1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

41ኛዉ የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ትርዒት በሰሜን አሜሪካ በድምቀት ጀመረ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2016

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የባህልና ስፖርት ትርዒት አትላንታ ጆርጂያ ውስጥ እየተካኼደ ነው። የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ለዶይቸ ቨለ እንዳስታወቁት፣ በዘንድሮ 41 ዓመት ትርዒት፣32 ቡድኖች ይሳተፉበታል። በአትላንታ በከፍተኛ ድምቀት በተከፈተው 41ኛው ዓመት የፌዴሬሽኑ ዝግጅት በአጭር ጊዜ የተሰናዳ ነዉ።

41 ኛዉ የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ትርዒት በሰሜን አሜሪካ በድምቀት ጀመረ
41 ኛዉ የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ትርዒት በሰሜን አሜሪካ በድምቀት ጀመረምስል Tariku Hailu/DW

41 ኛዉ የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ትርዒት በሰሜን አሜሪካ በድምቀት ጀመረ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የባህልና ስፖርት ትርዒት አትላንታ ጆርጂያ ውስጥ እየተካኼደ ነው። የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ለዶይቸ ቨለ እንዳስታወቁት፣ በዘንድሮ 41 ዓመት ትርዒት፣32 ቡድኖች ይሳተፉበታል።  ትናንት ምሽት አትላንታ ጆርጂያ ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት በተከፈተው 41ኛው ዓመት የፌዴሬሽኑ ዝግጅት ላይ፣ዶይቸ ቨለ ያነጋግራቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ዐቢይ ኑርልኝ እንዳሉት፣ የዘንድሮው መርሐ ግብር በአጭር ጊዜ ዝግጅት የተካሄደ ነው። 
የኢትዮጵያን ባህሎች የማስተዋወቅ ተልዕኮ 
"ይህ ዝግጅት እንግዲህ 41ኛ ዓመት ነው። በዚህ ዓመት የሚደረገው በተለያዩ ውስብስብ ምክንያቶች በጊዜ ለማዘጋጀት እና የምንሄድበትን ከተማ ለማስታወቅ አልቻልንም ነበር።ግን ከአትላንታ ኮሚቴ ጋር በመተባበር፣በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዚህ ያማረ ዝግጅት ልናደርግ ችለናል።ይኸው እንደምታያቸው፣ሜዳ ላይ እያዝናኑን ያሉት የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰብን ጨዋታዎች፣ዘፈኖች እየዘፈኑ ያሉት፣ እዚህ ሃገር ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ናቸው።" እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ1984 የተመሰረተው፣  የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣እጅግ የበለጸገውን የኢትዮጵያ ባህልና ቅርሳ ቅርሶች ማስተዋወቅ ዋነኛ ግቡ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። ፌዴሬሽኑ በቅርቡ የተወሰኑ የአመራር ለውጦች ማድረጉንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል። 
 "32 ቡድኖች ነው ያሉት፣ከ32 ቡድኖች እየተመረጡ እየተጠየቁ በጎ ፈቃደኞች እንዲሆኑ ነው ምርጫ የሚደረገው።ባለፈው ዓመት የውድድር አስተባባሪና  የሕዝብ ግንኙነታችን ያላቸውን የስራ ጊዜ ጨርሰው ስራቸውን በሚገባ አስረክበው አዲሶች ደግሞ ተተክተዋል። ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ፣እኛም ስራችንን አስረክብን ለሚቀጥለው እናስረክባለን። 
 

41 ኛዉ የኢትዮጵያ የባህልና ስፖርት ትርዒት በሰሜን አሜሪካ በድምቀት ጀመረምስል Tariku Hailu/DW

የኢትዮጵያውያን ቀን 
አዲሱ የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የአቶ ያሬድ ነጋሽ በበኩላቸው እንደገለጹልን፣የመርሐ ግብሩ አካል የሆነውና የፊታችን ዐርብ ለሚከበረው፣የኢትዮጵያውንን ቀን ባማረ ሁኔታ ለማካኼድ ዝግጅት ተደርጓል።  "ዐርብ ቀን የሚካኼደው፣የኢትዮጵያውያን ቀን በከፍተኛ ሁኔታ ባማረ በደመቀ ሁኔታ የሚከበረው እሱ ዝግጅት ነው።ለእሱ ፕሮግራም የተለያዩ ከሀገር ቤትም ምክር ከዉጪ ከዚሁ ከአሜሪካ ውስጥም ያሉ የተለያዩ ታዋቂ ድምፃውያን የባህልና ተወዣዋዦችን ጋብዘናል።የኢትዮጵያ ቀን አምሮ ደምቆ አሸብርቆ የሚከበርበት ቀን ነው የሚሆነው ብለን እናምናለን።" 
በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከመላው ዓለም ጭምር በሚታደሙበት በዘንድሮው የአትላንታው ዝግጅት ላይ፣32 የእግር ኳስ ቡድኖች እንደሚሳተፉበት አቶ ያሬድ ጠቁመዋል። 
"32 ቡድኖች አሉ።በፌዴሬሽኑ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ክለብ ሆነው 32 ክለቦች አሉ። እነዚህ 32 ቡድኖች 16 በአንደኛ ዲቪዚዮን፣ 16 በሁለተኛ ዲቪዚዮን  ትልቅ ውድድር እንደሚያካሂዱ ነው የሚጠበቀው። ታሪክ ለመስራት የሚዘጋጁ ሁለት ቡድኖች አሉ። በፌዴሬሽኑ ታሪክ ውስጥ ብዙ ዋንጫ በመብላት እኩል የሆኑ ሁለት ቡድኖች አሉ።አንድ ከዲሲ አንድ ከሎስ አንጀለስ፤እነሱ ጠንክረው ፉክክር አሳይተው ዋንጫውን በልተው ታሪክ ይሠራሉ ወይ የሚለው እሱም አንድ የምናየው ነው።ኳሱ ጨዋታ መረሳት የሌለበት እኩል እንዲነሳና ዋናው የሚያገናኘን ኳሱን እንዲነሳና እንዲታወስ የምንፈልገው ነገር ነው።የምንፈልገው ነገር ነው፣ብዙ ፉክክር ያለባቸው ጨዋታዎች አሉ።"

 

የፌሬሽኑ የክብር እንግዳ 
ዘንድሮ የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዶች በመሆን ከተጋበዙት መኻከል አንዱ፣ታዋቂው አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ነው። በዝግጅቱ ላይ አግኝተን ያነጋገርነው አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ፣ዝግጅቱ ለእኔ ታሪካዊ ነው ይላል። "አበሻ በሁሉ ቦታ ያሉ ሰዎች፣በእግር ኳስም እንዱሁም የመገናኛና የፍቅር ጊዜ የሚያሳልፉበትና አብረው መልካም ጊዜ፣ የፍቅር ጊዜ የሚያሳልፉበት ነው።ለእኔ ደግሞ ታሪካዊ ነው።41ኛው ዓመት የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌዴሬሽን፣ እኔ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፣በመገኘቴ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘኹትም የክብር እንግዳ አድርገው ስለጋብዙኝ በሁሉ ነገር በጣም ደስ ብሎኛል፤ ደግሞ ኢትዮጵያውያኖች በተለያዩ ቦታ ብዙ ጊዜ ያልተገናኘናቸው የሚያውቁኝ እዚህ በማግኘቴ፣እየደሰትኹ ስለሆነ ለእኔ የተለየ ጊዜ ይሆነኛል ብዬ አስባለሁ።" 
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ፣በአትላንታ ጆርጂያ ያሰናዳው መርሐ ግብር እስከ ፊታችን ቅዳሜ ድረስ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ታሪኩ ኃይሉ 
ነጋሽ መሐመድ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW