1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

37ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ድባብ

ዓርብ፣ የካቲት 8 2016

የአፍሪካ ህብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄደው በአስተናጋጇ ኢትዮጵያ ሳይቀር በሌሎች በርካታ አባል አገሮች፤ የሰላም ችግር ባለበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችም በድርቅ ምክንያት ለረሀብ አደጋ በተጋለጡበት ድባብ ነው። አስተያየት ሰጭዎች ህብረቱ በዘንድሮው ጉባኤ አዲሱ ነገር በደካማ አቋም ላይ መሆኑን ይገልፃሉ።

የአፍሪቃ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ
የአፍሪቃ ህብረት ስብሰባ በአዲስ አበባ ምስል Solomon Muchie/DW

የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ

This browser does not support the audio element.

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚካሂድበት ድባብ

የአፍሪካ ህብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባኤ ከቅዳሜ የካቲት 9 እስከ 10  2016 ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ፤  በህብረቱ የስብሰባ አዳራሽ የሚደረግ ሲሆን፤ አሰቅድሞም ባላፉት ሁለት ቀናት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ተካሂዷል። የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄደው በአስተናጋጇ ኢትዮጵያ ሳይቀር በሌሎች በርካታ አባል አገሮች፤ የሰላም ችግር ባለበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችም በድርቅ ምክንያት ለረሀብ አደጋ በተጋለጡበት ድባብ ነው። በዓለም ዙሪያ ግጭት ጦርነቶችን የሚከታተለውና የሚያጠናው ድርጅት (ክራይሥ ግሩፕ) ተመራማሪና የአፍርካ አማካሪ ወይዘሪት ሊስል ቫውድራን ለ DW እንደገለጹት ደግሞ ፤በዘንድሮው ጉባኤ አዲሱ ነገር ህብረቱ በደካማ አቋም ላይ መሆኑ ነው። “ አዲሱ ነገር እንደሚመስለኝ አፍሪካ ህብረት በዳክማ አቋም ላይ መሆኑ ነው። ምክኒያቱም አንዳንድ አባል አገሮች  ከአካባቢያዊ ድርጅቶች ወተዋል። ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ስብስብ (ኢኮዋስ) ሦስት አገሮች፤ ከምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አንድ አገር ወተዋል፡፤  የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪ እንደገለጹት እነዚህ የህብረቱ ምሰሶዎች ሲሆኑ፤  ምሰሶዎቹ  እየተናዱ ከሆነ ደግሞ ለአፍሪካ ህብረት ትልቅ  ድክመት ነው” በማለት የዘንድሮውን ጉባኤ ልዩ ድባብ አመላክተዋል።

የጐባኤው የትኩረት አጀንዳዎች

በእነዚህና በሌሎች በርካታ ችግሮች ውስጥም ቢሆን ግን፤ ህብረቱ በበርካታ አህጉራዊና ዓለማቀፍዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ነው የሚጠበቀው። ጉባኤው በዋናነት በትምህርት ላይ እንዲያተኩር ተፈልጎ የነበር ቢሆንም፤ የጸጥታና የሰላም ፤ የድርቅና የምግብ ዋስትና  አጀንዳዎች ዋናዎቹ ጉባኤው የሚወያይባቸው ረዕሶች እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የክራይሲስ ግሩፕ ባለሙያዋ ወይዘሪት ቫውድራም ይህንኑ ለዲደብሊው አረጋግጠዋል። “ ቀዳሚ አጀንዳዎቹ የጸጥታና ደህንነት አጀንዳዎች ናቸው። ለምሳሌ የሱዳን ጉዳይ ትልቁ ቀዳማይ አጀንዳ ነው። የታላቁ ሃይቅ አካባቢና በሌሎች አገሮችና አካባቢዎች ያሉት የጸጥታ ችግሮችና ግጭቶች የመሪዎቹ ጉባኤ ትኩረቶች ናቸው” በማለት፤ ባጠቃላይም የሰላምና ደህንነት፣ የጠመጃ ላንቃዎችን የመዝጋት ፣ የስላም ፈንድ የመሳሰሉት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር በገባቸው የወደብ ስምምነት ምክኒያት ከሱማሊያ ጋር የገባችበት ውዝግብ፤ የመሪዎቹ ጉባኤ አንዱ አጀንዳ ይሆን ወይ? ተብለው የተጠየቁት ወይዘሪት ቫውድራን፤  “በኦፊሲየል የተያዘ አጀንዳ አይደለም። መሪዎቹ በዝግም ይሁን በግልጽ በሚያካሂዱት ስብሰባ ዋና አጀንዳ አድርገው የሚወያዩበት አይመስለኝም።  ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያና የሱማኤ ጉዳይ ሲሆን፤ ከዋናው ጉባኤ ጎን ግን  የሚካሄዱ በርካታ የሁለትዮሽና የቡድን ውይይቶችና ድርድሮች እንደሚካሄዱና ይህም ጉዳይ በጎን ውይይት ሊካሂደበት እንደሚችል ያላቸውን እምንት ገልጸዋል፤ እንዲህ ባለ ትልቅ ጉባኤ ዋናው ስራ የሚከወነው ከመጋረጃ ጀርባ መሆኑን በማስታወስ ጭምር።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተረስና የአፍሪቃ ህብረት ዋና ተጠፊ ሙሳ ፋኪ በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ ምስል Solomon Muchie/DW

የህብረቱ ችግሮችና ተግዳሮቶች

55 አባል አገራትና  በድምሩ ከ 1.4 ቢሊዮን በላይ ህዝብ ያለው የአፍርካ ህብረት  ከሀያ ዓመት በፊት እ እ እ በ2002 ዓ.ም  ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት በመለወጥ አዲስ አደረጃጀት ቢይዝም፤ አሁንም ግን በበርካታ ችግሮች የተበተበ እንደሆነ ነው የሚነገረው። እንደ የክራይሥ ግሩፕ ባለሙያዋ ወይዘሪት ቫውድራ አስተያየት፤ የድርጅቱ ውጤት ተኮር ያለመሆንና  ቀድሞ እርምጃ ለመውሰድ ያለመቻል  የመሳሰሉ በርካታ ችግሮች አሉበት። የእነዚህ ችግሮች ምንጭ ደግሞ ህብረቱ የልዑዓላዊ አገሮች ስብስብ እንጂ ስልጣን ያለው ድርጅት ባለመሆኑ ነው በማለት የአፍርካ ህብረት እንደ አውሮፓ ህብረት ግዴታቸውን በማይወጡ አባል አገሮች ላይ እርምጃ ለመወሰድ ስልጣን ያለው አለመሆኑን አስረድተዋል። ሌላው የህብረቱ ችግር የገንዘብ አቅም ማነስ ሲሆን፤ በገንዘብ የሚደጉሙት እንደ አውሮፓ ህብረትና ሌሎች ለጋሾች በውሳኔውና አሰራሩ ላይ ተጽኖ ሳይሳድሩ አይቀሩም ነው የሚባለው።

ተጠባቂ ውሳኔዎችና  መግለጫዎች

ያም ሆኖ ግን የአፍርካ ህብረት አባል አገራቱን በማስተሳሰርና በማስተባበር ሰላም እንዲፈጠር ዴሞክራሲም እንዲስፋፋ እያደረገ እንደሆነና በዓለማቀፍ ደረጃ ተሳትፎውና ተፍላጊነቱ እያደገ እንደሆነ ነው የሚነገረው። የዘንድሮው ጉባኤም እንደተባለው በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚካሄድ  ቢሆንም፤ መሰረታዊና ጠቃሚ ውስኔዎችን እንደሚይሳልፍ ነው የሚጠበቀው። መሪዎቹ በጉባኤው  መጨረሻ በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች አንድነታቸውን አጠንክረው እንደሚወጡና በተለያዩ ኣገሮች ያሉትን የሰላም ችግሮችን ለማስወገድም አዳዲስ የሰላም አሳቦችን ሊያፈልቁ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ወይዘሪት ቫውድራ ለ DW አረጋግጠዋል። የመካከለኛው ምስራቅን በተለይም  ጋዛን በሚመለክት ጉባኤው ጠንካራ አቋም ሊወስድ እንደሚችልና መሪዎቹም በአንድ ድምፅ ሊናገሩ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። በጉባኤው የተብበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴረሽና የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት ሉዊ ሚሸል በታዛቢነት የሚታደሙ ሲሆን፤ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫም በጉባኤው የመክፈቻ ቀን በክብር እንግዳነት ይገኛሉ ተብሏል።

 

ገበያው ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW