1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

13 ሰዎች በግልገል በለስ ከተማ ተገደሉ

ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2015

በፓዌ ሆስፒታል የተጎዱ ሰዎችን በማሳከም ላይ የሚገኙ አንድ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ባለፈው አርብ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ በደረሰው ጥቃት ፀጥታ ሐይሎችን ጨምሮ ከ10 የሚበልጡ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ እስከ ትናንት ድረስ የጠፉ ሰዎች እየተፈለጉ ከተለያዩ ቦታ አራት ሰዎች በጫካ ሞተው መገኘታቸውንም ገልጸዋል

Äthiopien Gilgel Beles
ምስል Negassa Desalegn/DW

13 ሰዎች በግልገል በለስ ከተማ ተገደሉ

This browser does not support the audio element.

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ውስጥ ባለፈው አርብ ማምሻውን ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር 13 መድረሱን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የፀጥታ ኅይሎች በተገደሉበት ከምሽቱ 12፡30 ገደማ በደረሰው ጥቃት 17 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ቆስለው የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።፡ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ከወር በፊት የሰላም ተመላሽ ተብለው  የተመለሱ እና ከግልገል በለሰ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው የቻይና ካምፕ የሚባል ቦታ የሚኖሩ  መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ጉዳት ያደረሱ ታጣቂዎች በጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ ስም (ጉ.ህ.ዴ.ን) የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው የተባለ ሲሆን በጉባና ዳንጉር ወረዳ እና ሱዳን ድምንር አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብሏል፡፡ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ፓርቲ በበኩሉ በጥቃቱ ሁለት የታጣቂ ቡድን አበላት እና አራት ንጹን ዜጎች  ህይወት ማለፉን መረጃ እንደደረሰው ገልጾ ጥቃት አድራሾች ለሕግ መቅረብ እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡ የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ከተለያዩ ነዋሪዎች የተለያዩ መረጃ የተገኘ ሲሆን በመንግስት በኩል ስለ ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም፡፡
በፓዌ ሆስፒታል  የተጎዱ ሰዎችን በማሳከም ላይ የሚገኙ አንድ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ባለፈው አርብ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም በግልገል በለስ ከተማ በደረሰው ጥቃት ጸጥታ ሐይሎችን ጨምሮ ከ10 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡  እስከ ትናትናው ዕለት ድረስ የጠፉ ሰዎች እየተፈለጉ ከተለያዩ ቦታ አራት ሰዎች በጫካ ሞተው መገኘታቸውን ገልጸው በጥቃት  የደረሰው የጉዳት መጠን በየዕለቱ እየጨመረ እንደሚገኝ  አክለዋል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎችም ወደ አጎራባች ወረዳዎች መሸሻቸውን ገልጸዋል፡፡ 
በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በከተማው ውስጥና ቻይና ካምፒ የሚባል ስፍራ በጸጥታ ሀይሎች መሰብሰባቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌሎች ሁለት የከተማው ነዋሪዎች ለዶቸቬለ ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰው ታጣቂዎቹ ተደራጅተው እና ዘመናዊ መሳሪዎችን በመታጠቅ በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች እና በመኪና ላይ በከፈቱት ተኩስ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ በጉሙዝ ህዝብ ዴሚክራሲያዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ፓርቲ( ጉ.ህ.ዴ.ን) ስም ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ እነዚህ ታጣቂዎች በሚያዚያ  26/2015 ዓ.ም የሰላም ጥሪን ተቀብሎ ወደ ከተማ መግባታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ከእነ ትጥቃቸው ወደ ከተማ መግባታቸው ለነዋሪው ስጋት ሆኖ መቆየቱንም  ተናግረዋል፡፡ 
በግልገል በለስ እና አካባቢው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን  ጥቃት አስመልክቶ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀሩን ሁመር ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ቆይተን እንድንደውል ቃል ቢገቡም በተባለው ሰዓት በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ቢደውልም ስልካቸው አይነሳም፡፡  በግልገል በለስ ከተማ የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ በተመለከተ ዶቼቬለ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም በሰራው ዘገባ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀሩን ኡመር  በወቅቱ "በዚህ ጉዳይ ላይ እየሠራንበት ነው" የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ 
የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉዴታ ድርጅታቸው የሰላም ስምምነት ላይ ከደረሰ ወዲህ በድርጃቸው ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወደ ስልጠና እና ስራ መሰማራቸውን ተናግረዋል፡፡ በግልገል በለስ ጥቃት መደረሱንና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ድርጅታቸው እንደሚያወግዝና በንጹሀን ዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብሏል፡፡
ግንቦት 24/2015 ዓ.ም ጉ.ህ.ዴ.ን ባወጣው መግለጫ በፓርቲው ስም ታጥቆ ለሚንቀሳቀስ ቡድን ኃላፊነት እንደማይወስድ  አመልክተዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዳይሆን ለማደቀናፍ የሚሰሩ ኃይሎች አሉ ሲል የገለጸው ፓርቲው  የሰላም ጥሪን ከተቀበሉ ታጣቂዎች መካከል  የተወሰኑ ግለሰቦች  ግጭት ለመፍጠር ጥረት እያዳረጉ ነው ሲል በወቅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW