1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

19ኛዉ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ በዋርሶ

ሐሙስ፣ መስከረም 13 2008

«ኢትዮጵያ እንደሌሎች የዓለም ሃገራት ሁሉ በተመድ እዉቅና ያላት ናት ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ትልቅ ስልጣኔ፤ ትልቅ ታሪክ ትልቅ የሕዝብ ክምችት፤ ትልቅ የባህል ብዛሃነት ያላት ሃገር ናት» ፖላንድ ዋርሶ ላይ ስለተካሄደዉ ስለ19ኛዉ የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ የነገሩን የኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሀሰን።

Die 19. Internationale Konferenz der Ethiopian Studies
ምስል Dr. Andreas Wetter

19ኛዉ የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ

This browser does not support the audio element.


የጥንታዊ ቅርሶችና ታሪክ ባለቤት የሆነችዉ ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ አንስቶ የታሪክ የቅርስ ተመራማሪዎችን ትኩረት እንደሳበች ናት። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚካሄዱት የተለያዩ ጥናቶች ግብዓትነት ትልቅ አስተዋፅኦን ማድረጉም ይታወቃል። ለዚህም ከ60 ዓመት በላይ የሆነዉ የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተጠቃሽ ነዉ። ስለጉባዔዉ ፋይዳ ኢትዮጵያዉያንና አንድ ጀርመናዊ የጉባዔዉን ተሳታፊን አነጋግረንናል።

ምስል Dr. Andreas Wetter


የመጀመርያዉ ኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በጎርጎሪዮሳዊ 1959 ዓ,ም ነዉ የተካሄደዉ። በየሶስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚደረገዉ ይህ ጉባዔ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለት ጊዜ ከኢትዮጵያ ዉጭ በመፈራረቅ ነዉ ትኩረታቸዉን በኢትዮጵያ ባህል፤ ታሪክ፤ ቅርስ፤ ቋንቋ ላይ ያደረጉ የምሑራን ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት። በፖላንድ መዲና ላይ ለአምስት ቀናት የተካሄደዉ የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ምን ዓይነት መልክ ነበረዉ ? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሀሰን፤

« ይህ ጉባዔ ታሪክን ብቻ ሳይሆን የሚጠናዉ፤ በዚህ ጉባዔ ሥነ-ሕዝብ ይጠናል የቋንቋና ፤ ማኅበረሰባዊ ሳይንስ፤ ሥነ-ቋንቋ በሙሉ የሚቀርብበትና አዳዲስ ሃሳቦች የሚፈልቁበት ነዉ ። ከነዚህ ሃሳቦች ደግሞ ትምህርት የሚገኝበት የእዉቀት አድማስ የሚሰፋበት ነዉ። እኔ ስብሰባዉን ከሚከፍቱት ሰዎች አንዱም ነበርኩ። በመክፈቻ ንግግሪ ያወሳሁት የጉባዔዉን ታሪክ ነዉ። ጉባዔዉ ለመጀመርያ ጎዜ በጎርጎረሳዊ 1959 ዓ,ም ሮም ላይ ተካሄደ ከዝያ በ1972 ዓ,ም ማንችስተር ብሪታንያ ፤ 3 ተኛዉ በ1966 አዲስ አበባ፤ በ 1972 ሮም ኢጣልያ፤ በ 1977 ዓ,ም ኒስ፤ ፈረንሳይ፤ በ1978 ዓ,ም ቺካጎ፤ ዩኤስ አሜሪካ ፤ በ1980፤ ቴላቪብ ፤ እስራኤል፤ በ1982 ዓ,ም ፈረንሳይ፤ በ1991 አዲስ አበባ፤ በ1994 ሚቺገን፤ ዩኤስ አሜሪካ፤ በ1977ዓ,ም ኪዮቶ ጃፓን፤ 2000 ዓ,ም አዲስ አበባ፤ በ2003 ሃንቡርግ፤ ጀርመን ፤ በ2007 ኖርዊ፤ በ2009 ዓ,ም አዲስ አበባ ፤ በ2012 ዓ,ም ድሪደዋ ፤ በ2015 ዓ,ም ዋርሶ ፖላንድ ላይ ነዉ የተካሄደዉ። ይህ ሲሆን ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ ጥናት ጉባዔ ምስራቅ አዉሮጳ ላይ፤ በሩስያሞስኮ፤ ዋርሶ ፖላንድ፤ ላይ ሲካሄድ ምስራቁን ከምዕራቡ አደበላልቆ ብዙ ቦታዎችን የሚሸፍን የሕዝብን ትኩረት የሳበ ባህል ነዉ ያለን። በዚህ ጉዳይ እኛም የምንኮራዉ በታሪካችን በማንነታችን በባህላችን ነዉ። እነዚህ ጉባዔዎች የኢትዮጵያ ምስክር ናቸዉ።»
በዋርሶ በተካሄደዉ ኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወደ 476 ጉባዔተኞች ተገኝተዉበታ። በዚህ ጉባዔ የሚደንቀዉ ነገር ከኢትዮጵያ ተሳፍረዉ የመጡ ከ 100 በላይ ምሑራን ተሳታፊዎች እንደነበሩ ዶክተር አህመድ ሀሰን ተናግረዋል።
« በፖላንዱ ጉባዔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ዩንቨርስቲዎችን አሰባስበናል። የክልል ዩንቨርስቲዎች በጣም በሚያስደስት ሁኔታ ለምሁራኖቻቸዉ ገንዘብ እየሸፈኑ ወደ ጉባዔዉ ልከዋቸዋል። የምርምሩ አጀንዳ ዘርፈ ብዙ ነዉ። ችግር ፈቺ ምርምሮች ያሉበት ነዉ። የሚገርመዉ በዚህ ጉባዔ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ከኢትዮጵያ ዉጭ ሲሳፉ ለመጀመርያ ነበር። ኢትዮጵያዉያን መምህራን በከፍተኛ ቁጥር ታይተዋል። ከመቶ በላይ ነበሩ።»

በጀርመን መዲና ነዋሪ የሆነዉ የአፍሪቃ ጉዳይ ተመራማሪ እና አማረኛ ቋንቋ ተናጋሪዉ ጀርመናዊ ዶክተር አንድሪያስ ቬተር እስካሁን በተደረጉት በአብዛኞቹ ኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተካፋይ ነበር። በጉባዔዉ ላይ ስለኢትዮጵያ መንዙማ የጥናት ጽሑፋቸዉን አቅርበዋል። ዘንድሮ ዋርሶ ላይ የተደረገዉ ይህ ጉባዔ፤ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በምን ይለያል፤ ለሚለዉ ጥቃቄ ዶ/ር አንድርያስ ቬተር
«የሚለየዉ ቦታዉ አዲስ በመሆኑ ነዉ። ከሶስት ዓመት በፊት ጉባዔዉ የተካሄደዉ ድሪደዋ ላይ ነበር። ብዙ ልዩነት አልታየኝም። ጉባዔዉ ከድሮ ጊዜ ልዩነቱ አሁን ኢትዮጵያዉስጥ ብዙ ዩንቨርስቲዎች ስላሉ የኢትዮጵያ ምሁራን የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች እየበዙ መምጣታቸዉ ነዉ። ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ ሲታይ አብዛኛዉ የጉባዔ ተሳታፊ የሚመጣዉ ከጀርመን ነበር። አሁን ግን ከኢትዮጵያ የመጡ ተሳታፊ ምሑራን ነበሩ አብዛኞቹ። እንደዉም በገንዘብ ችግር ምክንያት ብዙዎች መምጣት አልቻሉም።»
ሌላዉ የጉባዔዉ ተሳታፊ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ረዳት ፕሮፊሰር አህመድ ዘካርያ ናቸዉ። አህመድ ዘካርያ በጉባዔዉ ላይ ስለ ኢትዮጵያ መንዙማ የጥናት ጽሑፋቸዉን ካቀረቡት ጥቂት ምሑራን መካከል አንዱም ነበሩ።
« በአጠቃላይ ስብሰባዉ በጣም ጥሩ ነበር። በዚህ ጉባዔ ስለ ኢትዮጵያ መንዙማ ብዙ የጥናት ጽሑፎች ቀርበዋል። በአጠቃላይ ስለ መንዙማ ይዘት ፤ ስለ ወሎ መንዙማ፤ ስለ ሀረር መንዙማ፤ ስለ ሙዚቃዊ ይዘቱ፤ ስለ ያዘዉ ሥነ- ጽሑፍ የተለያዩ የጥናት ወረቀቶች ቀርበዋል። በኢትዮጵያ ያለዉን የመንዙማ ዓይነቶች ለመዳሰስ ተሞክሮአል። አሁንም ግን አጠቃላይ ነዉ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም መንዙማ አፋሮች፤ ሶማሌዎች፤ ኦሮሞዎችም ጋር አለ። የመንዙማ ዓይነቶች በጣም ብዙ ናቸዉ። እስከ ዛሬ በስርዓቱ ስላላጠናናቸዉ አፍ ሞልቶ መናገር ግን አይቻልም። አሁን በይዘት ያሉት ግን በብዛት በካሴት ገበያም ላይ ያሉት፤ የኦሮምኛ እና የአማርኛ መንዙማዎች ናቸዉ። እነዚህ ሥራዎች ወደ ሕዝቡ ቀርበዋል፤ ምሑራን ይዘቶቻቸዉን እየተነተኑ የሚጽፉት ለጥናት ምርምር ግብዓት እየሆነ ነዉ በግለሰብ ደረጃም የእያንዳንዱን እየነቀሱም የሚያጠኑ ምሑራንም አሉ። ከዛ ዉጭ ያለዉን የሚያጠኑ አሉ። የአቀራረቡ ይዘት በጣም የተለያየ ነበር። ከዚህ በፊት አዲስ አበባም ላይ አንድ ዓለማቀፍ የመንዙማ ጉባዔ አካሂደን ነበር። ይህ ዋርሶ ላይ የተደረገዉ ጉባዔ ለመንዙማ ዓለማቀፍ ጥናት መድረክ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። ከዚህም ሌላ በተከታታይ ስለመንዙማ የጥናት ዝግጅቶች ይኖሩናል። የእዉቀት አድማሳችን በየጊዜዉ እየሰፋ የማወዳደርያም ነገር እያደረግነዉ ነዉ። የኢትዮጵያ መንዙማ ከዓለም አቀፍ መንዙማ እንዲሁም ከኦርቶዶክስ ዝማሬ ጋር ያለዉን ልዩነት እና ቅርበት የሚጠናበት ጊዜ ነዉ። በተለይ የሙዚቃ ቅኝት ጥናት ምሑራን የበለጠ ዘርፉን ያሰፉታል ብዩ ተስፋ አደርጋለሁ።»

ዶክተር አንድርያስ ቬተር በአፍሪቃ ቋንቋዎች ሙዚቃ እና ባህል ዙርያ በርካታ የምርምር ስራዎችን አድርጎአል። ኢትዮጵያዉያንም ከጫፍ እስከ ጫፍ ዞር ጎብኝቶአታል፤ አጥንቷታልም። የአዝማሪን ሥራ ለጀርመናዉያን ብሎም በዓለም አቀፍ መድረክ ለማስተዋወቅ ጥረት ካደረጉት ምሁራን ዉስጥ አንዱም ነዉ። ንጹህ ጀርመናዊ ነዉ። የኢትዮጽያን ባህላዊ ምግቦች እጅግ ይወዳል። ከባህላዊ ምግብ ሌላ የበዛወርቅ ትዝታ የዚነት ሙሃባ ዜማ፤ የኤፍሪም ሙዚቃ እጅግ እንደሚያዝናዉ ከዚህ ቀደም አጫዉቶናል። ኢትዮጽያን ስለሚወድ ቋንቋዋን አጥንቶ ባህልዋን ለምዶ እዚህ በሃገሩ በጀርመን በመዲና በርሊን በሚገኘዉ እዉቁ የሁን ቦልት ዪንቨርስቲ በአፍሪቃ በተለይ ደግሞ በኢትዮጽያ የአማረኛ እና በመጥፋት ላይ ባለዉ የአርጎባ ቋንቋ ላይ ጥናት ያደርጋል። በዋርሶ ጉባዔ ላይ በኢትዮጵያ የሥነ-ልሳናዊ ጥናትና መንዙማ ላይ የሰራዉን ጥናት እንዳቀበ ነግሮናል።
እንደ አህመድ ዘካርያ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ጥናት በተመለከተ በአብዛኛዉ ብዕራባዉያን ምሑራን ነበር የሚሳተፉበት ያሉት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ግን በርካታ ኢትዮጵያዉያን ተመራማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች የኢትዮጵያን ጉዳይ በጥልቅ እያጠኑ መሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናጥናት እያሉ ታሪክዋን ባህሉዋን ማኅበረሰቡን ወንዝ ሸንተረሯን የሚያጠኑ የሚመረምሩ አያሌ የዓለም ምሁራን የሚፈልጔት ብቸኛ ሃገር ናት ሲሉ የኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሀሰን ገልፀዋል። ፖላንድ ዋርሶ ላይ ስለተካሄደዉ 19ኛዉ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጥናት የተዘጋጀዉን ሙሉ ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ምስል Dr. Andreas Wetter
ምስል Dr. Andreas Wetter
ምስል Dr. Andreas Wetter
ምስል Dr. Andreas Wetter

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW