1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያዎቹ 6 የወሊድ ወራት የእናት ጡት አያጠቡም

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2016

በኢትዮጵያ 40% የሚሆኑ እናቶች የእናት ጡት ወተትን ለህፃናት ለተከታታይ 6 ወራት እንደማያጠቡ ተገለፀ። ችግሩ በተለይ በተፈናቃይ እናቶች እንደሚበረታ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አመልክቷል። አንዳንድ እናቶች ባለመመቻቸት የእናት ጡት ወተት በቂ አይደለም ብለው ስለሚምኑ ህፃናት 6 ወር ሳይሞላቸው ሌሎች ተጨማሪ ምግቦችን እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል።

40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያዎቹ 6 የወሊድ ወራት የእናት ጡት አያጠቡም
40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያዎቹ 6 የወሊድ ወራት የእናት ጡት አያጠቡም ምስል Tatu Yahaya/DW

40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያዎቹ 6 የወሊድ ወራት የእናት ጡት አያጠቡም

This browser does not support the audio element.

40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች በመጀመሪያዎቹ 6 የወሊድ ወራት የእናት ጡት አያጠቡም 
በኢትዮጵያ 40 ከመቶ የሚሆኑ እናቶች የእናት ጡት ወተትን  ለህፃናት ለተከታታይ 6 ወራት እንደማያጠቡ ተገለጠ፣ ችግሩ በተለይ በተፈናቃይ እናቶች እንደሚበረታ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አመልክቷል፤ አንዳንድ እናቶች በሥራ አለመመቻቸትና የእናት ጡት ወተት በቂ  አይሰጥም ብለው ስለሚምኑ ህፃናት 6 ወር ሳይሞላቸው ሌሎች ተጨማሪ ምግቦችን እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፣ ጡት የማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ለጨቅላ ህፃናት ከእናት ጡት ወተት ውጪ ሌላ ተጨማሪ ምግብ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ የጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይመክራሉ፣ የእናት ጡት ወተት ሁሉንም ንጥረ ነገሮች የያዘ በመሆኑ ለህፃኑ እደገትና ጤንነት ተወዳዳሪ እንደሌለው ነው ባለሙያዎቹ የሚገልፁት፡፡


የባለሙያ አስተያየት
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ወንድሜነህ ልየው የእናት ጡት ወተት በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ማጥባት ከፍተኛ ትቅም እንዳለው ነው የሚናገሩት፡፡ እንደባለሙያው  የእናት ጡት ወተት በተፈጥሮ የሚገኝና መተኪያ የማይገኝለት በንጥረ ነገሮች የዳበረ ነው፣  እስከ 6 ወራት ለህፃኑ በቂና አስተማማኝ ምግብ ነው፡፡ ለህፃኑ እድገትና ጤንነትም ዋስትና እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡  አንዳንድ እናቶች ግን በስራ ቦታ አለመመቻቸት፣ የእናት ጡት ወተት በቂ አይደለም ከሚል እሳቤና እናቶች በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈናቀሉበት ወቅት ህፃናቱ 6 ወራት ሳይሞላቸው ተጨማሪ ምግብ ለህፃናቱ እንደሚመግቡ አስረድተዋል፡፡


የእናቶች አስተያየት
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ አራስ እናት ለዶቼ ቬሌ ሲያስረዱ፣ “እናቶች በመንግስት ስራ፣ በንግድና በሌሎች ስራዎች ስንሰማራ  ቤት ከህፃኑ ጋር መዋል አስቸጋሪ በመሆኑ ተጨማሪ የቆርቆሮ ወተት፣ የላም ወተት፣ ውሀ  ህጻናቱ 6 ወር ሳይሞላቸው ለመመገብ እንገደዳለን፡፡” ብለዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ የኔሰው ካሳሁን ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ከተወለዱ ከ6 ወር በፊት ተጨማሪ ምግብ ይሰጡ እንደነበርና ምክንያት ያሉትን ጭምር ገልፀውልናል፡፡ በተለይ ጡታቸው ለተወለደው ህፃን ላያጠግብ ይችላል? ብለው ካሰቡ ተጨማሪ ምግብ እንደሚሰጡ ነው ያስረዱት፤ ያሳደጓቸውን ሁሉንም ልጆቻቸውን 6 ወር ሳይሞላቸው ተጨማሪ ምግብ እየመገቡ እንዳሳደጉ የነገሩን እኚህ እናት፣ ልጆቻቸውም እስካሁን ያጋጠማቸው ችግር እንደሌለ አብራርተዋል፡፡ ይህን አብዛኛዎቹ እናቶች እንደሚተገብሩትና ሰሞኑን አንዲት የወለዱ ጎረቤታቸው ህፃኑን 10 ቀን ሳይሞላው የቆርቆሮ ወተት ማስጀመራቸውን መመልከታቸውንም ገልጠዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በበቂ ሁኔታ የእናት ጡት ማጥባት አለመቻል በዓመት 16 ከመቶ ለሚሆኑ ህፃናት ሞት ምክንያት ነው፡፡ የእናት ጡት የሚጠቡ ህፃናት በተሻለ ሁኔታ ነገሮችን የማወቅና የመረዳት ችሎታ እንደሚያዳብሩና አስፈላጊ ያልሆነ ክብድትን ለመከላከልም ይረዳል ብሏል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባሰራጨው በዚሁ ዘገባ የእናት ጡት ወተት የሚያጠቡ እናቶች ለካንሰርና “ዓይነት ሁለት” ለተባለው የስኳር ህመም የመጋለጥ እድላቸውም ዝቅተኛ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

ፎቶ ማህደር ፤ የእናት ጡት ምስል Fabio Teixeira/AA/picture alliance


የእናት ጡት የሚያጠቡ እናቶች ቁጥር (%)
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ወንድሜነህ ልየው በመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ለህፃናቱ የእናት ጡት ወተት ብቻ የሚያጠቡ እናቶች ከ60 ከመቶ እንደማይበልጡ አንድ የተደረገን ጥናት መነሻ በማድረግ አብራርተዋል፡፡ በዚህ “የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት አካሂዶታል” በተባለው ጥናት በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ወር ድረስ ተጨማሪ ምግብ ሳይሰጡ የእናት ጡት ብቻ የሚያጠቡ እናቶ ከአጠቃላይ የእናቶች ቁጥር አንፃር 61 ከመቶ መድረሱ መረጋገጡን አስረድተዋል፣ ከአገር አቀፉ አንፃር ሲነፃፀር በአማራ ክልል ያለው አፈፃፀም የተሻለ እንደሆነ አቶ ወንድሜነህ ጠቁመው፣ በአማራ ክልል ለ6 ወራት ተጨማሪ ምግብ ሳይሰጡ የእናት ጡት ብቻ የሚያጠቡ እናቶች ቁጥር 75 ከመቶ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለችግሩ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች
ለችግሩ የተጋለጡት በዋናነት በተለያዩ ችግሮች ከቀያቸው የተፈናቀሉ እናቶች እንደሆኑም አቶ ወንድሜነህ ገልጠዋል፡፡ አቶ ወንድሜነህ በአማራ ክልል በ41 መጠለያ ጣቢዎችና በሚሊዮን የሚቆጠሩና ከማህበረሰቡ ጋር  የሚኖሩ፣ በድርቅ ምክንያት የተቸገሩ ነብሰ ጡር እናቶችና ወገኖች በእጅጉ ለእናት ጡት ወተት ማጥባት የተቸገሩ ናቸው ብለዋል፡፡
አንዲት በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ አካባቢ በሚገኝ ተፈናቃ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃይ እናት በቅርቡ እንደወለዱ አመልክተው ለህፃኑም ሆነ ለርሳቸው የሚሆን ምግብ ባለመኖሩ ጡታቸው ደርቋል፡፡

ወሳኝ የተባሉ የጡት የማጥባት ጊዜዎች
አቶ ወንድሜነህ እናቶች በ4ቱ ወሳኝ ጊዜዎች እናቶች በጥንቃቄ ህፃናቱን መመገብ አለባቸው ነው ያሉት፣ 4 ወሳኝ ጊዜዎች የሚባሉት ደግሞ፣
· ህፃኑ በተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ “እንገር” የተባለውን ወተት ማጥባት፣
· ህፃኑ ከተወለደ እስከ 6 ወር የእናት ጡት ወተት ብቻ እንዲመገብ ማድረግ፣
· ህፃኑ ከተወለደ ከ6 ወር በኋላ እስከ 2 ዓመትና በላይ ተጨማሪ ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኝ ማድረግና
· እናት ወይም ህፃን ሲታመሙ የእናት ጡት ወተት እንዳያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንደሆኑ  አስረድተዋል፡፡
እናቶች በአንዳንድ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ህፃናት 6 ወር ሳይሞላቸው ተጨማሪ ምግብ እንዲሰጡ የሚደረገው ቅስቀሳ ስነምግባር የጎደለውና ህገወጥ መሆኑን ተረድተው ከድርጊቱ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡

 ጡት ያማጥባት ሳምንት
ጡት የማጥባት ሳምንት ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1/2016 ዓ ም “ክፍተቱን ለመሙላት ሁሉንም እናቶች ጡት እንዲያጠቡ እንደግፍ” በሚል በአገራችን ለ16ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡


ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW