1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ሊቀላቀሉ ነው ተባለ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 13 2015

ሥራው "ለትግራይ ክልል ያደላ ነው" የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞችየቀረበላቸው ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ፣ይህ "ትክክል አይደለም"፣ የቀድሞ ተዋጊ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትግራይ ክልል ስለሆነ እንቅስቃሴያችን ክልሉ ላይ ጎላ ይላል ብለዋል።ኮሚሽኑ እንዳለው የሚያቋቁማቸው መንግሥት ላይ ጦር የመዘዙትን እንጂ ከጎኑ ተሰልፈው ለችግር የተዳረጉትን አይደለም።

Äthiopien Addis Abeba | Büro National Rehabilitation
ምስል Solomon Muche/DW

የቀድሞ ተዋጊዎችን ሥልጠናና ግንባታ

This browser does not support the audio element.

ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን በስምንት ክልሎች ከለያቸው 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች መካከል ከመጪው መስከረም እስከ ሕዳር 30 2016 ዓ. ም ድረስ በመጀመሪያ ዙር  75 ሺህ ያህል የቀድሞ ተዋጊዎች እንዲበተኑ ይደረጋል ተባለ። ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ተደርጎ የሥነ ልቦና እና የሙያ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋሉ ከተባሉት ውስጥ አብዛኛዎቹ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ። መልሶ ማቋቋሙ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከመንግሥት ጎን ሆነው የተሰለፉትን የማያካትት ይልቁንም በመንግሥት ላይ መሣሪያ አንስተው የተዋጉትን ብቻ የሚመለከት መሆኑን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ትናንት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረገው ውይይት አስታውቋል።ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ  ዝርዝሩን ያቀርብልናል። 
ከተቋቋመ ስምንት ወራቶች የሞላው ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የመቋቋሙ ዋና መነሻ የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ያደረገው የተኩስ ማቆም የሰላም ስምምነት ሲሆን በሌሎች ክልሎችም "የፖለቲካ ዓላማቸውን በኃይል ለማስፈፀም ወደ ትጥቅ ትግል የገቡትን" ጭምር ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ታልሞም ነው ተብሏል።
ትጥቅ የማስፈታቱን ሥራ መከላከያ ሠራዊት ይከውናል ያለው ኮሚሽኑ በስምንት ክልሎች እስካሁን 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች መለየታቸውንም አስታውቋል። መቀሌ ውስጥ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ተቋቁሟል ያሉት ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በሂደት በሌሎች ክልሎችም እንደየአስፈላጊነቱ ጽ/ቤቶች ይቋቋማሉ ብለዋል።
ሥራው "ለትግራይ ክልል ያደላ ነው" የሚል ጥያቄ በውይይቱ ከተሳተፉ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ጥያቄ የቀረበላቸው  የሥራ ኃላፉው ይህ "ትክክል አይደለም"፣ የቀድሞ ተዋጊ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትግራይ ክልል ስለሆነ እንቅስቃሴያችን ክልሉ ላይ ጎላ ይላል ብለዋል።ኮሚሽኑ የሚሠራው ሥራ መንግሥት ላይ ጦር የመዘዙትን እንጂ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው ለችግር የተዳረጉትን እንደማያካትት ተገልጿል።የወንጀል ተጠያቂነት ሊኖርባቸው የሚችሉ የቀድሞ ተዋጊዎች በሽግግር ፍትሕ ፓሊሲ ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ሥጋት መኖሩ ተጠቅሶ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። የመጀመርያው ዙር ተዋጊዎችን የመበተን ሥራ ከመጪው መስከረም እስከ ታህሳስ 30 2016 ይከናወናል ተብሏል። በዚህም 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎች የሚበተኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 50 ሺህ ያህሉ ከትግራይ ክልል ናቸው ተብሏል። ይህንን ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገው ገንዘብ አብዛኛው ከውጪ ረጂዎች ይገኛል በሚል የታቀደ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ዮneስ ገብረ እግዚአብሔር
 

ምስል Solomon Muche/DW
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW