84ኛው የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2017
የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል
84ኛው የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች የድል በዓል ዛሬ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተከብሯል። የፋሽስት ጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን ዳግም የወረረበትና ከአምስት ዓመታት የአርበኞች ተጋድሎ በኃላ ተሸንፎ የወጣበት ይህ ዕለት፣ በወራሪው ኃይል ወርዶ የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዳግም በክብር የተሰቀለበት ነው። ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ "ይህ ቀን የፋሺዝም እሳቤ እና ፍልስፍና ዳግም እንዳያንሰራራ፣ የቅኝ ግዛት እሳቤም በአፍሪካ ምድር እንዲንኮታኮትና መሸነፍን እንደሚችል ደግመን ለዓለም ሕዝብ ያሳየንበት ነው" ብለዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የታደሙ የአርበኞች ቤተሰቦች በበኩላቸው ይህ ትውልድ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እንዲያዳብር ብሎም ከመከፋፈል ርቆ አንድነትን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። የአርበኞች ድል 84 ኛው ዓመት ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው የአርበኞች መታሰቢያ ሐውልት ዙሪያ ሲከበር በሥነ ሥርዓቱ ላይ ያገኘናቸው የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማች ልጆችና የልጅ ልጆች ማህበር ፕሬዝዳንት እየሩሳሌም ከበደ ዛሬ ጎሳና ቋንቋን ለልዩነት ለሚያውለው ትውልድ መልእክት አላቸው። "ሁሉ ነገር አለን። ያጣነው አንድነትና ፍቅርን ብቻ ነው። አንዱ አንዱን በመግፋት የሚያሳልፈውን ጊዜ በሥራ ብናሳልፈው ሌሎች የደረሱበት ቦታ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም" በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሕፃናትና ታዳጊዎች በሕብር ዝማሬ፣ አርበኞች እና የአርበኞች ቤተሰቦች በልዩ ልዩ አልባሳትና ሜዳሊያዎች ተውበው፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችም ሀገሮቻቸውን ወክለው ታድመዋል። የኮርያ ዘማች ሰው ልጅ የሆኑት አቶ ወንደሰን ማሞም ተመሳሳይ የአንድነት ሀሳብ አላቸው። 74ኛዉ የድል በዓል
"ወጣቱ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት በውስጡ መላበስ አለበት"
ሌላው ያነጋገርናቸው የበዓሉ ታዳሚ አሥር አለቃ ጉደታ ገልሜሳ የድል ታሪኩ ዘመናትን እየተሸጋገረ መቀጠል ያለበት ነው ይላሉ።
"ለልጆቻችን እያስተላለፍን መሄድ ነው [የሚያስፈልገው]"። 82 ኛዉ የኢትዮጵያዉያን የድል በዓል በድምቀት ተከበረ
የዚህ ወቅት ትውልድ ይህንን የድል ሀብት እንዴት እንያዘው? እንዴት እንጠቀምበት? የሚል የሀሳብ ሸክም አለበት ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ናቸው።
"ኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ሀገር እንድትሆን የበኩላችንን ኃላፊነት እንድንወጣ" ሲሉም ጠይቀዋል። በድል አከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ርእሠ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ይህ የአርበኞች የድል በዓል "ፋሺዝም እና ቅኝ ገዢነት የተሸነፉበት ነው" ብለዋል።
ርእሠ ብሔር ታዬን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት በአርበኞች ሐውልት ሥር የአበባ ጉንጉን ካስቀመጡ በኃላ የድሉ ትምህርት መሆን አለበት ያሉትን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
"ከኢትዮጵያውያን አርበኞች የምንማረው ለሀገራችን ያለንን ፍቅር፣ ለብሔራዊ ነፃነታችን ያለንን ቀናዒነት፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር ያለንን ቁርጠኝነት እና ለራሳችን የምንሰጠው ክብርን ነው" 78ኛው የኢትዮጵያ የድል ቀን
ኢትዮጵያን ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የጣልያን መንግሥት አድዋ ላይ ድል ተነሳ። በዚህ እውነት ክፉኛ የተበሳጨው ፋሽስት ጣልያን ከ40 ዓመታት በኋላ ዳግም ወረራ ፈፀመ። በ1929 የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አውርዶ የራሱን ባንዲራም ሰቀለ። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን በርግጥም ጥንታዊያኑ ለአምስት ዓመታት በብርቱ ታገሉት። በኋላም አሸነፉት። የወረደው የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማም በ1933 በክብር ዳግም ቆመ። ይሄው በዓል በየ ዓመቱ በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ