2021 ዓ,ም እና ለአፍሪቃ ዴሞክራሲ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 17 2014
በተሰናባቹ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2021 ቻድ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና ሱዳን መፈንቅለ መንግሥት አስተናግደዋል። በእነዚህ አራት ሃገራት የጦር ኃይሉ ነው ሥልጣን ላይ የተንጠላጠለው። አፍሪቃ ውስጥ በተለይ በጎርጎሪዮሳዊው 1970 እና 80ዎቹ ዓ,ም ወታደራዊ ኃይሎች ሲቪል አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሲያካሂዱ የነበሩበትን የጭለማ ጊዜ ያስታውሳል። እንዲያም ሆኖ አሁን ድርጊቱን በዝምታ የሚመለከት ኅብረተሰብ የለም ይላሉ በዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ዴሞክራሲ ተቋም የምዕራብ እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ፎሙንዮ።
«ከ70ዎቹ እና 80ዎቹ ዓ,ም ጋር ሲነጻጸር አሁን መልካሙ ዜና አፍሪቃውያን እራሳቸው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹን ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸው ነው። ለዚህም ነው ሌላው ቀርቶ ሱዳን ውስጥ የጦርኃይሉ መፈንቅለ መንግሥት በማድረጉ ጠንካራ የተቃውሞ ሰልፍ የምናየው።»
ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ሕብረትም መፈንቅለ መንግሥትን በተመለከተ ጠንካራ አቋም እያሳየ መሆኑንም የሚገልጹም አሉ። በጀርመኑ የዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም የአፍሪቃ ጥናት ባልደረባዋ ዩሊያ ግራውፎግል የሕብረቱን ርምጃ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ይሉታል።
«ለእኔ የአህጉሪቱ ድርጅት ቀጣይነት የታየበት ርምጃዎችን መውሰዱ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው። ለምሳሌ በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ አባልነቷን ለጊዜው አግዷል።»
እንዲያም ሆኖ ሕብረቱ ሊሰናበት ጥቂት ቀናት በቀሩት በዚሁ ዓመት በሁሉም ረገድ አቋሙን ግልጽ ሲያደርግ አልታየም። ለማሳያም የዩጋንዳው የረዥም ዓመታት መሪ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ለስድስተኛ ጊዜ ሥልጣናቸውን ሲያራዝሙ ሕብረቱ ዝምታን መርጧል። ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ቦብ ዋይን በምርጫው ወቅት በዩጋንዳ ታሪክ የሚማይዘነጋ ማጭበርበር ተፈጽሟል ባይ ናቸው።
«ከምርጫው መጀመረያ ዝግጅት ጀምሮ በዩጋንዳ ታሪክ ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት ነበር። በርካታ ክሶች ነበሩ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ እኔ የምመራው የሕዝቦች ኃይል ንቅናቄ ፓርቲ ደጋፊ ወጣቶች በመንግሥት ታግተዋል።»
እራሳቸው በቁም እስር የቆዩት ዩጋንዳዊው ፖለቲከኛ እንደሚሉትም በሀገሪቱ በተባባሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጣለው እገዳ ዜጎች እንደልባቸው እየተሰባሰቡ ሃሳባቸውን እንኳ መግለጽ እንዳይቻሉ በማገዱ ተሰናባቹ ዓመት 2021 አምባገነን መሪዎች ሥልጣናቸውን ያጠናከሩበት ሆኗል። እንዲያም ሆኖ በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ሕዝቡ አምባገነኖችን በመቃወም በአደባባይ ድምጹን ማስማቱን መቀጠሉ አሁንም ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ያለውን ጥማት እንደሚያሳይ ዩሊያ ግራውፎግል አጽንኦት ይሰጣሉ። ይኽም በሱዳን ብቻ ሳይሆን በሴኔጋል እና በስዋዚላንድም ታይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ዓመት አፍሪቃ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዛምቢያ አካሂዳለች። አዲሱ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2022ም ተመሳሳይ አዝማሚያ እንደሚከተል የሚገምቱ አሉ። አንጎላ ውስጥ ከአምስት ዓመታት በፊት የረዥም ዘመኑን ፕሬዝደንት ጆሴ ኤዶዋርዶ ዶሳንቶሽን የተኩት ፕሬዝደንት ማኑዌል ሎሬንቾ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ይወዳደራሉ። አንጎላን ለ40 ዓመታት ገደማ በገዙት ዶሳንቶሽ እግር የተተኩት ፕሬዝደንት ሎሬንቾም የተመሳሳይ ገዢ ፓርቲ የመጡ በመሆናቸው ምርጫው ምን ያህል ነጻ እና ሚዛናዊ ይሆናል የሚለውን ታዛቢዎች በጉጉት እየጠበቁ ነው። ሌላዋ በትኩረት የምትታየው ሀገር ኬንያ ናት። ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬንያታ ከሁለት የሥልጣን ዘመናት በኋላ ይሰናበታሉ። ባለፈው የምርጫ ወቅት በስፋት የተፈጸመው ማጭበርበት ለ90 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑን የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ አድርጓል። ምንም እንኳን እንዲህ ያለው ክስተት ባይዘነጋም በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2022 አፍሪቃ የተሻለ አስተዳደር ለመመስረት የምታደርገው ጥረት የተሻለ እንደሚሆን ብዙዎች ተስፋ ሰንቀዋል።
ዳንኤል ፔልስ/ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ