31 ዓመት አገልግለው ከ100 ዶላር ያነሰ፥ ሶማሊላንድ 4ሺህ ዶላር የወር ክፍያ፦ ዶ/ር ፍስሃ
ዓርብ፣ ግንቦት 8 2017
ከ7 ዓመታት ትምህርት በኋላ በዶክተር ማእረግ ተመርቀው ለ31 ዓመታት አገልግለው በኢትዮጵያ የወር ደመወዛቸው 14 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፥ ዐለም አቀፍ ዕውቅና ያልተሰጣት ሶማሊላንድ እንኳን እስከ አራት ሺህ ዶላር እንደምትከፍልም ገልጠዋል፦ ዶክተር ፍሥሃ አሸብር ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ተገቢ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም የለንም በሚል ጥያቄ ያቀረቡ የጤና ባለሞያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሰሞኑ ሰልፍ አድርገዋል ። የኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች «መሠረታዊ የዳቦ» ላሏቸው ጥያቄዎች መንግሥት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሲጠይቁም ሰንብተዋል ። ባለሞያዎቹ ለጥያቄያቸው ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ሰኞ ዕለት ተጠናቅቋል ።
ማክሰኞ የሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ በብርቱ ሲያስጠነቅቁም ነበር። አንዳንድ የጤና ባለሞያዎች እንደታሰሩም ተዘግቧል ። ለመሆኑ በኢትዮጵያ የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ በዋናነት ምንድን ነው? ከሚመለከተው አካልስ ምን ምላሽ አገኙ? የትግራይ የጤና ባለሞያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሥሃ አሸብር ስለ ኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች የረዥም ጊዜ እሮሮ እና ጥያቄ ሊያብራሩ የዶይቸ ቬለ የሳምንቱ የአንድ ለአንድ እንግዳችን ሁነዋል ።
የጤና ባለሞያዎች ጥያቄ እና አጸፌታው በኢትዮጵያ
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የጤና ባለሞያ ለራሱ እና ለቤተሰቡ ምግብ፣ መጠጥ፣ የቤት ኪራይ እና ለመሳሰሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ወጪ ለማውጣት በወር የሚያገኘው ደመወዝ ምን ያህል ይበቃዋል የሚል ነበር ቀዳሚ ጥያቄያችን ። ከተማሪዎች ሁሉ ከፍተኛ ነጥብ አምጥቶ ለዓመታት በትምህርት ለፍቶ የተመረቀ ጀማሪ ዶክተር ወደ ሥራ ሲገባ እጁ ላይ ተጣርቶ የሚደርሰው ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ብር ብቻ ነው ብለዋል ዶክተር ፍሥሃ ።
የትግራይ ክልልን እንደ አብነት ብንወስድ ለቤት ኪራይ «ሦስት ሺህ እንኳን ይከፍላል ብንል የሚቀረው ሦስት ሺህ ብቻ ነው» ብለዋል ። አንድ ኩንታል ጤፍ ከ13 ሺህ እስከ 15 ሺህ በሚሸጥበት አገር፤ አምስት ሊትር 1 ሺህ 600 ብር በሆነበት አካባቢ የተረፈውን ለምግብ እና ለሌሎች ነገሮች ለማውጣት የጤና ባለሞያው እጅግ ችግር ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
አንዲት ነርስ የተጣራ የወር ደመወዟ አምስት ሺህ ብር ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ፍሥሃ «ቁርስ ስጪኝ እማ» የሚሉ ልጆቿን ድምፅ መስማት ያልቻለች ነርስ በሥራ ገበታዋ ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆና ያገኙበት አጋጣሚ መኖሩንም ነግረውናል ። እርሳቸው ከ7 ዓመታት ትምህርት በኋላ በዶክተር ማእረግ ተመርቀው ለ31 ዓመታት አገልግለው የወር ደመወዛቸው 14 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል ። ዐለም አቀፍ ዕውቅና ያልተሰጣት ሶማሊላንድ እንኳን እስከ አራት ሺህ ዶላር እንደምትከፍልም ገልጠዋል ።
ዶክተር ፍሥሃ አሸብር የጤና ባለሞያዎችን እሮሮ ከተጨባጭ መረጃዎች ጋር በማጣቀስ ማብራሪያ የሰጡበትን ሙሉ ቃለ መጠይቅ ከድምፅ ማእቀፉ ማድመጥ ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ