2ተኛው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 4 2017
የመጀመሪያው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ የዛሬ ሁለት ዓመት ነሐሴ 29 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 1 ለሦስት ቀናት ናይሮቢ ኬንያ ላይ ነበር የተካሄደው። የጉባኤ ዋና አላማም አፍሪቃ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች የዳር ተመልካችና ሁል ጊዜ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራትና የበኩሏን አስተዋጽኦ እንዲኖራት ለማድረግ ነው።
ከሰኞ ጳጉሜ 3 ቀን 2017 አንስቶም ሁለተኛው የአፍሪቃ አየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባ ላይ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው የሚሳተፉት 54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችም የዓለምን የአየር ንብረት ቀውስ በአረንጓዴ የኃይል ምንጮች ላይ ወረትን በማዋል ምሳሌ የሚሆን መፍትሄ ይዘው መቅረባቸውን ተናግረዋል። ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የአስተናጋጇ ሀገር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፍሪቃ ሃገራት ለድርድርና ውይይት የተሰባሰቡት እራሳቸውን ለማዳን ብቻ እንዳልሆነ በማመልከት አሁን ትክክለኛውን ውሳኔ መወሰንከተቻለ «እዚህ የተሰባሰብነው ቀጣዩን የአየር ንብረት ኤኮኖሚ ለመንደፍ ነው» ማለታቸው ተዘግቧል።
የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ በአየር ንብረት ለውጥ በሕብረቱ አባል ሃገራት ላይ የሚያስከትለው የዕዳ ጫና እና በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ክፍፍል ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በአየር ንብረት ፍትህ መፍትሄ ማግኘት እንዳለበት አሳስበዋል።
«በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አባል አገሮቻችን ያጋጠማቸው ተጋላጭነት ያስከትለው የዕዳ ጨና እና የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኢፍትሀዊ መዋቅር ፤ በአየር ንብረት ፍትህ መፍትሄ ማግኘት አለበት። ክፍለ ዓለማችን ተግባራዊ ለምታደርገው የተላምዶ የመኖር እቅድ በገንዘብ ድጋፍ፤ በቴክኒዎሎጂ እና በዕውቀት ረገድ እውነተኛ ትብብር እንፈልጋለን።»
በዚህ ጉባኤ ከሚሳተፉት አንዱ አቶ ገብሩ ጀንበር የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተደራዳሪ እና በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት የካርቦን ገበያ ተደራዳሪም ናቸው። አፍሪቃ ጉዳዩን በቅርበት እንደሚያውቅ ባለሙያ እንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ በአየር ንብረት ለወጥ መዘዞች በተደጋጋሚ እየተጠቃች ለምትገኘው አፍሪቃ ያለውን ፋይዳ እንዲህ ያስረዳሉ።
አፍሪቃ በክፍለ ዓለሙ የሚታየውን የአየር ንብረት ለውጥ ለማስተካከል ከፍተኛ አቅም እንዳላት የሚያምነው ይህ ጉባኤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ይህ አስተዋጽኦ ሚና እንደሚኖረው ነው ያመለከተው። የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ በዓለም ዓቀፉ የአየር ንብረት እንቅስቃሴ አፍሪቃ የመሪነት ሚና እንዲኖራትም ለማድረግ አልሟል። በዚህ መድረክም ሆነ ቀደም ብሎ በተካሄደው ተመሳሳይ የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ አማካኝነትም መጪው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ COP 30 ከመድረሱ አስቀድሞ ለድርድሩ የአፍሪቃን ድምጽ በአንድነት መልክ አስይዞ ለመዘጋጀት ወሳኝ መድረክ እንዲሆንም ታስቧል።
የመጀመሪያው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ተሞክሮ
ናይሮቢ ላይ ከተደረገው ከመጀመሪያው ጉባኤ የተገኙ ተሞክሮዎችም አሁን አዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ለሚገኘው ሁለተኛው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ግብአቶች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በዚህም ሁሉም የአፍሪቃ ሃገራትን ያሳተፈና ሁሉም ተሞክሮና ሃሳባቸውን የሚያካፍሉባቸው የተለያዩ መድረኮች መኖራቸውን የአየር ንብረት ተደራዳሪው አክለው ገልጸዋል።
በዋናነት ጉባኤው የአፍሪቃን የጋራ የአየር ንብረት ርዕዮት በአፍሪቃ መር መፍትሄ እንዴት ማምጣት እንደሚቻል ይነጋገራል። በተጨማሪም አፍሪቃ ለአየር ንብረት ተጽዕኖ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችሏት ስልቶች ላይ ትኩረት በማድረግም ውይይቶችን ያካሂዳል።
የኢትዮጵያን እና አዳጊ ሃገራትን የአየር ንብረት ጉዳይ ይዘው የሚደራደሩት አቶ ገብሩ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ሃገራት በኢንዱስትሪ ያደጉ ሃገራት ሊሰጡት ቃል የገቡት በአሜሪካን ዶላር በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠረውን ገንዘብ አፍሪቃ በልገሳ ሳይሆን በመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ማግኘት እንደምትሻ ነው የገለጹት።
የአፍሪቃ እምቅ አቅም
የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤው ክፍለ ዓለም አፍሪቃ የአየር ንብረትን በተመለከተ ለዓለም አቀፉ መፍትሄ የሚሆን እምቅ አቅም አላት ብሎ ያምናል። በዚህ ምክንያትም ፍትሀዊ፣ የጥሬ ሀብት ክፍፍልና ድጋፍ በተለይ ለአየር ንብረት ብክለቱ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ላላደረጉ የአፍሪቃ ሃገራት ሊደረግ ይገባል በሚልም ይሞግታል። ለመሆኑ አፍሪቃ የአየር ንብረት ለውጡን ለመቀልበት የምታቀርበው አላት የሚባለው እምቅ አቅም ምን ይሆን? አቶ ገብሩ፤ አፍሪቃ ያላት የወጣት ኃይል እራሱን የቻለ እምቅ ሀብት ነው የሚሉት የአየር ንብረት ተደራዳሪው፤ አፍሪቃ ከሠራችም ከራሷ አልፋ የሌላውን ዓለምም የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ የሚያስችል ሀብት እንዳላት ይናገራሉ።
ፓሪስ ላይ ሃገራት ከተስማሙበት የብክለት ቅነሳ ውል ዩናይትድ ስቴትስ በፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ከወጣች ሰነበተች። የአፍሪቃ መሪዎች ታዲያ ክፍተቱን ለመሙላት የራሳቸውን የመፍትሄ ሃሳብ ይዘው ለመቅረብ እንደሚፈልጉ እያሳዩ ነው። የመሬት መንሸራተት፤ ድርቅ፤ ኃይለና ዝናብ እና ጎርፍ የተደጋገመባት አፍሪቃ መሪዎች ምንም እንኳን የለውጡ ተጽዕኖ በገሀድ እየታየ ቢሆንም ሁሌም በተጎጂነት መንፈስ ከመቅረብ ይልቅ ካርቦንን በመሰብሰብ፤ ታዳሽ የኃይል ምንጭ አማራጮችንም በማከል ለአየር ንብረት ቀውሱ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ያሉትን ብራዚል ላይ ለሚካሄደው ለመጪው ዓመታዊ ዓለም አቀፍ ጉባኤ COP 30 ለማቅረብ እየተዘጋጁ ነው።
የአፍሪቃ የመፍትሄ አካል የመሆን ፍላጎት
አፍሪቃ በራሷ መንገድ አረንጓዴ ቴክኒዎሎጂን ተጠቅማ በኢንዱስትሪው ለማደግ እንደምትፈልግ፣ ለዚህም የቴክኒዎሎጂ ፈጠራዎች ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው የተገለጸው።
ዓለም አቀፉ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ COP ተብሎ የሚታወቀው በተለያዩ ሃገራትን ክፍለ ዓለማት በየዓመቱ በመካሄድ ላይ ነው። አፍሪቃ በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ደቡብ አፍሪቃ ላይ COP 17ን አስተናግዳለች። ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ አፍሪቃ እንድታዘጋጅ መታሰቡን ተከትሎ በጎርጎሪዮሳዊው 2027 ኢትዮጵያ እንድታካሂድ ፍላጎት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትናንት በጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው መጠቆማቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተደራዳሪ አቶ ገብሩ እንደሚሉት ጉዳዩ በመጪው ዓመት የሚታይ ይሆናል። ትናንት በይፋ የተጀመረው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ዛሬ ሁለተኛ ቀኑ ሲሆን በተለይ የአፍሪቃ መሪዎች በአየር ንብረት ፖሊሲው በኩል መሪ ሆኖ ለመውጣት ከተጠቂነት አልፎ የመፍትሄ አካል የመሆን የጀመሩት እንቅስቃሴ መበረታታት እንደሚኖርበት አቶ አብሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። ለሦስት ቀናት የሚዘልቀው የአፍሪቃ የአየር ንብረት ጉባኤ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ