1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

1447ኛው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ

ሐና ደምሴ
ረቡዕ፣ ግንቦት 19 2018

በመላው ኢትዮጵያ 1447ተኛው የኢድ አል አድሃ በዓል በድምቀትና በታላቅ የአንድነት ስሜት መከበሩ ተገለጠ። ታላቁ የሰዋዕትነት እና የደግነት መገለጫ የሆነው በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድም እየተከበረ ነው።

1,447ኛው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ
1,447ኛው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባምስል፦ Hanna Demisse/DW

1,447ኛው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

በመላው ኢትዮጵያ 1447ተኛው የኢድ አል አድሃ በዓል በድምቀትና በታላቅ የአንድነት ስሜት መከበሩ ተገለጠ። ታላቁ የሰዋዕትነት እና የደግነት መገለጫ የሆነው በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድም እየተከበረ ነው። በኢትዮጵያም 1,447ኛው የአረፋ በዓል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት፣ በጸሎት እና በምጽዋት ተከብሯል። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም እና የአካባቢው ጎዳናዎች በማለዳው የንጋት ጸሎት የዒድ ሰላት ለመታደም በነጩ ባህላዊ አልባሳት ባሸበረቁ ምዕመናን ተሞልተው ታይተዋል።

በዒድ ሰላቱ ወቅትም የእምነቱ መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአረፋ በዓል መሠረቱ መስዋዕትነት፣ ታማኝነት እና ለተቸገሩት መድረስ መሆኑን አስገንዝበዋል። በተለይም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የምዕመኑ መረዳዳት፣ መተሳሰብ እና ለሰላም የሚደረገው ጸሎት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተነግሯል።

በዓሉ የሃይማኖት እሴቶችን ጠብቆ ከመከበር ባለፈ፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና አብሮነት የሚያጠናክሩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች የሚጎለብቱበት ነው። የበዓሉ ዋነኛ አካል የሆነው የእርድ ሥጋ ቤተሰብ እና ለወዳጅ ዘመድ ከመከፋፈሉ ባለፈ፣ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ ለተዳከሙና አቅመ-ደካማ ለሆኑ ወገኖች በስፋት እንዲደርስ ተደርጓል። ይህም የበዓሉን ሰብአዊ ገጽታ ይበልጥ አጉልቶታል። የበዓሉ ታዳሚ ለዶቼ ቬለ «የዒድ አል-አድሃ አረፋ በዓል የምንተዛዘንበት አንዱ ለአንዱ የሚተሳሰብበት ነው።» ሲሉ ተናግረዋል።

1,447ኛው የዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባምስል፦ Hanna Demisse/DW

 ይህ ታላቅ የጋራ እሴት የሆነው በዓል፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ዘላቂ የአብሮነት ባህል የሚያሳይና ለሀገራዊ ሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑ ተገልጿል። ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮ እንኳን ለ1,447ኛው የዒድ አል-አድሃ አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ዒድ ሙባረክ።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW