1443ኛው የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓል በድሬደዋ ፣ ሀረር እና ጅግጅጋ ከተሞች
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 2 2014
ማስታወቂያ
1443ኛው የኢድ አል አድሀ አረፋ በዓል በድሬደዋ ፣ ሀረር እና ጅግጅጋ ከተሞች በድምቀት ተከብሯል። በዓሉን በመረዳዳት እና በመደጋገፍ እንደሚያከብሩም በየከተሞቹ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል።
በድሬደዋ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች "ኢድ ሜዳ" ተብሎ በሚጠራው የበዓሉ ማክበርያ ስፍራ ከንጋት ጀምሮ በመሰባሰብ በሶላት ስግደት በዓሉን አክብረዋል። ለዶይቼ ቬሌ አስተያየት የሰጡት አቶ ፈርሀን አብዱላሂ ከስግደት መልስ በዓሉን ያለኝን በማካፈል እንደሚያከብሩ ገልፀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበዓሉ በተለይ ወጣቶች ድሬደዋ የምትታወቅበትን የፍቅር እሴት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል። የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው "ሙስሊሙ ህብረተሰብ በተለይ ወጣቶች የሽብርተኞችን እና ፀረ ሰላም ኃይሎችን አፍራሽ ሴራ" እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ በጥንታዊቷ ሀረር ከተማም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሯል።የሀረር ነዋሪው አቶ ፈርሀን በበዓሉ መረዳዳት እና ጥላቻን ማስወገድ ይገባል ብለዋል። 1443ኛው የአረፋ በዓል በጅግጅጋም በድምቀት መከበሩን ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አቶ ሀሰን የተባሉ ነዋሪ ተናግረዋል።
መሳይ ተክሉ
ታምራት ዲንሳ