተኛ የሚያገለግል የሚጠቀለል ስስ ፍራሽ እንወስድላቸዋለን። ብዙውን ጊዜ ከ 70 እስከ 90 ሊትር የሚደርስ ክብደት ያላቸውን እርዳታዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ያሉበት ቡድን አለን። እቃዎቹ በጣም ከባድ ናቸው።»  

ጫካው ውስጥ ዘልቀው የተደበቁ ስደተኞች

በስልኩ መልዕክት ላይ እንደሚሰማው ከመካከላቸው አንዱ ከባዱ ቁስል አለው።  በውሃ የራሱት አፍጋናውያን ደግሞ ደረቅ ልብስ እና ጫማ ይፈልጋሉ። የተጎዳውን ስደተኛ ቁስል የሚያሳይ ፎቶም ለምክር ለሐኪም ይላካል። ይህ እየተካሄደ በዋናው ካምፓቸው ያሉት በጎ ፈቃደኞች ለስደተኞች ያስፈልጋሉ የተባሉትን ሁሉ በትላላቅ መያዣዎች እየሸከፉ ነው። 
ጥ ባለ መንገድ በኋላም ለደኅንነታቸው ሲባል በጫካው መሀል መንጎድ ያዙ። ስደተኞቹንም መጀመሪያ ምልክት ባደረጉበት ስፍራ አገኟቸው። ከመካከላቸው ሁለቱ ራቅ ብለው ስለተደበቁ እነርሱን ማግኘት ጊዜ ወስዷል። 
እድሜያቸው በሀያዎቹ አጋማሽ የሚሆነው ወንድ ስደተኞች እንግሊዘኛ መናገር አይችሉም። በዚህ የተነሳም አክቲቪስቶቹ ስልካቸው ላይ የተጫነ የሚተረጉም መተግበሪያ በመጠቀም በፓሽቱ ቋንቋ እየተረጎሙ ጥያቄ አቀረቡላቸው። ከጥያቄዎቹ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ጫካ ውስጥ ነበራችሁ? የሚል ነበር እነርሱም በስልካቸው ላይ ጥያቄውን ጽፈው ትርጉሙን ከተረዱ በኋላ ጥቂት ሳምንታት ፤ በፖላንድ በኩል፣ ሦስት ቀናት እንደሆናቸው፤ ፖላንድ ለመግባት የቻሉትም ከሦስት ጊዜ ሙከራ በኋላ መሆኑን  በሁለቱ ሙከራዎች ተገፍተው እንደተመለሱ ተናግረዋል። ያም ማለት የተገን ማመልከቻ ቢያቀርቡም የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች  ሁለት ጊዜ መልሰዋቸዋል። ፖላንድ ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 27 ቀን 2025 ዓም አንስቶ ከቤላሩስ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የስደተኞች ተገን የመጠየቅ መብታቸውን ለጊዜው አግዳለች።  ችርሳንቭስካ እንዳለችው  እርዳታ ፈላጊዎቹ ስደተኞቹን በጫካው ራቅ ያለ ስፍራ ውስጥ ነው ያገኟቸው።

«ከግማሽ ሰዓት በላይ መጓዝ ነበረብን። በጫካው መሐል ላይ ሁለት ሰዎችን አገኘን። አንዱ በጣም ደክሞ ነበር። የእግሩ ቁስልም ወደ እግሩ ጠልቆ የገባ ነበር።መጀመሪያ ስናየው ፈርተን ነበር። ምክንያቱም ጥሩ አይመስልም ነበር። እናም መራመድ አይችልም ብለን አስበን ነበር። ሆኖም በስልክ ሐኪም አማክረን ማድረግ ያለብን ተነገረን። በቁስሉ ጥልቀት ምክንያት ምናልባትም አምቡላንስ መጥራት ነበረብን ፤ምክንያቱም ሆስፒታል ውስጥ መጽዳትና መታከም ነበረበት። ሆኖም ፖላንድ ለዓለም አቀፍ ጥበቃ ማመልከትን አግዳለች። ከአምቡላንሱ ጋር ድንበር ጠባቂዎችም ይመጣሉ። ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች  ይህን ማድረጉ በጣም አደገኛ ነው »ትላለች።

የፖላንድ ድንበር አስከባሪዎች ምስል፦ Karol Grygoruk

 ምንም እንኳን ስደተኞቹ ቢጎዱም ይህን በማድረግ ወደ ቤላሩስ ተመልሰው የመላክ እድላቸው ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ስደተኞቹ ለተወሰኑ ቀናት አልበሉም አልጠጡም።በጎ ፈቃደኞቹ ያመጡላቸውን የሽንብራ ሾርባ ፣ሻይ እና ውሀ አመስገነው ተቀብለዋል።  ስደተኞቹ እየበሉና እየጠጡ ችርሳንቭስካ ከሐኪም ጋር ምን ማድረግ እንደነበረባት መልዕክት ትለዋወጥ ነበር። ዶክተሩ አሌክሳንድራ ችርሳንቭስካ ቁስሉን እንዴት ማጽዳትና መንከባከብ እንዳለባት መመሪያ ልኮላታል።

በድንበሩ የሽቦ አጥር የሚደርሱ ጉዳቶች

ጉዳት የደረሰበት ሰው በስልኩ ላይ እንደጻፈው እግሩ የቆሰለው ከድንበሩ አጥር ላይ ሲዘል ነው። ስደተኞቹን ድንበር ጋ የሚወስዱትየቤላሩስ ወታደሮችም በጣም ኃያለኛ እንደነበሩ በጉዞ ላይም ይደበድቧቸው እንደነበር ተናግረዋል። እነርሱ እንዳሉት አምስት ሜትር ርዝመት ባለው የሽቦ አጥር ጋ መሰላል ያስቀምጡና ወደ ፖላንድ ዘለው እንዲገቡ ያስገድዷቸዋል።  

የሀገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅቶች 

አሌክሳንድራ ችርሳንቭስካ በቻለችው መጠን የስደተኛውን እግር ቁስል አጸዳች። በከባድ ህመም ላይ የነበረው ስደተኛው ጫካው ውስጥ ተዘረረ። መራመድ መቻሉን ተጠራጥራ ነበር። ሆኖም ምግብ ከበላና ውሐም ከጠጣ በኋላ በፍጥነት ተረጋጋ። 
ችርሳንቭስካ እንደተናገረችው ስደተኞቹን መጀመሪያ ሲቀርቧቸው ይፈራሉ ይሸሻሉ።
«ስታገኟቸው ለመቅረብ ይከብዳሉ፤ በጭንቀትም የተሞሉ እና ፈሪዎችም ናቸው። አንዳንዴ በመደበቅ ራሳቸውን ለማዳን ስለሚሞክሩ በመጠኑም ቢሆን የዱር እንሰሳ የሚመስል ባህርይ አላቸው።ግን ልብስ ካገኙና ትኩስ ሻይ ከጠጡ እና ትኩስ ሾርባም ከበሉ በኋላ የሰው ልጅ ባህርያቸው ይመጣል። መሳቅ  አንዳንዴም ከኛ ጋር መቀለድ ይጀምራሉ። ሌላ ሰው እንደሚንከባከባቸው ሌሎች ሰዎችም አስፈላጊ ናቸው ብለው እንደሚያስቡ ሲያውቁ ይቀየራሉ። እነዚህ ከነርሱ ጋር መነጋገር ስንጀምር ልባችንን የሚነኩን ወቅቶች ናቸው። አንዳንዴ የሰጠናቸውን ምግቦች አብረን እንድንበላ ይጠይቁናል። ከነርሱ ጋር እንድትበሉ እንድትጠጡም ይፈልጋሉ። »

ስደተኞች በፖላንድ ድንበር ላይ ምስል፦ Karol Grygoruk

የፖላንድ መንግስት በጫካ ውስጥ ለተደበቁ ስደተኞች በእነዚህ አክቲቪስቶች የሚደረገውን እርዳታ በጥብቅ ይተቻል፤ ወንጀልም ነው ይላል። በአሁኑ ጊዜ በፖላንድ ድንበር ላይ ስደተኞችን የረዱ አምስት ሰዎች ምስራቅ ፖላንድ በሚገኘው ሃይኖቭካ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የዚህ ምክንያቱ ጫካ ውስጥ የነበረ አንድ የኢራቅ ኩርዶችን ቤተሰብ ከሰባት ልጆቻቸው ጋር በመርዳታቸው ነው። ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ደግፈዋል የሚል ክስ ነው የተመሰረተባቸው ። ችርሳንቭስካ ግን በዚህን መሰሉ ክስ አትሸማቀቅም። በአጭሩ መርዳት ሕጋዊ ነው ትላለች። ከጥቂት ሰዓታት  በኋላ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ ጥሪ መጣ ። እርዳታ የሚጠይቁ አራት አፍጋናውያን ናቸው፤ ከመካከላቸው አንዱ ከድንበሩ አጥሩ ላይ ወድቆ እግሩ ተሰብሯል። አሁን ግን እነችርሳንቭስካ ብቻቸውን ሳይሆን ከሐኪም ጋር ይሄዳሉ።

ናዲን ቮይቺክ /ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW